የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ - ኢዜማ Ethiopian Citizens for Social Justice

  • Home
  • Ethiopia
  • Addis Ababa
  • የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ - ኢዜማ Ethiopian Citizens for Social Justice

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ - ኢዜማ Ethiopian Citizens for Social Justice ዜግነትን መሠረት ያደረገ ፖለቲካን እና ማኅበራዊ ፍትህ እንዲሰፍን እንሰራለን።
(2)

26/08/2026

የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ሒደት እና ፍጻሜን አስመልክቶ
ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትኅ ( #ኢዜማ ) የተሰጠ መግለጫ

ሀገራችን ኢትዮጵያ ላለፉት ዘመናት በርካታ ፖለቲካዊ ቀውሶች ውስጥ አልፋለች። እነዚህ ዘመናትን የተሻገሩ ውስብስብ ችግሮቻችን፣ ሀገራዊ ህልውናችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ፣ የዜጎችን ሰብአዊና ዜጋዊ ደኅንነት የሚሸረሽሩ፣ ከድህነትና ከኋላቀርነት እንዳንወጣ የሚያደርጉ እንዲሁም እንደሀገር የጋራ ማንነት፣ ጥቅም፣ ፍላጎትና ስሜት እንዳናዳብር ያደረጉ ዋነኛ ማነቆዎች ሁነው የቆዩ መሆናቸውን እንገነዘባለን። ፓርቲያችን ኢዜማ ለህዝብ ይፋ ካደረጋቸው መሠረታዊ አቋሞቹ መካከል አንዱና ዋነኛው ሀገራችንን ከግጭት እና የኋላቀርነት አዙሪት ማውጣት የሚቻለው በሰለጠነ ምክክር ብቻ ነው የሚለው እውነት ነው።

ኢዜማ ሀገራዊ ምክክር ሀሳቡ ከተጠነሰሰበት ቀን ጀምሮ በከፍተኛ ሀገራዊ ኃላፊነት፣ በንቃት እና በሙሉ ቁርጠኝነት ሲሳተፍ ቆይቷል። የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የማቋቋሚያ አዋጁ ሲዘጋጅ የሕጉ መንፈስና ይዘት የምንመኘውን ሀገራዊ ግብ ማሳካት በሚችል ጥልቀት እንዲቀርፅ የምክረ-ሐሳብ በማቅረብ በንቃት ተሳታፊ ነበርን። አዋጁ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲፀድቅና ኮሚሽነሮች ሲሰየሙ፣ ገለልተኛና ብቁ የሆኑ አካላት ወደ ኃላፊነት እንዲመጡ ኢዜማ የራሱን አዎንታዊ ድርሻ አበርክቷል።

የሀገራዊ ምክክሩ ጉባኤ ከመካሄዱ ቀደም ብሎ፣ ሀገራዊ ችግሮቻችንን ለመፍታት ያስችላሉ ያልናቸውን የምክክር አጀንዳዎች በማዘጋጀት ለሕዝብ ያሳወቅን ሲሆን፣ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑም በይፋ አስረክበናል። ኢዜማ ሀገራዊ ምክክሩን በሚመለከት የጋራ ግንዛቤ ለማዳበር እንዲረዳ ያዘጋጀው ሰነድ ውስጥ የሀገር ሕልውና እና ቀጣይነት አደጋ፣ የዜጎች ሰብዓዊና ዜጋዊ ደህንነታቸው መከበር አለመቻል፣ ከድህነትና ከኋላቀርነት መላቀቅ አለመቻል፣ እንዲሁም የጋራ ማንነት፣ ጥቅም፣ ፍላጎትና ስሜት አለመዳበር የሚሉ አንኳር ነጥቦችን ያካተተ ነበር።

ሀገራችን ኢትዮጵያ በርካታ ማንነቶች፣ ጥቅሞች፣ ፍላጎቶች እና ስሜቶች በሚንጸባረቁበት ውስብስብ ሀገራዊ ሁኔታ ውስጥ የምትገኝ በመሆኑ፣ ይህንን ፈታኝ ሁኔታ መወጣት የምንችለው በአርቆ አሳቢነት፣ በሆደ-ሰፊነት፣ በከፍተኛ እውቀት እና ብልሃት የታገዘ ንቁ ተሳትፎ ከማድረግ ውጪ ሌላ ለሀገር የሚበጅ የተሻለ አማራጭ እንደሌለን ታሳቢ አድርገናል። በሀገራዊ ምክክሩ በተመለከተ የምናቀርበው ምክረ ሃሳብና የምንወስነው ውሳኔ ከኛ ከራሳችን የቡድንም ሆነ የግል ጥቅምና ፍላጎት ይልቅ የሀገራችን የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅምና ፍላጎት የሚያስቀድም ሊሆን ይገባል ብለን በምንችለው ሁሉ ሠርተናል።

ሀገራዊ ምክክሩ በይፋ ከተጀመረበት ሐምሌ 08 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ባለው ረጅም እና እልህ አስጨራሽ ሂደት ውስጥ በርካታ ስልታዊ ማነቆዎችና አሠራርን ያላከበሩ ችግሮች ባጋጠሙን ወቅት፣ ሂደቱ እንዳይበላሽ በማሰብ ጉዳዩን ወደ አደባባይ ከማውጣት ይልቅ ለኮሚሽኑ ምክር ቤት ቅሬታዎቻችንን በተደጋጋሚ ያቀረብን ሲሆን፣ በአካልም ከኮሚሽኑ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመወያየት የማረሚያ ሀሳቦችን አቅርበናል። በርካታ ችግሮችንም በዚሁ መንገድ ፈትተናል።

እንደማሳያም አንዳንድ በኤክስፐርትነት እና በአስተባባሪነት ስም የተመደቡ አካላት በምክክሩ ሂደት ያንጸባርቁት የነበረውን ግልጽ ወገንተኛነት እና የተዛባ አካሄድ በጽናት እየተከላከልን፣ ሂደቱ ሀገራዊ ተስፋን እንዳያከስም በሚል እምነት እስከ ፍጻሜው ለማድረስ ከፍ ያለ ዋጋ ከፍለናል።

እንደ ኢዜማ ሀገራዊ ምክክሩ በይፋ ከተጀመረበት እለት አንስቶ በይፋ እስከተጠናቀቀበት እለት ድረስ በከፍተኛ ሀገራዊ ኃላፊነት ንቁ ተሳትፎ ስናደርግ የቆየን ሲሆን ችግሮች ተከስተዋል ብለን ባመንንበት ግዜ ሁሉ ለኮሚሽኑ የእርምት እርምጃዎች እንዲወሰዱ በማሳሰብ እና መተግበራቸውን ጭምር በመከታተል ሂደቱ ትርጉም እንዲኖረው የበኩላችንን አስተዋፅኦ ተወጥተናል ብለን እናምናለን።

በምክክሩ ማጠናቀቂያ እለት ማለትም ነሐሴ 13 ቀን 2018 ዓ.ም. ለሁሉም የሥራ ቡድኖች (ለ4000 ተመካካሪዎች) የስምንቱም አጀንዳዎች ምክረ-ሐሳቦች በንባብ የቀረቡ ሲሆን፣ ኢዜማ በ8ቱ የምክክር ቡድኖች በጥቅሉ ተመካካሪዎች በውይይት አጎልብተውት፣ በሙሉ ድጋፍ ፈርመውበት ለጠቅላላው ጉባኤ ያቀረቧቸውን ምክረ-ሐሳቦች ብቻ የሚቀበላቸው መሆኑን እንገልጻለን።

በአጠቃላይ ሀገራዊ ምክክሩ የነበረው ሐደት ከነጉድለቶቹም ቢሆን እንደ መልካም ጅምር የምንወስደው እና ወደፊትም በሀገራችን ያሉትን ቀሪ ችግሮች በተመሳሳይ ከጠብመንጃ አፈሙዝ ውጪ በሆነ መልኩ በጠረጴዛ ዙሪያ ብቻ መፍታትን ልማድ እንድናዳብር አዲስ በር የሚከፍት መልካም ጅማሬ አድርገንም እንወስደዋለን።

የምክክር ሒደቱ የመመካከሪያ ምዕራፉ ቢጠናቀቅም የሒደቱ ወሳኝ ምዕራፍ የሆኑት በኮሚሽኑ የመጨረሻውን ምክረ ሀሳቦች ለመንግሥትና ለህዝብ የሚያቀርቡበት ሂደት እና የትግበራ ሂደት ገና ይቀራል። እነዚህ ሁለት ዋና ምዕራፎችም በጥንቃቄ እንዲያዙ ኢዜማ የሚከተሉትን አምስት ማሳሰቢያዎች መስጠት ይወዳል፡፡

1. የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለመንግሥትና ለሕዝብ የመጨረሻ ምክረ ሀሳቦችን በሚያቀርብበት ወቅት በአጠቃላይ የምክክሩን መንፈስ እና የተመካካሪዎችን በንባብ የቀረበውን የመጨረሻ ምክረ-ሀሳብ ብቻ ባከበረ መልኩ እንዲሆን፤

2. ኮሚሽኑ በተመካካሪዎች የቀረቡትን 400 ምክረ ሀሳቦች ለህዝብ ይፋ እንዲያደርግ ፤

3. በምክክሩ ሒደት ከጥቃቅን ቡድኖች ጀምሮ ያደረግናቸውን ውይይቶች ቃለጉባዔዎች በማገናዘብ እንዲከወን፤ እንዲሁም በማቋቋሚያ አዋጁ መሰረት የምክረ ሀሳቦቹን አፈፃፀም እንዲከታተል፤

4. መንግሥት የሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ውጤታማ የሚሆነው የቀረቡት ምክረ ሀሳቦች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሲደረጉ እንደመሆኑ አፈፃፀሙም ከተገቢው በላይ ግዜ እንዳይወስድ በፍጥነት እንዲፈፀም እንዲያደርግ ፤

5. የሀገራዊ ምክክሩ ምክረ ሃሳቦችን አተገባበር የሚከታተል ገለልተኛ እና ሕጋዊ አካል አንዲቋቋም እንጠይቃለን።

በመጨረሻም ሀገራዊ ምክክሮችን በማድረግ ልዩነቶቻችንን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የምናደርገው ሒደት ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን፤ በዚህ ረጅም ሀገራዊ ምክክር ውስጥ የተስተዋሉ የሒደት ጉድለቶች ቢኖሩም እንኳን በመጨረሻ የመጣው ውጤት የሚያበረታታ፤ ተስፋ ሰጪ እና የመመካከርን አስፈላጊነት በጉልህ ያሳየ፣ እንደ ሀገርም በጣም ጠቃሚ ፣ እንደ ፓርቲም ብዙ የተማርንበት መሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
ነሐሴ 20 ቀን 2018 ዓ.ም.

ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ1 ሺህ 501ኛው የነብዩ መሀመድ የልደት በዓል (መውሊድ) በሰላም አደረሳችሁ።መልካም በዓል!የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) #ኢዜማ ...
24/08/2026

ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ1 ሺህ 501ኛው የነብዩ መሀመድ የልደት በዓል (መውሊድ) በሰላም አደረሳችሁ።

መልካም በዓል!

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)

#ኢዜማ
#ኢትዮጵያ

በ  #ኢዜማ ዕይታ፤ «ያለን አንድ ሀገር ነው፤ በዚህ ሀገር ውሰጥ የሚኖር ሕዝብ አንድ ሕዝብ ነው» ይኽ ማለት ይህ ሕዝብ አንድ ቋንቋ፣ አንድ እምነት እና አንድ ባህል ብቻ ያለው ሕዝብ ነው ...
05/08/2026

በ #ኢዜማ ዕይታ፤

«ያለን አንድ ሀገር ነው፤ በዚህ ሀገር ውሰጥ የሚኖር ሕዝብ አንድ ሕዝብ ነው» ይኽ ማለት ይህ ሕዝብ አንድ ቋንቋ፣ አንድ እምነት እና አንድ ባህል ብቻ ያለው ሕዝብ ነው ማለት አይደለም።

#ኢዜማ
#ኢትዮጵያ

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ምርጫ ክልል የ  #ኢዜማ አባል የሆኑት ደምስ ገብሬ በኃላፊነት የሚመሩት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ...
31/07/2026

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ምርጫ ክልል የ #ኢዜማ አባል የሆኑት ደምስ ገብሬ በኃላፊነት የሚመሩት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በድጋሚ ስኬታማ ዓመትን አሳለፈ።

በክልሉ ሳይንስ፣ ኢንፎርሜሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ በተካሔደው የ 2018 ዓ.ም. የአፈፃፀም ምዘና የዞኑ መምሪያ 97.4 % እንዲሁም በኮደርስ አፈፃፀም 98.3 በማምጣት ክክልሉ 1ኛ ሆኖ በማጠናቀቅ የዕውቅና እና የተለያዩ ሽልማቶች ተበርክቶለታል።

ከዚህ ቀደም ይኸው መምሪያ በአባላችን እየተመራ ባለፈው 2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማና የ2018 እቅድ መድረክ ላይ በአጠቃላይ አፈፃፀም 1ኛ በመውጣት ሽልማት እንደተበረከተለት ይታወሳል።

ኢዜማ እሴቶቼ ናቸው ሲል ካስቀመጣቸው መካከል አንደኛው ልኅቀት (Excellence) ሲሆን የሀገራችን በርካታ ችግሮች መፍትሔ ማግኘት የሚችሉት ልኅቀትን መመዘኛ ባደረገ የሥራ ውጤት መለኪያ ብቻ ነው የሚል ጠንካራ እምነት ያለው ሲሆን ይህንን ልህቀት ለሚያሳዩ አባላት እንዲሁም የፓርቲው ልዩ ልዩ አሀዶች ዕውቅናን እንደሚሠጥም በግልጽ አስቀምጧል።

በዚሁ መሠረት የፓርቲያችን አባል ደምስ ገብሬ በአመራርነት ለተቋሙ ስኬታማነት ከሌሎች ሠራተኞች ጋር በመሆን ለዚህ ውጤት ላበረከቱት አስተዋፅኦ ምስጋና እያቀረበ በተጨማሪም ከፍ ያለ ኩራት እንደተሠማው ለመግለጽ ይወዳል።

#ኢዜማ
#ኢትዮጵያ

ከሐምሌ 08/2018 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሔደ ባለው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ፤ በተለዩት አጀንዳዎች ላይ ለመወያየት ከተደረገው ምደባ ጋር በተያያዘ የነበረውን ቅሬታ እንዲሁም እንዴት ተፈታ የሚለ...
22/07/2026

ከሐምሌ 08/2018 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሔደ ባለው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ፤ በተለዩት አጀንዳዎች ላይ ለመወያየት ከተደረገው ምደባ ጋር በተያያዘ የነበረውን ቅሬታ እንዲሁም እንዴት ተፈታ የሚለውን አሰመልክቶ የኢዜማ ተወካይ ዮሐንስ መኮንን ከebs television ጋር ያደረጉትን ቆይታ ይከታተሉ።

#ኢዜማ
#ኢትዮጵያ

EBS TV-Watch on Roku(PC/Mac & iPhone/iPad & Android Devices) : http...

የኢዜማ ም/መሪ ንጋቱ ወልዴ ሀገራዊ ምክክርን አስመልክቶ ከ NBC ETHIOPIA ጋር ያደረጉትን ሙሉ ቆይታ ይመልከቱ!! #ኢዜማ    #ኢትዮጵያ
18/07/2026

የኢዜማ ም/መሪ ንጋቱ ወልዴ ሀገራዊ ምክክርን አስመልክቶ ከ NBC ETHIOPIA ጋር ያደረጉትን ሙሉ ቆይታ ይመልከቱ!!

#ኢዜማ
#ኢትዮጵያ

National Media SC is here to support, the success of our country's ...

ለሰላም የቀረበውን ጥሪ አስመልክቶ ከኢዜማ የተሠጠ የድጋፍ መግለጫ!!በ 8 ፓርቲዎችና 11 ሲቪክ ማሕበራት የተቋቋመው የትግራይ ሰላምና ለውጥ ፈላጊዎች እንቅስቃሴ ሕጋዊ አካልነቱን ባጣው ሕወሓ...
17/07/2026

ለሰላም የቀረበውን ጥሪ አስመልክቶ ከኢዜማ የተሠጠ የድጋፍ መግለጫ!!

በ 8 ፓርቲዎችና 11 ሲቪክ ማሕበራት የተቋቋመው የትግራይ ሰላምና ለውጥ ፈላጊዎች እንቅስቃሴ ሕጋዊ አካልነቱን ባጣው ሕወሓት አማካኝነት በትግራይ ህዝብ ላይ እየተደረገ ያለው አፈና፣ ስቃይ እና እንግልት እንዲቆም እና ጦርነት እንዲቀር ጫና ለማድረግ ያለመ የሰላማዊ ሰልፍ በአዲስ አበባ እንደጠራ መረጃ ደርሶናል፤ የለውጥ እንቅስቃሴው ሁሉም ይህን ሰላማዊ ዓላማ የሚደግፉ ኢትዮጵያውያን በሰልፉ ድጋፋቸውን እንዲሰጡም ጥሪ አቅርቧል።

ፓርቲያችን ኢዜማ የትግራይን ህዝብ ከዳግም ጦርነት እና ስቃይ ለማዳን የሚደረጉ ሰላማዊ እንቅስቃሴዎች ሁሉ እንደሚደግፍ በተደጋጋሚ በገለፀው መሠረት ለዚህ ሰላማዊ ሰልፍ ይፋዊ ድጋፉን እየገለፀ የኢዜማ አባላትና ደጋፊዎችም በሰልፉ በመገኘት እምቢ ለጦርነት የሚል ድጋፋቸውን እንዲያሳዩ ጥሪውን ያቀርባል።

እምቢ ለጦርነት!
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)

#ኢዜማ
#ኢትዮጵያ

16/07/2026

የኢዜማ ም/መሪ ንጋቱ ወልዴ ሀገራዊ ምክክሩን አስመልክቶ ከ NBC Ethiopia ጋር ያደረጉትን ቆይታ ነገ ሐምሌ 10/2018 ዓ.ም ከምሽት 3:00 ሰዓት ጀምሮ ይከታተሉ።

#ኢዜማ
#ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) አመራሮች እና የቋሚ ኮሚቴ አባላት በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ለመወያያነት የቀረቡ አጀንዳዎችን ፓርቲው ለሃገራዊ ምክክር ካዘጋጃቸው አጀንዳዎች አንፃ...
11/07/2026

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) አመራሮች እና የቋሚ ኮሚቴ አባላት በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ለመወያያነት የቀረቡ አጀንዳዎችን ፓርቲው ለሃገራዊ ምክክር ካዘጋጃቸው አጀንዳዎች አንፃር ፈተሹ።

ውይይቱን የፓርቲው መሪ ኢዮብ መሣፍንት እና ሊቀመንበሩ ዶ/ር ሙሉዓለም ተገኘወርቅ ባቀረቡት መነሻ ሐሣብ የተጀመረ ሲሆን ተሳታፊዎች ተጨማሪ ሐሣቦችን አቅርበው ተወያይተዋል።

የውይይቱን መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የፓርቲው ምክትል ሊ/መንበር ማዕረጉ ግርማ ሀገራዊ ምክክር የኢዜማ ጉዳይ ብቻ እስኪመስል የተከታተልነው ዓበይት ጉዳይ መሆኑን ገልፀው በጉባኤውም ፓርቲውን ወክለው የሚሣተፉ አመራሮች ምን ያህል እንደተዘጋጀንበት እንደሚያሣዩ ጥርጥር የለኝም ሲሉ ገልፀዋል፤ መድረኩን የፓርቲው ም/መሪ ንጋቱ ወልዴ መርተውታል።

#ኢዜማ
#ኢትዮጵያ

Address

Ras Desta Damtew Street
Addis Ababa

Opening Hours

Monday 08:00 - 17:00
Tuesday 08:00 - 17:00
Wednesday 08:00 - 17:00
Thursday 08:00 - 17:00
Friday 08:00 - 17:00
Saturday 08:00 - 12:00

Telephone

+251944107661

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ - ኢዜማ Ethiopian Citizens for Social Justice posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The Organization

Send a message to የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ - ኢዜማ Ethiopian Citizens for Social Justice:

Shortcuts

Share