23/08/2026
የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የማለፊያ ነጥብ ያመጡ ተማሪዎች ቁጥር መሻሻል አሳይቷል - ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 16/2018 (ኢዜአ)፦ የ2018 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የማለፊያ ነጥብ ያመጡ ተማሪዎች ቁጥር መሻሻል ማሳየቱን የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።
የትምህርት ሚኒስቴር በ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎችን ውጤት አስመልክቶ ይፋዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንደገለጹት፣ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ለፈተና ከተመዘገቡት 563 ሺህ 960 ተማሪዎች መካከል 550 ሺህ 210 የሚሆኑት ፈተናውን ወስደዋል።
ከእነዚህም ውስጥ 70 ሺህ 544 ወይም 12.8 በመቶ የሚሆኑት ከ50 በመቶ በላይ በማምጣት ማለፍ ችለዋል።
በ2017 ዓ.ም ያለፉ ተማሪዎች ምጣኔ 8 ነጥብ 9 በመቶ ነበር።
እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፣ የማለፊያ ምጣኔው በትምህርት ዘርፎች ሲታይ በተፈጥሮ ሳይንስ 16.6 በመቶ፣ በማህበራዊ ሳይንስ ደግሞ 8.33 በመቶ ተማሪዎች ማለፊያ ነጥብ አምጥተዋል።
በከፍተኛ ውጤት ደረጃ በተፈጥሮ ሳይንስ በወንዶች በኦሮሚያ ክልል የአዳማ ኦዳ ስፔሻል ቦርዲንግ ትምህርት ቤት ተማሪ 591.6 ነጥብ በማምጣት ከፍተኛውን ውጤት ሲያስመዘግብ፣ በሴቶች ደግሞ ከአማራ ክልል እንጅባራ አገው ምድር ትምህርት ቤት ተማሪ 583 ነጥብ በማምጣት ከፍተኛውን ውጤት ይዛለች።
በማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ በወንዶች ከፍተኛው ውጤት 576 እንዲሁም በሴቶች 569 ሆኖ ተመዝግቧል።
88 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ተማሪዎቻቸውን ማሳለፍ ሲችሉ፣ በአንጻሩ 565 ትምህርት ቤቶች ደግሞ አንድም ተማሪ ማሳለፍ ሳይችሉ ቀርተዋል።
ሚኒስትሩ አክለው እንደገለጹት፣ ዘንድሮ ከባለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ቁጥር ያለው ተማሪ የማለፊያ ነጥብ በማስመዝገቡ ምክንያት ወደ ማካካሻ (Remedial) ፕሮግራም የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር ይቀንሳል።
ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ እና የማካካሻ ፕሮግራም ትክክለኛ የመቁረጫ ነጥብ በቀጣይ ይፋ እንደሚደረግ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።