Gullele Sub City Small Tax Payers Branch Office

Gullele Sub City Small Tax Payers Branch Office Revenue Collection

06/07/2026

ይህ ቻናል በገቢዎች ሚኒስቴር የመካከለኛ ግብር ከፋዮች ቁ.2 ቅ/ጽ/ቤት የከፈተው ኦፊሴላዊ የዩቲዩብ ቻናል...

06/07/2026

የኤሌክትሮኒክ ደረሰኝ ሥርዓት አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 1142/2018 በአጭሩ

***********************************

የታክስ አስተዳደራችንን ዘመናዊ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ እንዲሁም የግብር ስወራን ለመከላከል የገቢዎች ሚኒስቴር አዲስ የኤሌክትሮኒክ ደረሰኝ ሥርዓት አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 1142/2018 (Directive No. 1142/2026) አውጥቷል።

በመመሪያው የተካተቱ ዋና ዋና ነጥቦች፦

•ዲጂታል ደረሰኝ (Electronic Invoice)፦ በየቀኑ የሚደረጉ ግብይቶች በሚኒስቴሩ እውቅና ባገኘ ሶፍትዌር አማካኝነት ዲጂታል ሆነው ይመዘገባሉ። እያንዳንዱ ደረሰኝ ልዩ የደረሰኝ ምዝገባ ቁጥር (IRN) እና ፈጣን መላሽ ኮድ (QR Code) ይኖረዋል።

•የኢኮሜርስ (e-Commerce) እና የዲጂታል ገበያ ቦታዎች፦ በኦንላይን መድረኮች ላይ የሚከናወኑ ግብይቶችም በተናጠል በሻጩ የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር (TIN) ደረሰኝ እንዲቆርጡ ሥርዓት ተዘርግቶላቸዋል።

•ከቀጥታ ግንኙነት ውጭ (Offline Mode) መሥራት፦ የኢንተርኔት ግንኙነት በሚቋረጥበት ወቅት ግብይት እንዳይስተጓጎል ለተወሰነ ጊዜ ከመስመር ውጭ ሽያጭን መመዝገብና ግንኙነቱ ሲመለስ በቀጥታ ወደ ማዕከላዊ ሲስተሙ መላክ የሚያስችል አማራጭ ተካቷል።

• ጠንካራ የደህንነት ሥርዓት፦ ጥቅም ላይ የሚውሉ የሽያጭ መመዝገቢያ ሶፍትዌሮች ሁሉ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የደህንነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ማቅረብ ይኖርባቸዋል።

ለአቅራቢዎችና ለአገልግሎት ሰጪዎች የተቀመጡ ቅድመ-ሁኔታዎች፦

•የዕውቅና ምስክር ወረቀት ለማግኘት አልሚዎችና አቅራቢዎች እንደየዘርፋቸው ተስማሚ የባለሙያ ብዛትና በየሁለት ዓመቱ የሚታደስ የመልካም አፈጻጸም ዋስትና (Performance Guarantee) በባንክ ወይም በመድን ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፦

•የሽያጭ መመዝገቢያ ሥርዓት አቅራቢዎች፦ 30,000 የአሜሪካን ዶላር ዋስትና እና ቢያንስ 4 ባለሙያዎች

•የሶፍትዌር አገልግሎት አቅራቢዎች ፦ 50,000 የአሜሪካን ዶላር ዋስትና እና ቢያንስ 6 ባለሙያዎች

•የኢኮሜርስ ኦፕሬተሮች፦ 25,000 የአሜሪካን ዶላር ዋስትና

•ለራሱ ብቻ የሚጠቀም ታክስ ከፋይ፦ 15,000 የአሜሪካን ዶላር ዋስትና

የዋስትና መጠኑና የባለሙያዎቹ ብዛት እንደ ታክስ ከፋዮች ብዛትና ዓመታዊ ጥቅል የሽያጭ መጠን ሊጨምር ይችላል። ይህ መመሪያ በታክስ ሕጉ መሠረት የሂሳብ መዝገብ በሚይዙ ሁሉም ታክስ ከፋዮች ላይ ተፈጻሚ ይሆናል።

30/06/2026

በኢትዮጵያ ውስጥ የካሽ ማሽን አጠቃቀም ለብዙ ሰዎች ፈተና ነው፡፡ይህ የአንድ አጋጣሚ ቪዲዮ ሊጠቅም ይችላል...

30/06/2026

አቅርቦት ተከናወነ የሚባልበትን ጊዜ መረዳት (Understanding the Time of Supply)
*******************************

አቅርቦት ተከናወነ የሚባልበትን ጊዜ (Time of Supply) መረዳት በተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) አስተዳደር ውስጥ መሰረታዊ ጽንሰ-ሀሳብ ነው። ይህ ጊዜ የታክስ ግዴታ በትክክል መቼ እንደሚጀምር እና በዚህም ምክንያት ግብይቱ ለታክስ ባለስልጣን ሪፖርት መደረግ ያለበትን የታክስ ዘመን ይወስናል።

በተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 1341/2016 አንቀጽ 21(1) መሠረት አቅርቦት ተከናወነ የሚባለው ከሚከተሉት ሶስት ሁነቶች ቀድሞ በሚከሰተው ላይ ነው፦

1. የቫት ታክስ ደረሰኝ (Tax Invoice) የተቆረጠበት ቀን።
2. ማናቸውም ክፍያ (በከፊልም ቢሆን) የተፈጸመበት ቀን።
3. ዕቃዎቹ የተረከቡበት/ለገዢው ዝግጁ የሆኑበት ቀን ወይም ወይም በቀጥታ በገዢው ታክስ የሚከፈልበትን አቅርቦት በሚመለከት የአገልግሎት አሰጣጡ የተጠናቀቀበት ቀን።

ይህን አጠቃላይ ድንጋጌ ተግባራዊ በሆነ መልኩ ለማየት የሚከተሉትን ተጨባጭ ሁኔታዎች እንመልከት፡፡

ሁኔታ 1፦ የቅድሚያ ክፍያዎች እና የሰነድ ዓይነቶች (Advance Payments and Document Types)

• ምሳሌ 1፦ ኩባንያ "ሀ" ዋጋው 2,000,000 ብር የሆነ ጥሬ ዕቃ ከኩባንያ "ለ" ለመግዛት ተስማማ። ኩባንያ "ሀ" ዕቃዎቹን ከመረከቡ በፊት ሙሉውን ገንዘብ በቅድሚያ ይከፍላል፡፡ ኩባንያ "ለ" ደግሞ የቅድሚያ ክፍያውን ሲቀበል መደበኛ የሽያጭ ደረሰኝ ከመስጠት ይልቅ የገንዘብ መቀበያ ሰነድ (Cash Receipt Voucher) ለገዢው ይሰጣል፡፡ ይህ ድርጊት በተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ እንዲሁም በታክስ ደረሰኝ አጠቃቀም እና አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 149/2011 መሠረት ህጋዊ ወይስ ህገ-ወጥ? እስኪ ህጎቹ ምን እንደሚሉ እንመልከት፡፡
በተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 1341/2016 አንቀጽ 21 መሠረት፤ የመደበኛ የታክስ ደረሰኝ (Tax Invoice) የተቆረጠበት ቀን፣ ማናቸውም ክፍያ (በከፊልም ቢሆን) የተፈጸመበት ቀን፣ ዕቃዎቹ የተረከቡበት/ለገዢው ዝግጁ የሆኑበት ቀን ወይም የአገልግሎት አቅርቦትን ወይም በቀጥታ በገዢው ታክስ የሚከፈልበትን አቅርቦት በሚመለከት የአገልግሎት አሰጣጡ የተጠናቀቀበት ቀን አቅርቦት እንደተከናወነ ይቆጠራል።

በሌላ በኩል፣ በአዋጁ አንቀጽ 52(1) ላይ ታክስ የሚከፈልበትን አቅርቦት የሚያከናውን ማንኛውም የተመዘገበ ሰው፣ አቅርቦቱን ባከናወነበት ጊዜ ለገዢው መደበኛ የታክስ ደረሰኝ መስጠት እንዳለበት ተደንግጓል። ከዚህ በተጨማሪም የተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) ተመዝጋቢ የሆኑ ግብር ከፋይ ከዕቃ ወይም አገልግሎት አቅርቦት ግዢ ጋር በተያያዘ የቅድሚያ ክፍያ (Advance Payment) የተቀበለ እንደሆነ ለተቀበለው የቅድሚያ ክፍያ ወዲያውኑ የተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) ደረሰኝ የመስጠት ኃላፊነት እንዳለበት የታክስ ደረሰኝ አጠቃቀም እና አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 149/2011 አንቀጽ 13(4) ላይ ተገልፆ ይገኛል፡፡
በመሆኑም ኩባንያ "ለ" የግብይቱን ሙሉ ክፍያ በቅድሚያ የተቀበለ በመሆኑ በአዋጁ መሠረት ክፍውን በተቀበለበት ጊዜ አቅርቦት እንደተከናወነ ይቆጠራል። በዚህ መሠረት ኩባንያው ዕቃዎቹን ለገዢው ባያስረክብ እንኳ፣ በሕጉ መሠረት የተጨማሪ እሴት ታክስ ግዴታው በቅድሚያ ክፍያው ምክንያት የተቋቋመ በመሆኑ ለገዢው መደበኛ የታክስ ደረሰኝ የመስጠት ግዴታ አለበት። ስለሆነም አቅራቢው ላከናወነው አቅርቦት መደበኛ የታክስ ደረሰኝ መስጠት ሲገባው፣ የገንዘብ መቀበያ ደረሰኝ (Cash Receipt Voucher) መስጠቱ በሕግ ረገድ ተቀባይነት የሌለው ተግባር ሲሆን ኩባንያው ለተቀበለው የ2,000,000 ብር የግብዓት አቅርቦት ቅድመ ክፍያ ዕቃዎቹን እስኪያስረክብ ሳይጠብቅ፥ ክፍያውን በተቀበለበት ጊዜ መደበኛ የታክስ ደረሰኝ መስጠት እና በዛው የታክስ ጊዜ (አንድ ወር) ውስጥ ሂሳቡን መመዝገብና ማሳወቅ አለበት።

ሁኔታ 2፦ መሸጫ ማሽኖች እና አውቶማቲክ መሣሪያዎች (Vending Machines and Automated Devices)
ለተወሰኑ የግብይት ዘዴዎች፥ አፈጻጸሙን ቀላል ለማድረግ ተስማሚ የሆኑ አንቀፆችን ደንግጓል። ለምሳሌ ዕቃዎች በሳንቲም፣ በኖት ወይም በቶክን (Tokens) በሚሠሩ ማሽኖች ወይም መሣሪያዎች አማካኝነት በሚቀርቡበት ጊዜ፥ ለእያንዳንዱ ግብይት የተወሰነውን ጊዜ መከታተል በተግባር አስቸጋሪ ነው።
አንቀጽ 21(2) እንደሚደነግገው፥ በእነዚህ አውቶማቲክ መሣሪያዎች ለሚከናወኑ ሽያጮች አቅርቦት የተከናወነበት ጊዜ ተደርጎ የሚወሰደው ገንዘቡ ወይም ቶክኑ በአቅራቢው ወይም በአቅራቢው ወኪል አማካኝነት ከማሽኑ ውስጥ በአካል በወጣበት (በተሰበሰበበት) ትክክለኛ ቀን ላይ ነው። አንድ ማሽን በጥር ወር ሙሉ ሳንቲሞችን ቢሰበስብም፥ ነጋዴው ማሽኑን ከፍቶ ገንዘቡን የሰበሰበው በየካቲት 2 ቀን ከሆነ፥ የዚያ ሽያጭ ሙሉ የቫት ግዴታ የሚወድቀው በየካቲት ወር የታክስ ዘመን ውስጥ ነው።

ሁኔታ 3፦ በየጊዜው እና በተከታታይ የሚከናወኑ አቅርቦቶች (Periodic and Continuous Supplies)
ሁሉም ግብይቶች በአንድ የተወሰነ ጊዜ ላይ ብቻ ተከስተው አያልቁም። እንደ የኪራይ-ግዢ ስምምነቶች (Hire-purchase)፣ የፋይናንስ ሊዝ (Finance Leases)፣ የቤት/ንብረት ኪራይ ወይም ደረጃ በደረጃ የሚፈጸሙ የአገልግሎት ውሎች ያሉ የረጅም ጊዜ ስምምነቶች በአንቀጽ 21(4) መሠረት "በየጊዜው የሚከናወኑ አቅርቦቶች" (Periodic Supplies) ተብለው ይመደባሉ።
ሕጉ ሙሉውን የረጅም ጊዜ ውል እንደ አንድ ግዙፍ ግብይት ከመቁጠር ይልቅ በአንቀጽ 21(3) መሠረት ውሉን በተከታታይ ወደሚከናወኑ የተለያዩ ትናንሽ አቅርቦቶች ይከፋፍለዋል። ለእያንዳንዱ ተከታታይ ክፍል የታክስ ማሳወቂያ ጊዜ የሚሆነው ከሚከተሉት ሁለት ቀናት ቀድሞ በሚመጣው ቀን ነው፦

1. ክፍያው መፈጸም ያለበት ቀን (Due date)።

2. ክፍያው በተግባር የተገኘበት ቀን (Received date)።

ምሳሌ፦ ኩባንያ "A" ለአንድ ዓመት የሚቆይ የቢሮ ሕንፃ ለኩባንያ "B" አከራየ፤ በውሉ መሠረት ክፍያው በየወሩ በ1ኛው ቀን መፈጸም አለበት።

ትምህርታዊ ትንታኔ፦ ይህ በሊዝ ውል አማካኝነት በየጊዜው የሚቀርብ የአገልግሎት ዓይነት ነው። ለ12ቱም ወራት የሚሆነውን ቫት (VAT) ገና መጀመሪያ ላይ በአንድ ጊዜ ከማሳወቅ ይልቅ፥ ግብይቱ እንደ 12 የተለያዩ አቅርቦቶች ይቆጠራል። ኩባንያ "B" የጥር ወር ኪራዩን በታህሳስ 28 ቀን በቅድሚያ ቢከፍል፥ የዚያች ክፍል የታክስ ማሳወቂያ ጊዜ ታህሳስ (ገንዘቡ የተገኘበት ቀን) ይሆናል። በአንጻሩ ኩባንያ "B" ቢያረፍድና የየካቲት ወር ኪራዩን በየካቲት 10 ቀን ቢከፍልም እንኳ፥ የታክስ ማሳወቂያ ጊዜው አሁንም የካቲት ወር (ክፍያው መፈጸም በነበረበት ቀን) ይሆናል።

30/06/2026

አስተዳደራዊ መቀጫን ስለማስታወቅ (መመሪያ ቁ. 1063 መሠረት)

▫️ የታክስ ህጎችን በመተላለፍ የተፈጸመዉ ጥፋት ግልጽና መቀጫዉ የሚጣለዉ በታክስ አዋጆች በተደነገገዉ መሠረት እስከሆነ ድረስ አስተዳደራዊ መቀጫን ለማስታወቅ የሚሰጠዉ ማስታወቂያ የታክስ ኦዲት ሳይደረግ ሊሰጥ ይችላል ፡፡
▫️ አስተዳደራዊ መቀጫን ለመጣል የሚሰጠዉ ማስታወቂያ ገቢን የማስታወቅ ግዴታን ባለመወጣት ፣ ገቢን አሳንሶ በማስታወቅ ፣ ታክስ ባለመክፈል እና በመሳሰሉት ሌሎች የህግ የመተላለፍ ተግባራት የሚሰጥ ሲሆን ፤አስገዳጅነት ያለዉ መቀጫን የማስከፈያ ትዕዛዝ በመሆን ያገለግላል ፡፡

26/06/2026

የዕቃ ቆጠራ እና የጠፉ ዕቃዎች በኤክሳይዝ ታክስ አስተዳደር ሥርዓት መመሪያ ቁጥር 1071/2017 መሠረት

1) እያንዳንዱ የተፈቀደለት ሰው በእያንዳንዱ የተፈቀደለት ፋብሪካ ውስጥ የሚገኙ ጥሬ ዕቃዎችን ጨምሮ በፋብሪካው ውስጥ በሚገኙ ዕቃዎች ላይ በየዓመቱ የተሟላ ቆጠራ ማካሄድ አለበት፡፡
2) ከዚህም በተጨማሪ የተፈቀደለት ሰው ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን የሚያሳይ ተከታታይነት ያለው ወርሀዊ ቆጠራ ማካሄድ አለበት፡-
ሀ) በእያንዳንዱ ወር መጨረሻ በፋብሪካው ውስጥ የሚገኘውን ጥሬ ዕቃና የመጨረሻ ምርት፣
ለ) አዲስ ወደ ፋብሪካው የገቡ ጥሬ ዕቃዎችን፣
ሐ) በፋብሪካው ውስጥ ጥቅም ላይ የዋሉ ጥሬ ዕቃዎችን፣
መ) በፋብሪካው የተመረቱ የመጨረሻ ምርቶችን፣
ሠ) በፋብሪካው ተመርተው ወደፋብሪካው መጋዘን የገቡ ዕቃዎችን
ረ) የኤክሳይዝ ታክስ ተከፍሎባቸው ከፋብሪካው ቅጥር ግቢ የወጡ ዕቃዎችን፣
ሰ) የኤክሳይዝ ታክሰ ሳይከፈልባቸው ከፋብሪካው ቅጥር ግቢ የወጡ ዕቃዎችን፣
ሸ) የታክሱ ባለሥልጣን በሚያወጣው መመሪያ በሚወሰነው መሠረት በአደጋ ምክንያት ከጥቅም ውጪ የሆኑ ዕቃዎችን፣

26/06/2026

የተመዘገበ የውጭ አቅራቢ የተጨማሪ እሴት ታክስ ሰነዶች እና የሚከፈል የተጨማሪ እሴት ታክስ
************************************

1/ የተመዘገበ የውጭ አቅራቢ ለሚያቀርባቸው ታክስ የሚከፈልባቸው አቅርቦቶች የታክስ ደረስኝ መስጠት የለበትም፤ ሆኖም የሚከተሉትን መረጃዎች የያዘ የኤሌክትሮኒክስ ደረሰኝ መስጠት አለበት፦

ሀ) ለኢንቮይሱ ወይም ለደረሰኙ በተለይ የተሰጠ ቁጥር፤
ለ) የውጭ አቅራቢውን ስም፤ አድራሻ፤ የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር እና የተጨማሪ እሴት ታክስ ምዝገባ ቁጥር፤
ሐ) የአቅርቦቱን ተቀባይ ስም እና አድራሻ፤
መ) አቅርቦቱ የተፈጸመበትን ቀን፤
ሠ) የዕቃዎቹን እና ከሩቅ የተሰጡትን አቅርቦቶች መግለጫ፤ እና
ረ) ለአቅርቦቱ የተከፈለውን ዋጋ እና የተከፈለውን የተጨማሪ እሴት ታክስ

2/ የተመዘገበ የውጭ አቅራቢ የተጨማሪ እሴት ታክስ ሰነዶችን በውጭ አገር ሊይዝ የሚችል ሲሆን፤ በታክሱ ባለስልጣን በሚሰጥ የጽሁፍ ማስታወቂበሚወሰን ቀን እነዚህን ሰነዶች እንዲያቀርብ ተጠየቀ ጊዜ ማቅረብ አለበት።

በተመዘገበ የውጭ አቅራቢ የሚከፈል የተጨማሪ እሴት ታክስ
1/ የተመዘገበ የውጭ አቅራቢ በሂሳብ ጊዜው ሊከፈል የሚገባውን የተጨማሪ እሴት ታክስ ማስታወቅ ባለበት ጊዜ መክፈል አለበት።
2/ የተጨማሪ እሴት ታክስ የሚከፈለው የገቢዎች ሚኒስቴር በሚያወጣው መመሪያ በሚወስነው የኤሌክትሮኒክ ዘዴ መሆን አለበት።
3/የተመዘገበ የውጭ አቅራቢ የታክሱ ባለሥልጣን በሚፈቅደው መሠረት የተጨማሪ እሴት ታክሱን በአሜሪካ ዶላር፤ በዩሮ፤ በእንግሊዝ ፓውንድ ወይም በሌላ የገቢዎች ሚኒስቴር በሚያፀድቀው የውጭ አገር ገንዘብ ሊከፍል ይችላል።

የሒሳብ መዝገብ አያያዝ  የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ፡፡ሰኔ 18 ቀን 2018 ዓ.ም. በጉለሌ ክ/ከተማ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅ/ፅ/ቤት በተለያዩ ዘርፎች ለተሠማሩ ግብር ከፋዮች የተሻሻ...
25/06/2026

የሒሳብ መዝገብ አያያዝ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ፡፡
ሰኔ 18 ቀን 2018 ዓ.ም.
በጉለሌ ክ/ከተማ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅ/ፅ/ቤት በተለያዩ ዘርፎች ለተሠማሩ ግብር ከፋዮች የተሻሻለው የሒሳብ መዝገብ አያያዝ ቁጥር 176/2014 ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና የተሰጠ ሲሆን ስልጠናውን የተሰጠው በታክስ ከፋዮች ትምህርትና ድጋፍ ቡድን አስተባባሪ በአቶ ተስፋሁን ታገሰ ሲሆን ከስልጠናው መጠናቀቅ በኋላ በሰልጣኞች የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን በወቅቱ ለተነሱት ጥያቄዎች፣ አስተያየቶችና በስራዎቻቸው ላይ ስለሚገጥማቸው ችግሮች ላይ ተገቢውን ማብራሪያ እና ምላሽ ተሰጥቷል፡፡
በጉለሌ ክ/ከተማ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽ/ቤት
የታክስ ከፋዮች ትምህርትና ድጋፍ ቡድን

follow our telegram channel
https://t.me/G_Rev_tt

24/06/2026

የኤክሳይዝ ታክስ የሚከፈልበት ጊዜ

ሀ) የተፈቀደለት አምራች በኢትዮጵያ ውስጥ በሚያመርታቸው የኤክሳይዝ ታክስ በሚከፈልባቸው ዕቃዎች ላይ
የተመረቱት ዕቃዎች ፡-
• ከአምራቹ ፋብሪካ በሚወጡበት ጊዜ የኤክሳይዝ ታክሱን የመክፈል ግዴታ ይቋቋማል፡፡
• በተፈቀደለት አምራች ፋብሪካ ውስጥ ጥቅም ላይ የዋሉ ዕቃዎች ጥቅም ላይ በዋሉበት ጊዜ ከፋብሪካው እንደወጡ ይቆጠራል፡፡
ለ) የኤክሳይዝ ታክስ የሚከፈልባቸውን ዕቃዎች ወደ አገር የሚያስገባ አስመጪ በሚከተለው ጊዜ የኤክሳይዝ ታክሱን የመክፈል ግዴታ አለበት፡-
• ሚኒስትሩ በሚያወጣው መመሪያ በልዩ ሁኔታ ካልፈቀደ በስተቀር የነዳጅ ምርቶች ወደ አገር በሚገቡበት ጊዜ፣
• ሌሎች ዕቃዎች ፣ ዕቃው ወደ አገር ሲገባ፣
ሐ) ለኤክስፖርት ምርቶች ማምረቻ የሚመረቱ ለአገር ውስጥ ፍጆታ እንዲውሉ ሲወጡ፣

24/06/2026

ተቀባይነት የሌለው የግብዓት ታክስ ተቀናሽ (በ1341/2016 መሠረት)

🔘በተጨማሪ እሴት ታክስ ለተመዘገበ ሰው ከዚህ በታች ለተዘረዘሩት የከፈለው የግብአት ታክስ ተቀናሽ አይደረግም፡-
▫️የተመዘገበው ሰው የመንገደኛ ተሽከርካሪ ግብይት ወይም ኪራይ ላይ የተሰማራ እና ተሽከርካሪው የተገዛው እና ፈቃድ የተሰጠው ለዚህ ታክስ የሚከፈልበት የሥራ እንቅስቃሴ ካልሆነ በስተቀር የመንገደኞች ተሽከርካሪ ግዥ ወይም ከእነዚህ ተሽከርካሪዎች መለዋወጫ ወይም ጥገና ወይም ዕድሳት ጋር በተያያዘ የከፈለው ታክስ፤
▫️ከዚህ በታች ከተመለከቱት በስተቀር፤ የተመዘገበው ሰው ለመዝናኛ ወይም የመዝናኛ አገልግሎት ለመስጠት ያከናወነው ግዢ ከሆነ፤ እና
የመዝናኛው አገልግሎት የተሰጠው ማናቸውም ሰው ታክስ የሚከፈልበትን መደበኛ የመዝናኛ አገልግሎት በሚሰጥበት ሁኔታ ከሆነ እና ✔️የመዝናኛ አገልግሎቱ ግንኙነት ላለው ሰው ወይም ለሰራተኛ የተሰጠ ካልሆነ፤
✔️የመዝናኛ አገልግሎቱ የተሰጠው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ስራውን ለማከናወን ወይም የቀጣሪውን ስራ ለማከናወን ከመኖሪያ ቤቱ ርቆ ባለበት ጊዜ ከሆነ፤ወይም
✔️ታክስ የሚከፈልበት የስራ እንቅስቃሴ የትራንስፖርት አገልግሎትን የሚያካትት ሆኖ የመዝናኛው አገልግሎት የትራንስፖርቱ አካል ሆኖ ለመገደኞች የተሰጠ ከሆነ፤
🔘በኢትዮጵያ ውስጥ ቋሚ የንግድ ሥራ ቦታ ሳይኖረው ታክስ የሚከፈልበት የንግድ ሥራ እንቅስቃሴ የሚያከናውን የተመዘገበ ሰው ከሚያከናውነው ታክስ የሚከፈልበት ግብይት ጋር በተያያዘ ማናቸውንም አይነት የግብአት ታክስ ተቀናሽ ሊያገኝ አይችልም፡፡

🔘ለታክስ ህጉ አፈጻጸም፣
▫️‹‹መዝናኛ›› ማለት ማናቸውም የምግብ፣ የመጠጥ፣ የመኝታ፣ የማዝናናት ወይም የመስተንግዶ አገልግሎት ነው፡፡
▫️‹‹የመንገደኛ ተሽከርካሪ›› ማለት ድርብ ጋቢና ያለውን ተሽከርካሪ ጨምሮ ከነአሽከርካሪው ስምንት ወይም ከዚያ በታች የሆኑ መንገደኞችን እንዲጭን ተደርጐ የተመረተ ወይም ማሻሻያ የተደረገበት ተሽከርካሪ ነው፡፡

Address

እንቁላል ፋብሪካ አካባቢ ቃሲም ሕንፃ ላይ
Addis Abeba
-

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Gullele Sub City Small Tax Payers Branch Office posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Shortcuts

Share