29/06/2026
።
በሳውዲ አረቢያ ለ13 ረጅም ዓመታት በጽኑ እስር ላይ ቆይታ የሞት ፍርድ ተበይኖባት የነበረችው እህታችን ለይላ ኑርሰቦ ረዲ ከእስር ተፈትታ ዛሬ በትውልድ ሀገሯ ምድር አዲስ አበባ ስትገባ የታየው እጅግ ልብ የሚነካና በከፍተኛ ስሜት የተሞላው የቤተሰብ መገናኘት ትዕይንት መላውን ህዝብ በአንድነት ያስለቀሰና ያስደሰተ ታላቅ ተአምር ሆኗል።
ከአስራ ሶስት ዓመታት ረጅም ስቃይ ስጋትና መከራ በኋላ በአካል ተገናኝተው እናትና ልጅ እርስ በእርሳቸው ተቃቅፈው ያነቡት የእንባ ጎርፍ፣ "አትሙቺ ያላት ነፍስ አትሞትም" የሚያሰኝና የፈጣሪን ታላቅነት በግልጽ ያሳየ እውነተኛ አስገራሚ አጋጣሚ ነው።
ይህ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው እና በአሁኑ ወቅት እውን የሆነው እጅግ ስሜት ቀስቃሽ የምስራች በሰላም ወደ እናቷ ሙቅ ጉያ በመመለሷ ሁላችንም በታላቅ እፎይታና ደስታ “እግዚአብሔር ይመስገን” ብለን የተቀበልነው ታላቅ ክስተት ነው።
ይህንን የመሰለ ታላቅ ሰብአዊና ብሔራዊ ስኬት በድል ለማጠናቀቅ የተቻለው በሪያድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባደረገው ተከታታይነት ያለው ሰፊ የዲፕሎማሲ ጥረት ብቻ ሳይሆን፣ ከተጎጂው ወገን ቤተሰቦች ጋር በተደረገው ሰፊ የእርቅ ሂደትና መከፈል የነበረበት የካሳ ክፍያ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ በመፈጸሙ ነው።
በዚህ እጅግ አስቸጋሪና ሌሊትና ቀን በተሰራበት አገራዊ የልፋት ውጤት ላይ የበኩላቸውን ታላቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱት የኮሚቴ አባላት፣ ለሀገር ሽማግሌዎች፣ ለሃይማኖት መሪዎች፣ ለሚዲያ ባለሙያዎች እንዲሁም በአንድነት ለቆሙት መላው ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ኤምባሲው የላቀ ምስጋናውንና አክብሮቱን አቅርቧል።
እኛም ለዚህ ሰብአዊ ትብብር ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ አብረው ለቆሙት ወገኖቻችን ሁሉ ያለንን ታላቅ አክብሮት እየገለጽን፣ የእህታችን የለይላ ኑርሰቦ በሰላም አገር ቤት መግባት የተባበረ ክንዳችን ውጤት በመሆኑ ለሁላችንም እንኳን ደስ አለን እንላለን።