06/09/2026
የ2026 የፊፋ የ"ያንግ ታለንት" የወጣት ዳኞች ስልጠና ተጠናቀቀ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከፊፋ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የፊፋ "ያንግ ታለንት" የወጣት የጨዋታ አመራሮች ስልጠና ላለፉት አምስት ተከታታይ ቀናት በተግባር እና ንድፈ ሐሳብ ሲሰጥ ቆይቶ ዛሬ በአዜማን ሆቴል በይፋ ተጠናቋል።
በፊፋ ቴክኒክ ኢንስትራክተር ሊ ቾንግ፣ በፊፋ የአካል ብቃት ኢንስትራክተር ማርክ ምዜንጎ እንዲሁም በሀገር ውስጥ ኢንስትራክተሮች አማካኝነት ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ማጠናቀቂያ ላይ ኢንስትራክተር ጌራወርቅ ከተማ ባደረጉት ንግግር ስልጠናው ምንም እንኳን አጭር ቆይታ ቢሆንም ሰልጣኞች ከፍተኛ እውቀት ያገኙበት እንደነበር ገልጸዋል። አክለውም ሰልጣኞች ወደየመጡበት ሲመለሱ ያገኙትን እውቀት መተግበር እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የፊፋ ቴክኒክ ኢንስትራክተር ሚስተር ሊ ቾንግ በበኩላቸው ፌዴሬሽኑ ለወጣት ዳኞች ትኩረት ሰጥቶ ይህንን መርሐ ግብር በአንድ ሆቴል በማሰባሰብ ስላዘጋጀ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በስልጠናው ወቅት በዘመናዊ የመግባቢያ ቴክኖሎጂዎች እና በቪዲዮ የተደገፉ አዳዲስ የዳኝነት ፅንሰ-ሀሳቦችን ማስተዋወቅ መቻሉን የገለጹት ሚስተር ሊ "ይህ አሰራር አርአያነት ያለው ሞዴል በመሆኑ ሌሎች ሀገራትም እንደሚተገብሩት አልጠራጠርም" ብለዋል። በተጨማሪም ቀደም ሲል ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማን በወጣትነቱ ተመልከተው አቅሙን እንደተረዱ በማስታወስ የወጣት ዳኞች አቅም በስልጠና እና በተግባር ማደግ እንደሚችልና በቀጣይም ከእነዚህ ሰልጣኞች መካከል በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገራቸውን የሚያስጠሩ ዳኞች እንደሚወጡ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የፊፋ የአካል ብቃት ኢንስትራክተር ሚስተር ማርክ ምዜንጎ በስልጠናው የተሳተፉት ወጣት ዳኞች ከኤሊት ዳኞች ጋር ያላቸው የአቅም ልዩነት በጣም አነስተኛ መሆኑን ጠቁመው "አካል ብቃት ለዳኝነት እንደ ቪዛ ነው፤ ያለ ቪዛ ትኬት ቢኖራችሁ እንኳ መጓዝ እንደማትችሉ ሁሉ ያለ አካል ብቃትም ወደ ላቀ ደረጃ መሸጋገር አይቻልም" በማለት ሰልጣኞች ጠንክረው እንዲሰሩ መክረዋል።
የኢ/እ/ፌ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ባሕሩ ጥላሁን በበኩላቸው ፌዴሬሽኑ አዳዲስ አሰራሮችንና ስትራቴጂዎችን በመቅረፅ ወጣት ዳኞችን ለማፍራት እያደረገ ያለውን ጥረት አብራርተዋል። እንደ ባምላክ ተሰማ እና ሊድያ ታፈሰ ያሉ አንጋፋ ዳኞች ከዳኝነት መገለላቸውን ተከተሎ የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት የትውልድ ቅብብሎሹ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል። አዳዲስ አሰራሮች ሲዘረጉ ከውስጥም ከውጭም ተቃውሞዎች ማጋጠማቸው አልቀሬ ቢሆንም ፌዴሬሽኑ ወጣት ዳኞች ላይ ኢንቨስት ማድረጉን እንደሚቀጥልና ለሰልጣኞች ማደሪያና ስልጠና ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
አቶ ባሕሩ የኢትዮጵያ ዳኞች በታማኝነት እና በቅንነት ሥራቸውን በማከናወን በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ መልካም ስም ያላቸው መሆኑን ገልጸው አዲሶቹ ወጣት ዳኞችም ይህንን ታማኝነት እና ሙያዊ ብቃት አስጠብቀው እንዲቀጥሉ አደራ ብለዋል።