Motivated, Competent and Compassionate /MCC/ Health Workforce / Ethiopia

Motivated, Competent and Compassionate /MCC/ Health Workforce / Ethiopia Motivated Competent, Care, respect and compassionate Health work force

05/09/2023

+++የ2016 ባሕረ ሐሳብ አወጣጥ በአባ አትናቴዎስ +++
ሼር በማድረግ ለሌሎቹም ያጋሩ
በ2016 ዓመተ ምህረትየሚውሉ አጽዋማት እና በዓላት ከቅዱስ ድሜጥሮስ ታሪክ ጋር በቀመረ ድሜጥሮስ

ባሕረ ሐሳብ ማለት ምን ማለት ነው
ባሕረ ሓሳብ ማለት ከሁለት ጥምር ቃላት የተገኘ ሕብረ ቃል ሲሆን ትርጉሙም፤
ባሕር ማለት ዘመን ማለት ነው። “በመዳልው ደለወ ዓለመ ወበመሥፈርት ሰፈራ ለባሕር” እንዲል።
ሐሳብ ማለት ደግሞ ቁጥር ማለት ነው። ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “ብፁዓን እለ ተኀድገ ሎሙ ኃጢአቶሙ ወእለ ኢሐሰበ ሎሙ ኲሎ ጌጋዮሙ - ኃጢአታቸው የተተወላቸው በደላቸውንም ያልቆጠረባቸው ንዑዳን ናቸው ” /መዝ 31፡1/በማለት እንደተናገረው ሐሳብ ማለት ቁጥር የሚል ትርጉም ይይዛል።

ባሕረ ሐሳብን ማን ደረሰው †

ባሕረ ሀሳብን ለማወቅ ብዙ አበው የተመኙ እና የደከሙ ቢሆንም የተገለጸው ግን ለእስክንድርያ 12ኛ ሊቀ ጳጳስ ለነበረው ለቅዱስ ድሜጥሮስ ነበር። እርሱም ልክ እንደ ቅዱስ ሕርያቆስ የቤተክርስቲያን ዕውቀት ያልነበረው ዳሩ ግን መስተገብረ ምድር /ገበሬ/ ነበር። የርሱ አባት እና አጎቱ በዘመነ ሰማዕታት ከኢየሩሳሌም ተሰደው ከባዕድ ሀገር ይኖሩ ነበር። የድሜጥሮስ አባት እንደራኒቆስ ሲባል አጎቱ ደግሞ አስተራኒቆስ ይባላል። ለአስተራኒቆስም ልእልተ ወይን የተባለች መልከመልካም ልጅ ነበረችው። የእረፍቱ ጊዜ ሲደርስም /በዚያ ስፍራ ከነርሱበቀር ሌላው ሁሉ አሕዛብ ነበርና/ “ልጄን ለአሕዛብ እንዳትድራት ብሎት ሞተ”።

ሁለቱም ለአቅመ አዳም ወሔዋን ሲደርሱ እንደራኒቆስ የወንድሙን አደራ በማስታወስ “ለአሕዛብ አጋብቼ ሕንፃ ሃይማኖት ከሚፈርስ ሕንፃ ሥጋ ቢፈርስ ይሻላል” በማለት ልእልተ ወይንን እና ቅዱስ ድሜጥሮስን ያጋቧቸዋል። በሠርጋቸውም ዕለት ማታ ሥርዓተ መርዓት ወመርዓዊ እንዲፈጽሙ ከጫጉላ ሲተዉአቸው እነርሱ ግን የወንድማማች ልጆች ስለሆኑ ሩካቤ ለመፈጸም ባለመፈለጋቸው በሐዘን ተውጠው ያለቅሱ ጀመር።

ልእልተ ወይንም “ይህን የሠራኸው እኔን ንቀህ ነው ወይስ ተዛምዷችንን” አለችው። እርሱም እህቴ የአባቴን ፈቃድ ለመፈጸም እንጂ አንቺንም ሆነ ተዘምዷችንን ንቄ አይደለም አላት ከዚህ በኋላ ፈቃድሽ ከሆነ ብንለያይ አንቺን ለሌላ አህዛባዊ እኔንም ለሌላ አህዛባዊት ያጋቡናል ተስማምተን ንጽህ ጠብቀን ባልና ሚስት መስለን እንኑር መከኑ ሰነፉ ይሉናል እንጂ በዚህ የሚጠረጥረን የለም አላት በዚህሜ ሐሳብ ተስማምተው በሩካቤ ሳይተዋወቁ 48 ዓመት ተቀመጡ ።

በንጽሕናም ሲኖሩ መልአከ እግዚአብሔር አንድ ክንፉን ለልዕተ ወይን አንድ ክንፉን ለድሜጥሮስ አልብሷቸው ይተኙ እና ጠዋት በርግብ አምሳል በመስኮት ሲወጣ ይታያቸው ነበር።

እንዲህም ባለ የንጽህና ጉዞ 48 ዓመታትን አብረው ከኖሩ በኋላ የእስክንድርያው 11ኛ ሊቀ ጳጳስ ዮልያኖስ የእረፍቱ ጊዜ ደርሶ ነበር እና ከርሱ ቀጥሎ የሚሾመው ማን እንደሆነ ለመንገር ሕዝቡን በቤተክርስቲያን ጠራ።

ቅዱስ ድሜጥሮስም ድኮ ታጥቆ ሞፈር አርቆ የሚኖር ነበረና ወደእርሻው በገባ ግዜ ያለ ጊዜዋ የደረሰች የወይን ፍሬ አገኘ ይህ ለሊቀ ጳጳሱ ይገባል እንጂ ለኛ አይገባም ብሎ ወደ ቤቱ ሔደ ለልዕተ ወይን ሰጣት ልዕልተ ወይንም ይህ ለሊቀ ጳጳሱ ይገባል እንጂ ለኛ አይገባም ብላ በመሶበ ወርቅ አድርጋ ሰጠችው
ለሊቀ ጳጳሱ ይዞ ሄደ ሊቀ ጳጳሱም በሰጠው ጊዜ ከርሱ ቀጥሎ እንደሚሾም በሱባኤ ስለተገለጠለት ቅብዓ ሜሮን ቀብቶ ሥርዓተ ጵጵስናን ፈጽሞለታል ብለው ይናገራሉ መተርጉማን ። ይህ ሲሆን ግን ቅዱስ ድሜጥሮስ አላወቀም ነበር።

ከጥቂት ቀናትም በኋላ ሊቀ ጳጳሱ ሲያርፍ ከርሱ ቀጥሎ ሊቀ ጳጳስ የሚሆነው ቅዱስ ድሜጥሮስ እንደሆነ ነግሯቸው ነበርና መንበር ብቻውን አያድርም በማለት ሂደው በመንበረ ማርቆስ ላይ ሊቀ ጳጳስ እንደሚሆን ነገሩት። እርሱ ግን “እኔ በአንድ በኩል ያልተማርኩ ገበሬ ነኝ፣ በዚያውም ላይ ሕጋዊ ነኝ። እንዴት ንጹሁ በነበረበት እኔ ሕጋዊው
ጻድቁ በነበረበት እኔ ኃጥኡ
የተማረ በነበረበት እኔ መሐይሙ እንዴት ይሆናል አይሆንም አላቸው

አይሆንም ቢላቸው እነርሱ ግን አባታችን ግብር ገብቶ ሱባዔ ይዞ ነግሮናል ብለው ግድ አሉት አስቀመጡትም። በዮልያኖስ ፈንታ ተሾመ

ለድሜጥሮስም ቅዳሴ እና መጻህፍት ተገልጠውለት ሕዝቡን ያስተምራቸው ጀመር። ከንጽሕናውም የተነሳ የሕዝቡ ሁሉ ኃጢአት ይታየው ነበር እና አንተ በቅተሀል ተቀበል አንተ ንስሐ ግባ እያለ ይመልሳቸው ጀመር። ሕዝቡም “እርሱ ሚስቱን አቅፎ እየተኛ በንጹሑ መንበረ ማርቆስ ላይ ብናስቀምጠው ጭራሽ ይከለክለን ጀመር በማለት በሐሜት ሲጎዱ መልአከ እግዚአብሔር ተገልጾለት ሕዝቡ በሐሜት ስለተጎዳ ኢትፍቅድ አድህኖ ርዕስከ ራስህን ማዳንን አትፍቀድ አለው በልዕልተ ወይንና በርሱ መካከል ያለውን ንጽሕናቸውን እንዲገልጽላቸው ይነግረዋል። ድሜጥሮስም ሕዝቡ ሁሉ እንጨት እንዲያመጡ ነግሯቸው አንድ አንድ ሸክም ዕንጨት እየያዙ መጡ ያንን እንደ ደመራ አስደምሮ ቅዳሴ ገባ።

ከቅዳሴም በኋላ በደመራው እሳት ውስጥ እየተመላለሰ ያጥን ጀመር። ልእልተ ወይንንም ከምቋመ አንስት/ከሴቶች መቆሚያ/ አስጠርቶ “ስፍሒ አጽፈኪ - ልብስሺን ዘርጊ” በማለት ፍሕሙን እያነሳ በልብሷ ላይ ጨመረ እና እየዞረች ለሕዝቡ ሁሉ አሳየች። እርሷም ሆነ ልብሷ ምንም በእሳቱ አልተነኩም ነበር። ድሜጥሮስንም ምንድነው ይህ ነገር አባታችን ብለው ሲጠይቁት ለ48 ዓመት አብረው ሲኖሩ በግብረ መርዓት ወመርዓዊ/በተራክቦ/ እንደማይተዋወቁ ሲገልጥላቸው ሕዝቡ ሁሉ በመጸጸት አባ ሥረይ ለነ እያሉ ይቅርታ ጠየቁ። እርሱም “ይፍታ ያንጽሕ ወያስተሥሪ” ሊቅ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ናዝዟቸዋል ኑዛዜ በዚህ ጊዜ ተጀምሯል ።

ይህም ቅዱስ አባት በመንበረ ጵጵስናው ሳለ አንድ ትልቅ ተምኔት ነበረው። ጾመ ነነዌ ዐቢይ ጾም እና ጾመ ሕዋርያት ከሰኑይ፣ ደብረ ዘይት ሆሳዕና ትንሳኤ እና ጰራቅሊጦስ ከእሑድ፣ ርክበ ካህናት እና ጾመ ድኅነት ከረቡዕ፣ ዕርገት ከሐሙስ ስቅለት ከዓርብ ባይወጣ እያለ ይመኝ ነበር። ምክንያቱም እሊህ በዓላት ለመጀመሪያ ጊዜ የዋሉት በእነዚህ ዕለታት ስለነበር ነው።

እንዲህም እያለ ሲመኝ የታዘዘ መልአክ ወደርሱ መጥቶ በምኞት ብቻ እንደማይሆን ነግሮት ሱባኤ እንዲገባ ይነግረዋል። “ከሌሊቱ 23 ሱባኤ ግባ እና አበቅቴ ይሁንህ፤ ከቀኑ 7 ሱባኤ ግባ እና መጥቅዕ ይሁንህ” ብሎታል።

ሌሊቱን አብዝቶ ቀኑን ማሳነሱ ለምንድነው ቢሉ ቀኑን የተጣላ ሲያስታርቅ፣ የታመመ ሲጠይቅ ሲያስተምር እንዲህ ባለው ሁሉ ግብር ስለሚያሳልፍ ነው።

ሌሊት ግን ይህ ሁሉ የለበትምና ከዚህም ጥንተ አበቅቴ እና ጥንተ መጥቅዕ ይገኛሉ።
አዋጅ፦ ማንኛውም ቁጥር ከ30 ከበለጠ በ30/በዐውደ ወርኅ/ ይገደፍና ይተዋል ።
የቀኑን ስናሰላ
አንድ ሱባኤ ማለት ሰባት ዕለት ነው።
7×7=49 ይህንም በ30 ስንገድፈው 1 ጊዜ ይደርስና 19 ይቀራል። ይህም ጥንተ መጥቅዕ ይባላል።
ይህም መጥቅ ከዕለታት ተውሳክና ከአጽዋማትና ከበዓላት ጋር ተደምሮ ከ30 ከበዛ ሰላሣውን ገድፎ ትርፉን እየያዙ ማውጫ ነው

23×7=161 ይህንም በ30 ስንገድፈው 5 ጊዜ ይደርስና 11 ይቀራል። ይህም ጥንተ አበቅቴ ይባላል።
ሌሎች ቀመሮች ላይ ሌሊትን ለማውጣት እና የየዓመታቱን አበቅቴ ለማውጣት እንገለገልበታለን።

ይህም በተለይም ካህናት ጸሎትን ለማሣረግ አሥርቆት የሚያደርጉበት ነው።
ባሕረ ሐሳብን ማን መማር አለበት? †
በጉባኤ ቤት ከመጻሕፍት ጉባኤ ጋር በአንድነት የሚሰጥ ትምህርት ነው። በዚህም ካህን የሆነ ሁሉ በበረሀ ጥላ ሥር እንዳለች ምንጭ የሚያረካ እንዲሆን መማር አለበት። ምክንያቱም በዓላትን እና አጽዋማትን አውጥቶ ለልጆቹ መንገር አለበት እና ነው።
ምእመናንም ቢሆኑ በተለያየ ምክንያት ከሀገር የሚወጡበት አጋጣሚ ስለሚኖር በባዕድ ሀገር ሁነው በዓላትን በአግባቡ ለማክበር እና አጽዋማትን ለመጾም ማወቅ ያስፈልጋቸዋል።

ጥንታት ሦስት ናቸው
የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር የሚጀምረው ከጥንታት ነው። ጥንትነቱም ከፍጥረተ ዓለም፣ ከፍጥረተ ፀሐይ፣ ከፍጥረተ ጨረቃ እና ክዋክብት ነው። ዓለም የተፈጠረበት ዕለተ እሁድ ጥንተ ዕለት ይባላል። እንዲህም መባሉ ፍጥረታት መፈጠር የጀመሩበት እለት በመሆኑ ነው።
አዝርዕት ዕጽዋት እና አትክልት የተፈጠሩበት እለተ ሠሉስ ደግሞ ጥንተ ቀመር ይባላል። ቁጥር የተጀመረበት እለት ስለሆነ ነው።
ፀሐይ ጨረቃ እና ክዋክብት የተፈጠሩበት ዕለተ ረቡዕም ጥንተ ዖን/ዮን/ በመባል ይታወቃል። ዖን ማለትም ብርሃን ማለት ነው። በመጽሐፍ “ዖን ይእቲ ስማ ለፀሐይ” እንዲል

የእስክንድርያ 12ኛ ሊቀ ጳጳስ (ፓትርያርክ) የነበረው ቅዱስ ድሜጥሮስ

ከ180-222 ዓ.ም ድረስ ለ 42 ዓመት ሊቀ ጳጳስ ነበር ይላል ታሪኩ ሊቀጳጳስ ከመሆኑ በፊት መስተገብረ ምድር (ገበሬ)ነበር ሞፈር አርቆ፣ በአጭር ታጥቆ የሚሰራ ትጉህ ገበሬ ነበርከልዕልተ ወይን (የቤተክርስቲያን ለቃውንት የሚጠሯት ስም) ጋር አጋብተዋቸው ነበር።

ቤተ ክርስቲያን አራት ጉባዔ ቤቶች አሏት

· ብሉይ ኪዳን

· ሐዲስ ኪዳን

· መጽሐፈ መነኮሳት (ማር ይስሐቅ፣ ፈልክስዩስ)

· ሊቃውንት (ሃይማኖተ አበው)

· አምስተኛ ጉባዔ ተደርጐ በሁለት መንገድ ይሰጣል። አቡከክር (አቡካኻር) ባሕረ ሀሳብ ተብሎ

አቡካኻር (ወልደ አቤል ሄሬም) የተባለ መነኩሴ ሲሆን ባሕረ ሐሳብን ጨምሮ ሌሎች የሥነ ጸሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት ሊቅ ነው። ባሕረ ሀሳብም አብሮ ተገልጾለታል።

ከዲሜጥሮስ በተጨማሪ ባሕረ ሀሳብን ለማወቅ የተመኙ

1. ሰዒድ ወልደ ጰጥሪቅ

2. መሀቡብ ወልደ መንጋ

3. ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

4. ኤጲፋንዮስ ዘመንፈስ ቅዱስ

5. ጊዮርጊስ ወልደ አሚድ

6. ማርቆስ ወልደ ቀምበር

7. ዮሐንስ ወልደ አቤልሔሬም (አቡካክር) … እና ሌሎችም

የቅዱስ ድሜጥሮስ ምኞት

Ø በዓላትና አጽዋማት ከጥንተ ዕለታቸው ባይወጡ ባይነዋወጡ እያለ ይመኝ ነበር። ይኸውም

· ጾመ ነነዌ፣ ዐብይ ጾም፣ ጾመ ሐዋርያት፣ ከሰኞ፣

· በዓለ ርክበ ካህናት፣ ጾመ ድኅነት ከረቡዕ፣

· በዓለ ዕርገት ከሐሙስ፣

· በዓለ ደብረ ዘይት፣ ሆሳዕና፣ ትንሳኤ፣ ጰራቅሊጦስ ከእሁድ

መልአከ እግዚአብሔር ነገር በምኛት አይሆንም ሱባዔ ገብተህ አግኘው አለው

ከሌሊቱ 23 ሱባዔ ገብተህ አበቅቴ፣

ከቀኑ 7 ሱባዔ ይዘህ መጥቅዕ ይሁንህ ብሎታል

ምነው ሌሊቱን አብዝቶ ቀኑን አሳነሰው? ቢሉ ቀን የተጣላውን ሲያስታርቅ የተበደለውን ስያስክ የታመመውን ሲጠይቅ ይውላል ሌሊት ግን ይህ ሁሉ የለበትምና

23 ሱባዔ ማለት

1 ሱባዔ = 7 ቀናት

23 ሱባዔ = 161 ቀናት

አዋጅ ፦ ማንኛውም ቁጥር ከ30 ከበዛ በ30 ግደፈው ዘይም ለ30 አካፍለው ቀሪውን መያዝ ነው

161 ÷ 30 = 5 ደርሶ ወይም በአምስት ሰላሣ ገድፎ 11 ይቀራል 11 ጥንተ አበቅቴ ይባላል።

ሰባት ሱባዔ ማለት፦

1 ሱባዔ = 7

7 ሱባዔ = 7× 7= 49

በ 30 ስንገድፈው (49÷30) =1 ደርሶ 19 ይቀራል

19 ጥንተ መጥቅዕ ይባላል።

መጥቅዕና አበቅቴ ተደምረው ከ 30 አይበልጡም ፣ ከ 30 አያንሱም

አዋጅ “አበቅቴ ወመጥቅዕ ክልዔሆሙ ኢየዓርጉ እም፴ ወኢይወርዱ እም፴ ወትረ ይከውኑ ፴” ይላል

አዕዋዳት

አዕዋድ ዖደ ከሚል የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ዞረ ማለት ሲሆን በየጊዜው እየዞረ የሚመጣ ማለት ነው።

ዓመተ ዓለም የሚሠፈርበት ሰባት አዕዋዳት አሉ። እነሱም፦

+ ዓውደ ዕለት ከሰኞ - እሁድ

+ ዓውደ ወርኅ በፀሐይ 30 ቀናት፤ በጨረቃ 29ና 30

+ ዓውደ ዓመት- በፀሐይ 365 ቀናት 6 ሰዓት (15 ኬክሮስ)፤ በጨረቃ 354 ከ 22 ኬክሮስ

+ ዓውደ አበቅቴ (ንዑስ ቀመር) = 19 ዓመት

+ ዓውደ ፀሐይ = 28 ዓመት

+ ዓውደ ማኅተም (ማዕከላዊ ቀመር) = 76 ዓመት

+ ዓውደ ዐቢይ ቀመር (ዐቢይ ቀመር) = 562

(ወንበር 10)

· የዘመኑን አበቅቴንና መጥቅዕ የሚያስገኝ ነው።

· ወንበር ለማግኘት ቀድመን ዓመተ ዓለሙን ማውጣት

5500 ዓመተ ፍዳ፣ ዓመተ ኩነኔ
የሰው ልጅ ከገነት ወጥቶ ከፈጣሪው ጋር ተጣልቶ በመከራ በጭንቅ ይኖር ነበረና

2016 ዓመተ ምህረት ዓመተ ሥጋዌ
(ለምን ዓመተ ምህረት ተባለ?)
አዳም የበደለውን በደል ለመካስ በምህረት በይቅርታ ስላዳነው የምህረት ዘመን ስለሆነ ዓመተ ምህረት ተብሏል

በድምሩ 7516

ይህንና በሶስቱ ቀመሮች እንቀምረዋለን።

· ዐቢይ ቀመር ፣ 532

· ማዕከላዊ ቀመር ፣76

· ንዑስ ቀመር፣ 19

1ኛ. ለዐቢይ ቀመር

7516 ÷ 532

14ቱ ዐቢይ ቀመር 7448 ሆኖ 68 ይቀራል

2ኛ. ለማዕከላዊ ቀመር

68 ማዕከላዊ ቀመር (76) አይችልም

3ኛ. ለንዑስ ቀመር



አዋጅ “አሐደ አዕትት ለዘመን - አንድ ለዘመኑ ስጥ”

የ 20016 ዓ.ም. ወንበር 10

አበቅቴ 20

· ተረፈ ዘመን

· ቁጥረ ሌሊት

· ሥፍረ ሌሊት ማለት ነው።

አበቅቴን ለማግኘት፦

ጥንተ አበቅቴ ከወንበር ጋር ማባዛት

ከ30 ከበለጠ - በ30 መግደፍ

አበቅቴ = 20 × 10=30

+ አበቅቴ የሚጠቅመን ሌሊቱን ለማግኘት ነው።

· ሌሊት = ዕለት + አበቅቴ + ሕፀጽ

ሕፀጽ - ጉድለት ማለት ነው።

ጨረቃ ከፀሐይ የምታጐድለው ማለት ነው።

የዓመቱ ሕፀጽ፦

· የመስከረምና የጥቅምት = 1

· የሕዳርና የታህሣሥ= 1 ከላይኛው ጋር = 2

· የጥርና የየካቲት = 3

· የመጋቢትና የሚያዚያ =4

· የግንቦትና የሰኔ = 5

· የሐምሌና የነሐሴ = 6

· ጳጉሜ ወር ስለማትሞላ 6 ነው።

· የመስከረም 1/2016 ዓ. ም ሌሊት፦

ዕለት + አበቅቴ + ሕፀጽ

1 + 10+ 1 = 12

መጥቅዕ

· ደወል ማለት ነው

ደወል ሲመታ የራቁ ይቀርባሉ፣ የተበተኑ ይሰበሰባሉ። ይህም መጥቅዕ በዓላትና አጽዋማትን ይሰበስባል።

የዘመኑን መጥቅዕ ለማግኘት ጥንተ መጥቅዕን ከወንበር ጋር ማባዛት

· ከ 30 ከበለጠ ለ 30 ማካፈል ነው

19 × 10= 190 ÷30=6=ቀሪ 10
አበቅቴ 20
መጥቅዕ 10 ነው።

መባጃ ሐመር

· ባጀ - ቆየ ፣ ሰነበተ

· ሐመር - መርከብ

በዓላትና አጽዋማት የሚያሰነብት ስለሆነ መባጃ ሐመር ተብሏል።

መባጃ ሐመርን ለማግኘት፦

· መጥቅዕና በዓለ መጥቅዕ የዋለበትን የዕለት ተውሳክ መደመር ነው።

ከ 30 ከበለጠ በ 30 መግደፍ

በዓለ መጥቅዕ መቼ ይውላል?

አዋጅ ፦ መጥቅዕ ከ14 በላይ ከሆነ በመስከረም

ከ 14 በታች ከሆነ በጥቅምት

(መጥቅዕ ሲበዛ ከመስከረም ንዛ መጥቅዕ ቢያንስ ከጥቅምትን ዳስ) ይላል መርሐ ዕውር

መጥቅዕ 10 ነው ስለዚህ መጥቅዕ በጥቅምት ይውላል

በዓለ መጥቅዕ በጥቅምት (በጥቅምት 10) ቀን ይውላል።

የዕለት ተውሳክ፦

· ተውሳክ - ወሰከ - ጨመረ

- ጭማሪ ማለት ነው።

· የቅዳሜ ተውሳክ = 8

· የእሑድ = 7

· የሰኞ = 6

· የማክሰኞ = 5

· የረቡዕ = 4

· ሐሙስ = 3

· ዓርብ = 2

ጥቅምት 10/2016 ዓ. ም. ቅዳሜ ይውላል (8ተውሳክ)

መባጃ ሐመር = መጥቅዕ + የዕለት ተውሳክ

10+ 8= 18

መባጃ ሐመር 18

ከበዓላትና አጽዋማት ተውሳክ ጋር በመደመር የየዘመኑንን በዓላትንና አጽዋማት ያስገኝልናል።

የበዓላትና አጽዋማት ተውሳክ የሚውልበት

1ኛ. ጾመ ነነዌ ተውሳክ የላትም (0 ነው)

ስለዚህ መባጃ ሐመር ትወጣለች

አዋጅ ፦ በዓለ መጥቅዕ በመስከረም ከዋለ ጾመ ነነዌ በጥር ትገባለች፣

በዓለ መጥቅዕ በጥቅምት ከዋለ ጾመ ነነዌ በየካቲትገባለች

በዓለ መጥቅዕ በመስከረም 30 ከዋለ በጥቅምት ትገባለች

ዘንድሮ በዓለ መጥቅ 10 ስለሆነ በጥቅምት 10 ይውላል
ጥቅምት 10 ቅዳሜ ቀን ይሆናል የቅዳሜ ተውሳክ 8
መጥቅዕ ሲደመር የዕለት ተውሳክ እኩል ይሆናል መባጃ ሐመር በዓለ መጥቅዕ በጥቅምት ስለዋለ ጾመ ነነዌ በየካቲት ትገባለች።

የአጽዋማትና የበዓላት ተውሳክ
1ኛ ለጾመ ነነዌ ተውሳክ የላትም በመባጃ ሐመር ትወጣለች
2ኛ. የዐቢይ ጾም ተውሳክ = 14

3ኛ. የበዓለ ደብረ ዘይት = 11

4ኛ. የበዓለ ሆሳዕና = 2

5ኛ. የበዓለ ስቅለት = 7

6ኛ. የበዓለ ትንሣኤ = 9

7ኛ. የበዓለ ርክበ ካህናት = 3

8ኛ. የበዓለ ዕርገት = 18

9ኛ. የበዓለ ጰራቅሉጦስ = 28

10ኛ. ጾመ ሐዋርያት = 29

11ኛ. ጾመ ድኅነት = 1



በዓላትና አጽዋማት

1. ጾመ ነነዌ መባጃ ሐመር ተውሳክ የላትም ብለናል

10+8= 18
ጾመ ነነዌ የካቲት 18

2. በዐተ ዐቢይ ጾም 18+ 14 = 32÷30=2

ዐቢይ ጾም መጋቢት = 2

3. ደብረ ዘይት 18 +11 = 29
በዓለ ደብረ ዘይት መጋቢት 29

4. በዓለ ሆሳዕና 18+ 2 = 20

በዓለ ሆሣዕና ሚያዚያ 20 (እሁድ)

5. በዓለ ስቅለት 18+ 7 = 25

በዓለ ስቅለት ሚያዚያ 25 ( አርብ)

6. በዓለ ትንሣኤ 18+ 9 = 27

በዓለ ትንሣኤ ሚያዚያ 27 (እሁድ)

7. በዓለ ርክበ ካህናት 18 + 3 = 21

ርክበ ካህናት ግንቦት 21

8. በዓለ ዕርገት 18+ 18 = 36÷30=6

በዓለ ዕርገት ሰኔ 6 (ሐሙስ)

9. በዓለ ጰራቅሊጦስ 18 + 28 = 46÷30=16

በዓለ በራቅሊጦስ ሰኔ 16 (እሁድ)

10. ጾመ ሐዋርያት 18 + 29 = 47÷30=17

ጾመ ሐዋርያት ሰኔ 17 (ሰኞ)

11. ጾመ ድኅነት 18 + 1 = 19

ጾመ ድኅነት ሰኔ 19 (ረቡዕ)
የ2016 አጽዋማትና በዓላት በዚህ መልኩ ይቀመራል

ኢየዓርግና አይወርድ

ጾመ ነነዌ ከጥር 17 አትወርድም ከየካቲት 21 አትወጣም
ዓቢይ ጾም ከየካቲት 1 ወደ ታች አይወሬድም ከመጋቢት 5 ወደ ላይ አይወጣም
ደብረዘይት ከየካቲት 28 ወደ ታች አይወርድም
ከሚያዝያ 2 ወደ ላይ አይወጣም
ሆሣዕና ከመጋቢት 19 ወደ ታች አይወርድም
ከሚያዝያ 23 ወደ ላይ አይወጣም
በዓለ ስቅለት ከመጋቢት 24 ወደ ታች አይወርድም
ከሚያዝያ 28 ወደ ላይ አይወጣም
በዓለ ትንሣኤ ከመጋቢት 26 ወደ ታች አይወርድም
ከሚያዝያ 30 ወደ ላይ አይወጣም
ርክበ ካህናት ከሚያዝያ 20 ወደ ታች አይወርድም
ከግንቦት 24 ወደ ላይ አይወጣም
በዓለ ዕርገት ከግንቦት 5 ወደ ታች አይወርድም
ከሰኔ 9 ወደ ላይ አይወጣም
በዓለ ጰራቅሊጦስ ከግንቦት 15 በታች አይወርድም
ከሰኔ 19 በላይ አይወጣም
ጾመ ሐዋርያት ከግንቦት 16 በታች አይወርድም
ከሰኔ 20 በላይ አይወጣም
ጾመ ድኅነት ከግንቦት 18 በታች አይወርድም
ከሰኔ 22 በላይ አይወጣም



ዓመተ ወንጌላውያኑን ለማግኘት

ዓመተ ፍዳ + ዓመተ ምህረት

5500 + 2016= 7516 = ዓመተ ዓለም

ዓመተ ዓለሙን ለ 4ቱ ወንጌላውያን በማካፈል

· ቀሪው 1 ከሆነ ማቴዎስ

· 2 ከሆነ ማርቆስ

· 3 ከሆነ ሉቃስ
ዜሮ ወይም እኩል ከሆነ ዮሐንስ

7516 ÷ 4 = 1879 ደርሶ ዜሮ ይቀራል
ወይም 1878 ደርሶ 4 ይቀራል
አራት ቀረ ወይም ዜሮ ከሆነ ዮሐንስ ይሆናል ስላልን

ወንጌላዊው ዮሐንስ

2. መስከረም 1 ( ዕለተ ቀመር)

ዓመተ ዓለም + መጠነ ራብዒት = ለሰባቱ ዕለታት ማካፈል

7516+ 1879 = 9395

9395 ÷ 7= 1342 ደርሶ 1 ይቀራል። ቀሪ፦

· 1 ከሆነ = ማክሰኞ

· 2 ከሆነ = ረቡዕ

· 3 ከሆነ = ሐሙስ

· 4 ከሆነ= ዓርብ

· 5 ከሆነ = ቅዳሜ

· 6 ከሆነ = እሁድ

· 0 ከሆነ = ሰኞ
በ2016 ዕለተ ዮሐንስ ማክሰኞ ቀን ስለ መዋሉ በዚህ ይረጋገጣል

3 . ዕለቱን ለማግኘት

ዕለት + አጽፈ ወርኅ + ጥንተ ዮን

መስከረም 30 + የመስከረም እጥፍ + ጥንተ ዮን

ጥንተ ዮን መስከረም 1 ረቡዕ ከዋለ = ጥንተ ዮን አንድ ነው።

· ሐሙስ ከዋለ = 2

· ዓርብ ከዋለ = 3

· ቅዳሜ ከዋለ = 4

· እሑድ ከዋለ = 6

· ሰኞ ከዋለ = 7
ማክሰኞ ከዋለ = 8

·(((( መስከረም 1 ቀን ማክሰኞ ስለዋለ ጥንተ ዮን 8 ነው።))))

ዕለት + አጽፈ ወርኅ + ጥንተ ዮን

30 + 2 + 1 = 33

33ን ለሰባት ማካፈልና ቀሪው

· 1 ከሆነ እሁድ

· 2 ከሆነ ሰኞ

· 3 ከሆነ ማክሰኞ

· 4ከሆነ ረቡዕ

· 5 ከሆነ ሐሙስ

· 6 ከሆነ ዓርብ

· 0 ከሆነ ቅዳሜ

የ2016
አጽዋማትና በዓላት በዚህ መልኩ አጠናቀናል

ዓመቱን የሰላም የፍቅር የአንድነት ዓመት ያድርግልን

ጸልዩ በእንተ ሠላም
ስለ ሰላም እንጸልይ
ስለ ሀገራችን እንጸልይ
በጭንቅ በመከራ ስላሉት እንጸልይ
በረሀብ በስደት ስላሉት እንጸልይ
ስለ ቤተ ክርስቲያን እንጸልይ
የሰላም አምላክ ሰላሙን ሁሉ ያድለን
ዘመኑን ዘመነ ሠላም ዘመነ ፍቅር ያድርግልን

አባ አትናቴዎስ ወልደ ጎርጎርዮስ
ዘዝዋይ ገዳም
29/12/2015
ሼር ላይክ ፎሎው በማድረግ ቤተሰብ ይሁኑ

በኮሮና ቫይረስ ተለዋዋጭ ባህሪ ምክንያት ከሚመጣ የጤና ችግር ራስዎንና ቤተሰብዎን ለመጠበቅ  !
21/06/2022

በኮሮና ቫይረስ ተለዋዋጭ ባህሪ ምክንያት ከሚመጣ የጤና ችግር ራስዎንና ቤተሰብዎን ለመጠበቅ !

የጤና ሚኒስቴር በሀገር አቀፍ ደረጃ የጤና ባለሙያዎች ሙያ ለማሻሻል እና ተደራሽ ለማድረግ የተከታታይ ሙያ ማጎልበቻ ስርዓትን  ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡ ከነዚህም ውስጥ የስልጠናዎችን ደረ...
13/08/2021

የጤና ሚኒስቴር በሀገር አቀፍ ደረጃ የጤና ባለሙያዎች ሙያ ለማሻሻል እና ተደራሽ ለማድረግ የተከታታይ ሙያ ማጎልበቻ ስርዓትን ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡ ከነዚህም ውስጥ የስልጠናዎችን ደረጃ ለማስጠበቅ 82 ስልጠና የሚሰጡ እና 32 እውቅና ሰጪ ተቋማት ዝርዝር ተለይተዋል፡፡
ስለዚህ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ስልጠናዎችን ሲሰጡ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት እውቅና ያገኙ የተከታታይ ሙያ ማጎልበቻ ማዕከላት እንዲጠቀሙ እናሳስበለን፡፡
The Ministry of Health is working hard to improve health professionals continuing professional development (CPD) in Ethiopia. To this end, 82 CPD providers and 32 CPD Accreditors from different institutions are accredited. So all stakeholders that are providing in-service training are required to use accredited CPD providers.

26/04/2021

የሃዘን መግለጫ
_______________
በጤና ሚኒስቴር በእናቶችና ህፃናት ጤና ዳይሬክቶሬት ለማሕበረሰባቸው አገልግሎት በመስጠት የቆዩት ወ/ሮ ነፃነት ብርሃኑ በኮቪድ-19 ተይዘው ተገቢው የሕክምና እርዳታ እየተደረገላቸው እያሉ ሕይወታቸው አልፏል፡፡

በወ/ሮ ነጻነት ብርሃኑ ህልፈተ ህይወት የጤና ሚኒስቴር አመራሮችና ሰራተኞች የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን እየገለጹ ለቤተሰቦቻቸው እና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ልባዊ መጽናናትን እንመኛለን!

የጤና ሚኒስቴር
______

ለጤና ባለሙያዎች በአዲስ መልክ የበለጸገውን እና በሞባይል መተግበሪያ የሚሰጠውን የኮቪድ-19 ክትባት ስልጠና ከዚህ በታች የሚገኘውን ሊንክ በመጫን ይውሰዱ !ሰርተፍኬት ያግኙ !የኮቪድ-19 ክ...
16/04/2021

ለጤና ባለሙያዎች በአዲስ መልክ የበለጸገውን እና በሞባይል መተግበሪያ የሚሰጠውን የኮቪድ-19 ክትባት ስልጠና ከዚህ በታች የሚገኘውን ሊንክ በመጫን ይውሰዱ !
ሰርተፍኬት ያግኙ !

የኮቪድ-19 ክትባት ስልጠና ይውሰዱ፣ የተሻለ የጤና እንክብካቤ ይስጡ!

http://bit.ly/3apv5J2

የጤና ሚኒስቴር ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለመስጠት ባለሙያዎች ለሚሰጡት የጤና አገልግሎት አጋዥ የሆኑ ሰነዶችን በማዘጋጀት ለሁሉም ጤና ባለሙያዎች ተደራሽ እንዲሆን እያደረገ ይገኛል፡፡ በ...
28/01/2021

የጤና ሚኒስቴር ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለመስጠት ባለሙያዎች ለሚሰጡት የጤና አገልግሎት አጋዥ የሆኑ ሰነዶችን በማዘጋጀት ለሁሉም ጤና ባለሙያዎች ተደራሽ እንዲሆን እያደረገ ይገኛል፡፡

በዚህም መሰረት እ.ኤ.አ በ2014 የተዘጋጀውን Standard Treatment Guideline በማሻሻል ክለሳ ያከናወነ ሲሆን የተዘጋጀው ሰነድ በባለሙያዎች ተቀባይነት ያለውና የሚያሰራ እንዲሆን ለማድረግ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ ያላችሁ የጤና ባለሙያዎች፣የሙያ ማህበራት፣የትምህርትና ምርምር ማዕከላት፣የጤና ተቋማትና ሌሎችም፤ በተዘጋጀው ሰነድ ላይ መሻሻል ይገባቸዋል የምትሏቸውን ጉዳዮች በኢሜል አድራሻ [email protected] በኩል እንድትሰጡበት እየጠየቅን ሰነዱን ከዚህ ከታች በተጠቀሰው አገናኝ (link) ላይ ገብታችሁ ማግኘት የምትችሉ መሆኑን ይገልጻል፡፡
http://www.moh.gov.et/ejcc/am/STG
የጤና ሚኒስቴር

ተከታታይ የጤና ማጎልበቻ ፕሮግራም እንደ ኮቪድ-19 ያሉ አዳዲስ በሽታዎችን ለመከላከል፣ ለማከምና ለመቆጣጠር ያለዉ ሚና እጅግ የጎላ ነው፡፡
06/10/2020

ተከታታይ የጤና ማጎልበቻ ፕሮግራም እንደ ኮቪድ-19 ያሉ አዳዲስ በሽታዎችን ለመከላከል፣ ለማከምና ለመቆጣጠር ያለዉ ሚና እጅግ የጎላ ነው፡፡

13/04/2020

ባለፉት 24 ሰዓታት የላቦራቶሪ ምርመራ ከተደረገላቸው 247 ግለሰቦች መካከል፤ ሶስቱ የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው ተረጋግጧል።
__________

ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ከተረጋገጠባቸው ግለሰቦች መካከል ተጨማሪ አራት ሰዎች ከበሽታው አገግመዋል።

ቫይረሱ የተገኘባቸው ሶስቱም ግለሰቦች ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ የላቸውም።ሶስቱም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ናቸው።

ከግለሰቦቹ መካከል ሁለቱ ወንዶች ሲሆኑ፤ሁለቱም ከበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ እንዳላቸው ገና አልተረጋገጠም።

አንዷ የ23 ዓመት እድሜ ያላት ስትሆን ከበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ እንዳላት ተረጋግጧል።

ይህን ተከትሎም በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 74 ደርሷል።

ቫይረሱ እንዳለባቸው ከተረገጠባቸው ግለሰቦች መካካል ተጨማሪ አራት ግለሰቦች ከበሽታው ያገገሙ ሲሆን፤ይህን ተከትሎም በአጠቃለይ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር ወደ 14 ከፍ ብሏል።

በኢትዮጵያ እስካሁን ለ4 ሺህ 110 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎላቸዋል።

04/04/2020

የሕክምና ጓንት በሚጠቀሙበት ወቅት ሊቀደው የሚችል እንደ ጥፍር ፤ቀለበት ያሉትን ያስወግዱ!

#ኮሮናቫይረስ #ኮቪድ19
8335 or 952 ራስዎን ከኮሮና ቫይረስ ለመከላከል ይህንን መልእክት በመተግበር ጥንቃቄ ያድርጉ! ለሌሎችም ያጋሩ!

31/03/2020

Address

Addis Ababa
1234

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Motivated, Competent and Compassionate /MCC/ Health Workforce / Ethiopia posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The Organization

Send a message to Motivated, Competent and Compassionate /MCC/ Health Workforce / Ethiopia:

Share