03/08/2026
ኢትዮጵያ በዓለም ፊት የመሪነት ሚናዋን ለማሳየት የምትችልበት እድል ላይ ትገኛለች
ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም (የገቢዎች ሚኒስቴር)
ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚደርሱ ተፈጥሮአዊ አደጋዎችን ለመከላከል፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት "የአረንጓዴ አሻራ" ኢኒሼቲቭን ይፋ ማድረጓ ይታወቃል። ላለፉት ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ እና በአካባቢ ጥበቃ ላደረገችው ተከታታይ ጥረት ከዓለም መንግሥታት ትልቅ እውቅና በማግኘት፣ ታላቁን እና 32ኛውን የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ የ"ኮፕ" (COP) 2027 ን ጉባዔ እንድታዘጋጅ ተመርጣለች።
ዘንድሮም "ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ቃል በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል መርሃ-ግብር በሚካሄድበት ወቅት በልዩ ሁኔታ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን ለማዘጋጀት መመረጧን ተከትሎ የአገሪቱን የአረንጓዴ ዐሻራ ተነሳሽነት፣ የከተማ አረንጓዴ ልማት እና የአካባቢ ጥበቃ ተግባራት ለዓለም ለማሳየት በሚያስችል መልኩ ከICT ፓርክ እስከ ቢሾፍቱ ደቡብ መውጫ ባለው 45 ኪሎ ሜትር የመንገድ ኮሪደር ውስጥ የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ ዓይናለም ንጉሴ እና ሚንስትር ዴኤታዎች፣ የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ (ደ/ር)፣ የጉምሩክ ምክትል ኮሚሽነሮች እና ሌሎችም የተቋማቱ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ሁሉም የሚኒስቴር መስሪያቤቶች አሻራቸውን አሳርፈዋል።
በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ ገርጂ ማርያም በሚባል ቦታ የሁለቱም ተቋማት አመራሮች እና ሰራተኞች ችግኞችን ተክለዋል።
በየጊዜው ሁለቱ ተቋማት የሚተክሏቸውን ችግኞች የመንከባከብ ስራም ተንከባካቢ ሰራተኞችን ጭምር በመቅጠር እያከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በአዳነ ውበት
ፎቶ:- የትናየት እንዳያፍሩ