05/09/2018
“በከተሞች የሚታዬውን የመሬት ወረራ ለመቆጣጠር የካዳስተር ስርዓቱን በቁርጠኝነት ተግባራዊ ማድረግ ይገባል” አቶ ጃንጥራር አባይ-የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር
16ኛው የከተማ ልማትና ቤቶች ሴክተር ጉባኤ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል
የከተማ ልማትና ቤቶች ዘርፍ ሴክተር ጉባኤ በአዳማ ከተማ በተካሄደበት ወቅት የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትሩ አቶ ጃንጥራር አባይ ለተሳታፊዎች እንደገለፁት፣ በከተማ መሬት አስተዳደር ላይ እየታየ ያለውን ብልሹ አሰራር ለመቅረፍ የህጋዊ ካዳስተር ስርዓቱን በሙሉ አቅም ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ የከተማ መሬት አስተዳደር ስርዓቱን የዘመነ በማድረግ አገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋ ለማድረግ የህጋዊ ካዳስተር ስራ ቁልፍ ስራችን ይሆናልብለዋል፡፡
መንግስት የከተማ መሬት አስተዳደር ስርዓቱን የዘመነ ለማድረግ የህጋዊ ካዳስተር ስርዓትን በሀገር ደረጃ ወጥና ተናባቢ በሆነ መልኩ በከፍተኛና መካከለኛ ከተሞች ለመተግበር ይችል ዘንድ በሁለተኛው ዕደገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን በእቅድ አካቶ መያዙ የሚታወቅ ነው፡፡ሆኖም የበላይ አመራሩ ለስራው የሰጠው ትኩረት አናሳ በመሆኑ ስራው የሚፈልገው ግብዓት በወቅቱ ባለመሟላቱ የዜጎች የይዞታ ዋስትና የማረጋገጥ ስራዎች በሚፈለገው ደረጃ እየተከናወኑ እንዳልሆነ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
በመሆኑም በሚቀጥሉት አመታት የህጋዊ ካዳስተር ስርዓቱን በከተሞች ተግባራዊ በማድረግ በመሬት ዘርፍ የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችን ለማስዎገድ ከመቸው ጊዜ በላይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡
በ2010 በጀት አመት በሀገራችን በ14 ከተሞች 107,208 /አንድ መቶ ሰባት ሺህ ሁለት መቶ ስምንት/ ይዞታዎች ላይ የይዞታ ማረጋገጥ ሥራ የተከናወነ ሲሆን በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በ6 ከተሞች (ባህር ዳር፣ ጎንደር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደሴ፣ ኮምቦልቻ እና ደብረ ብርሃን) 2,783 ይዞታዎች፣ በደቡብ ብ/ብ/ህ/ ክልል በሚገኙ 6 ከተሞች (ወላይታ ሶዶ፣ አርባ ምንጭ፣ ሆሳዕና፣ ዲላ ፣ አርባ ምንጭ፣ ሐዋሳ እና ሳውላ) 9,343 ዞታዎች፣ በኦሮሚያ ክልል በአዳማ ከተማ ብቻ 840 ይዞታዎች፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 94,242 ይዞታዎች ላይ የይዞታ ማረጋገጥ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡
በሌላ በኩል በሰባት ከተሞች ለ69,758 ዜጎች የይዞታ ዋስትና ምዝገባ የተካሄደ ሲሆን በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት በሚገኙ 5 ከተሞች (በሃዋሳ፣ ዲላ፣ አርባምንጭ፣ ወላይታ ሶዶ እና ሆሳዕና) 3,754 የመሬት ይዞታዎች ፣ በአማራ ክልል 1 ከተማ (ደ/ማርቆስ) 20 የመሬት ይዞታዎች፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር (በማነዋል- 26,299 እና በሲስተም 39,685 የመሬት ይዞታዎች) በድምሩ 65,984 ይዞታዎች የይዞታ ዋስትና ምዝገባ ተካሂዷል፡፡
የይዞታ ማረጋገጥና የምዝገባ ስራዎቻችን ከታቀደው አንፃር ሲታዩ ዝቅተኛ አፈፃፀም ያላቸው ሲሆን ለዚህም በምክንያትነት የሚጠቀሱት ስራውን አቅሎ በማየት በቅድመ ዝግጀት ሥራ ላይ አጥርቶ ባለመስራት የገጠሙ ፈተናዎች መበራከት፤ የምዝገባ ተቋም በማቋቋም ወደ ስራ ያለመግባት፣ በከተማ የምዝገባ ተቋሙ በሰው ሃይልና በግብአት ያለመሟላት እና ከመብት ሰጪው ተቋም የይዞታ ሰነዶች ተደራጅተው እንዲቀርብ ማድረግ ባለመቻሉ እና በዋናነት ግን የአመራሩ ተረጋግቶ አለመቀመጥና የፖለቲካ አመራሩ ለዘርፉ የሚፈለገውን ያህል ትኩረት አለመስጠት ናቸው፡፡ ለአብነትም የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ወደ ተግባር ያለመግባት፣ በሐረሪብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ተቋሙ በተደራጀ አግባብ ያለማቋቋም፣ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳድር በቂ የሆነ የሰው ኃይል እና የግብአት አቅርቦት ያለመሟላት፣ ኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ከአዳማ ከተማ ውጪ ቀሪዎቹ ወደ ስራ ያለመግባት ይጠቀሳሉ፡፡
16ኛውን የከተማ ልማትና ቤቶች ዘርፍ ሴክተር ጉባኤን የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የዘርፉ ቢሮ ሀላፊዎች፣ የኤጀንሲ ሀላፊዎች፣ የዘርፉ ባለሙያዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመውታል፡፡