10/05/2020
ጉርብትና
።።።።።።።
እሽ ሥንታየሁ እንዴት ዋልክ ቡና ትጠጣለህ? አለችኝ...
አይ አልጠጣም አልኩ። እሷም ይሄን እንድል እና እንዲህ ብላ ከጠየቀችኝም እንዲህ እንደምል ስለምታውቅ ነው ና ቡና ጠጣ ከማለት ይልቅ ትጠጣለህ? ብላ የጠየቀችኝ። ምቀኛ።
እኔ ምለው ምን አረኳት ቆይ ...ባለፈው ለኮሮና በሽታ መድሃኒት ፈውስ ይሆን ዘንድ ዝንጅብል ፌጦ ማር እና ነጭ ሽንኩርት ቀላቅላችሁ ተጠቀሙ ተብሎ ከገዳም አባቶች ታዟል የተባለ ግዜ ምድረ ተከራይን እያንኳኳች በለሊት ቀስቅሳ መዳኒት ተብዬውን በማንኪያ ስታስልስ እኔ መብራት አብርቼ ሳልተኛ ቤት ውስጥ እያለሁ እያወቀች ሳታንኳኳ አለፈችኝ...የተባለውን መድሃኒት በእጦት ምክንያት ሳልወስድ ሞቼ ቢሆን ለሞቴ የተባበረችን እሷ ነበረች። ኪራይ ቀጥታች አላውቅ ለምን እንደደበርኳት እንጃ።
ዛሬ ደግሞ ሁሉንም ኑ ቡና ጠጡ እያለች ደጇ ደግሳ ጠርታ ስታበቃ ለኔ ሲሆን ቡና ትጠጣለህ እንዴ? ማለት ምን ማለት ነው ጎበዝ?
።..
ይቺን ንዴቴን ቤቴ ውስጥ ሆኜ እያብሰለሰልኩ ሳለ ድንገት ጮክ ብለው ደጅ ላይ የተጠሩት ሁሉ በአንድ ላይ ሲስቁ ከማብሰልሰሌ ባነንኩ...እነዚህ ሰዎች በአንድ ላይ ለምን ሳቁ? እኔን ለማናደድ ተልዕኮ አላቸውን? ይሄን ያህል በአንዴ የሚያስቅ ኮሜዲያን እዚህ ግቢ ውስጥስ አለን? ይሄን ያህል በአንዴ የሚያስቅስ ጉዳይ በተለይም በዚህ ሰአት በሃገራችንስ ከየት ተገኘ? የሰው ልጅ እንዲህ በአንዴ ተግባብቶ ይስቅ ዘንድ ሳይንሱስ አግባብ ነው ይላልን? በጣም መሳቅስ ኮሮናን አያስተላልፍም ወይ? እያልኩ በንዴት ጥያቄ አሽጎደጉድ ጀመር።
በድንገት ደሞ እናቴ ትዝ አለችኝ....አቤት የኛ ቤት ንፍሮ እኮ ብይ ብይ ነው እኮ የሚያክለው አልኩ እነሱ ሃሳቤን እየሰሙ ይናደዱልኝ ይመስል። እንደናንተ በመርፌ ቀዳዳ የሚሾልክ የላመ ንፍሮ መሰላችሁ እንዴ የኛ ቤት አልኩ በውስጤ...ደግሞ ንፍሮ ብቻ አይደለም እኛ ቤት አልኩ...በጉ ፣ ጠላው ፣ አረቄው ፣ ድፎው ፣ ብርዙ ምንትሱ አልኩኝ በሃሳቤ በቤቴ ውስጥ ለብቻዬ ቁጭ ብዬ። እነዚህ የሆነች ብናኝ ንፍሮ እና ቡና ነው ያዙ ያዙ ሲባባሉ ያየሁትም የሰማሁት።
ለነገሩ በግ አለያም ዶሮ ባያርዱም ከሚያመሰኩት ኩጫጭ ንፍሮ ጋር አብረው የለቀቀች የዱሮ ተከራይ ሴት እያሙ ስለነበር ያው ድግሱን የፍስግ አድርገውታል። እሷ ደሞ መንቃራ አይደለች እንዴ እያሉ ያሽካካሉ። ቤተክርስቲያን የሚባል ነገር አትወድም እኮ አንች ትላለች ሌላኛዋ ደግሞ....(በሷ ቤት አሁን የሷን ሃሜት እግዚአብሔር የሚወደው ነው የመሰላት) ..ደሞ የምታመጣቸው ወንዶችስ ብዛት ብትይ ብላ ሌላዋ ደሞ ከት ብላ ሳቀች...እሱንማ ተይው ድፍረቷ መቼም አይን አውጣ ነበረች ፡ እኔ ስንት ሰው አከራይቻለሁ እንደ እሷ ጋጠ ወጥ ገጥሞኝ አያውቅም አለች አከራይዋ።
እየውልሽ አንዴ አምሽታ ጥግብ ብላ ሰክራልሽ ከአንዱ ወንድ ጋር እየተወለጋገደች መጣችና በሩን ለሁለት ይቀጠቅጣሉ...አንች ከለሊቱ 6፡30 ሆኗል እኮ እንዴት እንደደነገጥኩ...በዛ ላይ ኧረ መጣሁ ብዬ ተነስቼ እስክከፍት ድረስ ፋታ ሊሰጡኝ መሰለሽ ለሁለት በሩን ሊሰብሩት በቃ.. ምድረ ተከራይ አልቀረ ጎረቤት አልቀረ የምን ጉድ ነው ብለው በየቤቱ ወጥተው ብታይ (ይች ሴትዮ ስታወራ ግነቷ አይጣል) ኧረ ማን ነው ቀስ ብዬ በሩን ክፍት ሳደርግ ተቃቅፈው በር ላይ ቆመዋል...ንድድ ብሎኝ አንች ያምሻል እንዴ ግን ጤነኛ አይደለሽም? በለሊት ሰው ከተኛ በኋላ መምጣትሽ ሳያንስ ደግሞ በስነስርአት አታንኳኩም እንዴ እላታለሁ ፡ ያ ሰካራም ለፍዳዳ ወንዷ ውልግድግድ ባለ አንደበቱ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው?....ም....ምን ታ...ታመጫለሽ ቆይ....ክ....ክፈቺ ተ...ባልሽ አይደል....ዝም ...ብለሽ መክፈት ነው....አሁን...ዞር በይ አትጩሂብን....ቤተ-መን...ግስት ያከራየሻት መ...መሰለሽ እንዴ? አይለኝም። ከዛ ተከራዮቹ በሙሉ ይሄን ሁሉ ነገር በለሊት ተነስተው አይተው ስለነበር ..ልብ አርጉልኝ ይሄን ሁሉ ብልግና ብዬ ምስክር አድርጌ ነገውኑ ቤት ፈልገሽ እንድትወጭ ማነሽ ስላት....ያ ሰካራም ሰውዬ በድጋሜ ተለፋደደብኝ.....
ስሚ ሃ...ሃበሻ እኮ ማለት....ግር ብሎ በተ..ጠራበት የሚገኝ ከ...ከንቱ መንጋ ነው...እነዚህም ምስኪን....የማይዝናኑ ተከራዮችሽ ግርርር ብለው ቢ..መ...ሰክሩልሽ አይገርምም....ግን ነገ አይደለም እስከወዲያኛው ትወጣልሻለች...ለዚህ ትኋናም የወፍ ጎጆሽ....ደና ቤት እንዳ..ላት ውጭልኝ ትላለች እንዴ ማፈሪያ ብሎ አላቀለለኝም መሰለሽ እያለች ውርደቷን ለምድረ ተከራይ ታወራለች።
እኔ ይሄን ሁሉ ዲስኩር ቤቴ ውስጥ ሆኜ እየሰማሁ ፈገግ እላለሁ።
ይሄን ሁሉ ሃሜት ስሰማ ቡና ትጠጣለህ እንዴ ሥንታየሁ? ስትለኝ አይ አልጠጣም ማለቴን ወደድኩት።
ለመሆኑ የኛ ሃገር ህዝብ መች ነው ሃይማኖታዊ በዓልን አውዱን ጠብቀን አክብረን የምናሳልፈው። ልብ በሉ እስቲ ለገና በዓል ቀን በሬዲዮ እና በቴሌቭዥን ካልደሰኮሩልን በቀር በስህተት ስለጌታችን ልደት ሃሳብ ተነስቶ ለ5 ደቂቃ እንኳ አይወራም በቃ ተሰብስቦ መብላት መጠጣት ከርስ መሙላት ብቻ ነው። ለፋሲካ ዕለትም እንዲሁ ኧረ እዚጋ ዱለት አንሷል አንቺ..
ምንድን ነው ቁርጥ ጨምሩላቸው እንጂ ለልጆቹ....ጠላውስ የት ሄደ ስንል እንጅ የምንውለው የጌታን ትንሳኤ ማን ልብ ብሎት።
ዛሬም የወላዲተ አምላክ የቅድስት ብፅዕት ድንግል ማርያም ልደቷ ሳለ...ቢያንስ ለምን ተሰብስበን ደጅ ላይ ንፍሮ ቀቅለን እንደምናከብር እንኳን ሃሳብ አንስቶ እንወያይ ያለ የለም ...እ ቡና ደረሳችሁ? እህ ዝገኝ እንጂ ከንፍሮው ሲባባሉ ብቻ ነው የሰማሁት። በዓላቶቻችን በሙሉ የከርስ መሙያ ...መስከሪያ እና መለፋደጃ ሆነዋል። በተለይም ኃይማኖታዊ በዓላትን ስናከብር በቅጡ መብላት መጠጣቱ እንዳለ ሆኖ ስለ በዓሉ ምንነትና ምክንያት እውቀት እና ሃሳብ እየተወያየን ቢሆን ትውፊቱን በቀጣይ ትውልድ ውስጥም ጠብቆ ለማዝለቅ ያግዛል ባይ ነኝ።
አይ ዘንድሮ አምና እኮ ብታይ በሬ የሚያህል ሙክት አርደን ደጅ ላይ ሰፈራችንን ቀውጢ አርገነው ነበር እድሜ ለኮሮና ዘንድሮ በየግቢያችን ለየብቻ ሰበሰበን....ብላ አከራይዋ ያቆመችውን ወሬ ስትቀጥል...በሉ ደህና እደሩ እኔ ልሂድ እግዜር ይስጥልኝ ብላ አንዷ ተከራይ ወደ ቤቷ ገባች። ከመቅጽበት ቤት ከመግባቷ አከታትላ ታስነጥስ ጀመር...እህህህ ብላ ጉሮሮዋንም ትጠራርግ ጀመር...አሃ ወዳ አይደለም ለካ ቶሎ ብላ ወሬ አቋርጣ ደና እደሩ ብላ የወጣችሁ አልኩ በውስጤ....
ይሄኔ ታድያ አከራይዋ ማነሽ አመለ....አመለ ብላ ተጣራች....
አቤት እትዬ ጸጋ....
ምነው ሰላም አይደለም?
እየሰማሽኝ አይደል እንዴ እያጣደፈኝ ምን ትጠይቂኛለሽ...
ዋ አመለ ከማንም ጋር ስራ ቦታ ስትጋፊ እየዋልሽ ብቻ.....አሃሃሃሃ ብላ ሳቀች።
ከዛ በኋላ የደጁ ጨዋታ ቀዘቀዘ...ይሄ ቅዝቃዜውም ምኑም ዝናቡም ሳል ያመጣል እኮ እየተባባሉ እነሱም በየቤታቸው ገብተው ዘና ብለው ሊስሉና ሊያስነጥሱ ነው መሰል የተጠራው ሰው ሁሉ ወደየቤቱ ክትት አለ.....እድሜ ለኮሮና ስንት ሃሜትና ጨዋታ ቀዘቀዘ።