20/08/2026
በአገራት መካከል የሚፈፀሙ ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች
******************
መግቢያ
አገራት ከሌሎች አገሮች ጋር የሚኖራቸውን የተለያዩ ግንኙነቶች ለማስተዳደር የሁለትዮሽ ስምምነቶች (Bilateral Agreements) ወይም በብዙ አገራት መካከል የሚደረጉ ስምምነቶች (Multilateral Agreements) ሊያደርጉ ይችላሉ። እነዚህ ስምምነቶች በሰላም፣ በንግድ፣ በሰብዓዊ መብቶች፣ በአካባቢ ጥበቃ እንዲሁም ሌሎች ዘርፈ-ብዙ ጉዳዮች ላይ ሊያተኩሩ ይችላሉ። በተጨማሪም አገራት በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መስኮች የሚያደርጓቸውን ግንኙነቶች በዓለም ዓቀፍ ሕግ በመምራት የጋራ ጥቅምና ፍላጎቶቻቸውን ይጠብቃሉ። ለዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች መሠረት የሆነው እ.ኤ.አ በ1969 ዓ.ም በቪየና በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ኮንፈረንስ የወጣው የቪየና የስምምነቶች ሕግ (Vienna Convention on the Law of Treaties) ሲሆን ይህ ሕግ የዓለም ዓቀፍ ስምምነቶችን ትርጓሜ፣ የሚቋቋሙበትን ሁኔታ፣ ሥነ-ሥርዓት እንዲም የተፈፃሚነት ውጤት በሚመለከት በርካታ ድንጋጌዎችን አካቷል። በዚህ ጽሑፍ የዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች ምንነት፣ የዓለም ዓቀፍ ስምምነት ዓይነቶች፣ የስምምነቶች አተረጓጎም (Interpretation of Treaties) ፣ የስምምነቶች ዋጋ ማጣት (መሰረዝ)፣ መቅረት፣ መቋረጥ እና አለም አቀፍ ስምምነትን የብሔራዊ ሕግ አካል የማድረግ ሥርዓትን የሚመለከቱ ጉዳዮች በአጭሩ ይዳሰሳሉ።
የአለም አቀፍ ስምምነቶች ምንነት
በቪየናው የዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች ሕግ (1969) አንቀጽ 2(1)(ሀ) በተሰጠው ትርጉም መሠረት “treaty” means an international agreement concluded between States in written form and governed by international law, whether embodied in a single instrument or in two or more related instruments and whatever its particular designation”. ይህ ወደ አማርኛ ሲመለስ “አለም አቀፍ ስምምነት” ማለት በአንድ ነጠላ ሰነድ ወይም ተያያዥነት ባላቸው ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ሰነዶች የሚካተት፣ በመንግሥታት መካከል በጽሑፍ የሚደረገና በዓለም አቀፍ ሕግ የሚገዛ ስምምነት ሲሆን፣ የተሰጠው ልዩ ስያሜ ምንም ይሁን ምን እንደዚሁ ይቆጠራል።” የሚል ትርጉም ይሰጠናል።
ከዚህ ድንጋጌ በተጨማሪ እንደምንረዳው በተግባርም እንደሚታየው አለም አቀፍ ስምምነቶች በተለያዩ ስያሜዎች ማለትም የውል ስምምነት (Treaty)፣ ኮንቬንሽን (Convention)፣ ፓክት (Pact)፣ ፕሮቶኮል (Protocol) ወይም ቻርተር (Charter) ተብሎ ሊጠሩ ይችላሉ።
በአገራችን በአለም አቀፍ ስምምነቶች መዋዋያ እና ማጽደቂያ ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1024/2009 አንቀጽ 2(7) መሠረት አለም አቀፍ ስምምነት ማለት በአለም አቀፍ ሕግ የሚገዛ በኢትዮጵያ እና በሌላ አገር መካከል የተፈፀመ የሁለትዮሽ ስምምት፣ በኢትዮጵያና በሁለት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ አገራት መካከል የተፈፀመ የባለብዙ ወገን ስምምነት ወይም በኢትዮጵያና እና በአለም አቀፍ ድርጅት ወይም ድርጅቶች መካከል የተፈፀመ የሁለትዮሽ ወይም የባለብዙ ወገን ስምምነት ነው፡፡ ይህ ትርጉም ከቪየናው ስምምነት ትርጉም ጋር ተቀራራቢነት ያለው ሲሆን አለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የሚደረገውንም ስምምነት አካቶ ይገኛል፡፡
የአለም አቀፍ ስምምነት ዓይነቶች
አለም አቀፍ ስምምነቶች በተለያዩ መስፈርቶች የተለያዩ ክፍፍሎች ቢኖራቸውም እንደ ተሳታፊዎቻቸው ብዛት በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፈላሉ፡-
• የሁለትዮሽ ስምምነቶች (Bilateral Treaties):- በሁለት አገራት መካከል ብቻ የሚደረጉ ስምምነቶች ናቸው። ለምሳሌ በሁለት አገራት መካከል የተደረገ የድንበር ወይም የሁለትዮሽ የንግድ ስምምነት።
• ባለብዙ ወገን ስምምነቶች (Multilateral Treaties):- ከሁለት በላይ በሆኑ በርካታ አገራት መካከል የሚደረጉ ስምምነቶች ናቸው። ለምሳሌ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር ወይም የፓሪስ የአየር ንብረት ስምምነት።
የስምምነቶች አተረጓጎም (Interpretation of Treaties)
አለም አቀፍ ስምምነቶች የሚፈፀሙባቸው ወይም የሚተረጎምባቸው መንገዶች በቪየናው የስምምነቶች ሕግ ከአንቀጽ 31 እስከ 33 የተደነገጉ ሲሆን የአለም አቀፍ ስምምነቶችን የሚመለከቱ ክርክሮች ወይም ልዩነቶች የሚዳኙት ከነዚህ ድንጋጌዎች አንፃር ይሆናል። በዚህም በተጠቀሰው ስምምነት አንቀጽ 31 መሠረት ማንኛውም ስምምነት በቅን ልቦና (Good Faith) መተርጎም እንዳለበት በግልፅ ተመላክቷል፡፡ በመሆኑም በስምምነቱ ቃላት ለሚሰጣቸው መደበኛ (ተራ) ትርጉም፣ በአውዱ (Context) ውስጥ እንዲሁም የስምምነቱን ዓላማና ግብ (Object and Purpose) ከግምት ውስጥ በማስገባት መፈጸም ይኖርበታል። ይህም አጠቃላይ የትርጓሜን ደንብ (General rule of interpretation) መሠረት ያደረገ ነው።
ሌላው በአንቀጽ 32 መሠረት በተጨማሪ የትርጓሜ ዘዴዎች (Supplementary means of interpretation) የሚደረግ ትርጉም ሲሆን የስምምነት ድንጋጌ ትርጉም በቅን-ልቦና አተረጓጎም መሠረት ከተተረጎመ በኋላም ግልጽ ካልሆነ ወይም አሻሚ ከሆነ ትክክለኛውን ትርጉም ለማግኘት የምንጠቀምባቸው ዘዴዎች ናቸው። ይህም የስምምነቱን ዝግጅት ሥራ (preparatory work of the treaty) እና ስምምነቱ የተደረገበትን ሁኔታ (Circumstances of its conclusion) ያካትታል። በመጨረሻም በሁለቱ የአተረጓጎም ዘዴዎች መሠረት ከተተረጎመ በኋላም ግልጽ ካልሆነ ወይም አሻሚ ከሆነ በሁለት ወይም ከዚያ በላይ ቋንቋዎች በይፋ የተረጋገጡ ስምምነቶች ትርጓሜ በመጠቀም ትክክለኛውን ትርጉም ለማግኘት ጥቅም ላይ የሚውል ዘዴ ተደንግጎ እናገኛለን። ይህም በአንቀጽ 33 የተደነገገ መርህ ሲሆን አንድ ስምምነት በሁለት ወይም ከዚያ በላይ ቋንቋዎች በእኩል ሕጋዊ ኃይል የተረጋገጠ (authenticated) ከሆነ ሁሉም የቋንቋ ጽሑፎች በእኩል ዋጋ ይታያሉ። በቋንቋዎች መካከል የትርጉም ልዩነት ከተፈጠረ የስምምነቱን ዓላማና ግብ በተሻለ ሁኔታ የሚያሳካው ትርጉም ይመረጣል።
የስምምነቶች ዋጋ ማጣት (invalidity of treaties)
የስምምነት ዋጋ ማጣት (invalidity of treaties) ስምምነቱ በአለም አቀፍ ሕግ የተቀመጡ መስፈርቶችን ባለማሟላቱ ወይም በሕጋዊ ጉድለቶች ምክንያት ሕጋዊ ኃይሉን ማጣቱን የሚያመላክት ነው። አንድን ስምምነት ዋጋ ቢስ የሚያደርጉ ምክንያቶች በቪየናው የስምምነቶች ሕግ ከአንቀጽ 46 እስከ 53 ባሉት ድንጋጌዎች የተካተቱ ሲሆን እነርሱም፡-
o ሥምምነቱ የተደረገው የአገር ውስጥ ሕግን በመጣስ ከሆነ (Violation of internal law regarding competence to conclude treaties)(አንቀጽ 46)
o ስምምነቱ የተደረገው የተወካይን ሥልጣን ገደብ በመጣስ ከሆነ (Specific restrictions on authority) (አንቀጽ 47)
o በፍሬ ነገር ወይም በሁኔታ ላይ ስህተት ሲኖር (Error)(አንቀጽ 48)
o በተደራዳሪ ወገን የተፈፀመ ማጭበርበር ሲኖር (Fraud)(አንቀጽ 49)
o ስምምነቱን የፈረመው ተወካይ ሥምምነቱን የፈረመው ከሌላ ተደራዳሪ ጋር በተፈፀመ ሙስና ከሆነ (Corruption of a representative)(አንቀጽ 50)
o ስምምነቱ የተፈረመው በአገር ተወካይ ላይ በተደረገ ማስገደድ ከሆነ (Coercion of state representative)(አንቀጽ 51)
o ስምምነቱ የተደረገው የአለም አቀፍ ሕግን በመጣስ በሌላ አገር ላይ ኃይል ለመጠቀም በተደረገ ማስፈራራት ከሆነ (Coercion of a State by the threat or use of force) (አንቀጽ 52)እና
o ስምምነቱ ከአጠቃላይ ዓለም ዓቀፍ ሕግ አስገዳጅ መርሆዎች ጋር የሚጋጭ ከሆነ (Treaties conflicting with a peremptory norm of general international law (“jus cogens”)( አንቀጽ 53) ናቸው።
የስምምነቶች መቅረትና ለጊዜው መቋረጥ (Termination and suspension of the operation of treaties)
የስምምነቶች መቅረትና መቋረጥ የሚፈፀመው አንድ አዓለም አዓቀፍ ስምምነት ስለመቅረቱና ስለመቋረጡ ስምምነቱ ራሱ በሚደነግገው መሠረት ወይም ደግሞ ሁሉም ተዋዋይ አገሮች እንዲቀር ወይም እንዲቋረጥ በሚስማሙበት ጊዜ ነው። ምንጊዜም ቢሆን አንድ ስምምነት የተቋቋመበት ዓላማ ሲያበቃ ወይም ስምምነቱ የጊዜ ገደብ ያለው ሲሆን የተወሰነው ጊዜ ካለፈ ስምምነቱ ቀሪ ይሆናል።
ከሁለት በላይ የሆኑ አገራት ስምምነት ሲያደርጉ ተዋዋዮቹ ወገኖች የተወሰኑ ድንጋጌዎችን አፈጻጸም ለጊዜው ለማቋረጥ ሊስማሙ ይችላሉ። ይህ ዓይነቱ ስምምነት ሕጋዊ የሚሆነው በጉዳዩ በተስማሙበት አገራት መካከል ነው። ስምምነትን ማቋረጥ የሚቻለው ፈቃጅየሚፈቅድ ድንጋጌ በሚኖርብት ጊዜ፣ የስምምነቱ መቋረጥ የሌሎችን አባል አገራት መብት የማይጥስ ወይም ግዴታቸውን ከመፈፀም የማያግዳቸው ሲሆንና አጠቃላይ የስምምነቱን ዓላማና ተግባር የማይፃረር ሲሆን ነው።
አለም አቀፍ ስምምነትን የብሔራዊ ሕግ አካል የማድረግ ሥርዓት
አለም አቀፍ ስምምነቶች የአንድ አገር የብሔራዊ ሕግ አካል ለመሆን የሕግ ማዕቀፍ ማግኘት እና የተለያዩ ሥርዓቶችን ማለፍ ይጠበቅባቸዋል። እንደማሳያ በየአገሮቹ የሥራ አስፈፃሚው አካል ድርድር እና ውይይት መደረግ፣ በተዋዋይ አገሮች እንደራሴዎች ተፈርመው እና የሕግ አውጪ ምክር ቤቶችን ይሁንታ አግኝተው መጽደቅ ይኖርባቸዋል።
በቪየናው የስምምነቶች ሕግ አንቀጽ 11 ስር እንደተደነገገው የአገራት በስምምነቱ ለመገዛት ፍቃደኛ መሆን ፊርማቸውን በማኖር፣ የስምምነት ሰነዱን በመለዋወጥ፣ በማጽደቅ፣ በመቀበል፣ ወይም በመቀላቀል ወይም ከተስማሙ በማንኛውም ሌላ መንገድ ሊገለጽ ይችላል።
በአገራችንም አለም አቀፍ ስምምነቶች የሚፀኑት በማጽደቅ ሥነ- ሥርዓት ሲሆን በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 55(12) ስር እንደተደነገገው የሕግ አስፈፃሚው አካል የሚዋዋላቸውን አለም አቀፍ ስምምነቶች የማፅደቅ ሥልጣን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። በዚህ ድንጋጌ መሠረት በአለም አቀፍ ስምምነቶች ዙሪያ የመደራደር፣ የመፈረምና የመዋዋል ሥልጣን የሥራ አስፈፃሚው አካል መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። ይህ የሥራ አስፈፃሚው ኃላፊነት በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 77 የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሥልጣንን በሚደነግገው ክፍል ሥር በግልጽ የተቀመጠ አይደለም። ነገር ግን በአስፈጻሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር መወሰኛ አዋጅ ቁጥር 1263/2014 አንቀጽ 39(1)(ሐ) ላይ በግልጽ እንደተደነገገው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያ ከሌሎች መንግሥታትና አለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የምታደርጋቸውን ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር ለመደራደርና ለመፈረም ሥልጣን ተሰጥቶታል። እንዲሁም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አለም አቀፍ ውሎች እንዲጸድቁ ለማድረግ የሚያስፈልጉትን ፎርማሊቲዎች ሁሉ ያከናውናል።
አስፈፃሚው አካል የፈረመውን ስምምነት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስምምነቱን ያጸደቀው ከሆነ የጸደቀው ስምምነት በሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት በተፈረመ ጊዜ ወይም ለፕሬዚዳንቱ ከደረሰ ከ15 ቀናት በኋላ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ እንዲወጣ ይደረጋል። በዚህ መልኩ ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸው አለም አቀፍ ስምምነቶችም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 9(4) መሠረት የአገሪቱ ሕግ አካል ይሆናሉ።
ማጠቃለያ
በአጠቃላይ አገራት የተለያዩ ጉዳዮችን ለማከናወን ስምምነቶችን የሚፈራረሙ ሲሆን ስምምነቶቹ የሚፈፀሙት በዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች ሕግ መሠረት ነው። ስምምነቶች የተለያዩ ሁኔታዎችን አሟልተው እንደሚቋቋሙ ሁሉ በሕግ የተቀመጡ ሁኔታዎችን ያላሟሉ እንደሆነ ዋጋ ቢስ ይሆናሉ። የስምምነቶች መሰረዝ እና መቋረጥም በአለም አቀፍ ስምምነቶች ሕግ መሠረት የሚከናወን ነው። እንዲሁም ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶችን የአንድ አገር ሕግ አካል ለማድረግ በሕግ የተቀመጡ ሁኔታዎች መሟላት ያለባቸው ሲሆን በኢትዮጵያ የኢ.ፈ.ዲ.ሪ. ሕገ መንግሥት አለም አቀፍ ስምምነቶች የአገሪቱ ሕግ አካል የሚሆኑበትን ሁኔታ ደንግጎ ይገኛል።
በንቃተ ሕግና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ
የፍትሕ ሚኒስቴርን የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገፆችን እና ድረ-ገፅን ይቀላቀሉ
Website
https://www.justice.gov.et
Facebook
https://web.facebook.com/MOJEthiopia/
(x) Twitter
https://x.com/MOJEthiopia
YouTube channel
https://youtube.com/...3701...
Telegram
https://t.me/fdreattorneyGeneral_externa