17/08/2026
ለውጤታማ የመማር ማስተማር ሥራ ትምህርት ቤቶችን ዝግጁ ከማድረግ ጀምሮ ብቁና ተወዳዳሪ ተማሪዎችን ለማብቃትም ከወዲሁ ልሰራ እንደሚገባ ጥሪ አቀረቡ፦ ኢንጂነር በኃይሉ አጎናፍር
ነሐሴ 11/2018 ዓ.ም (ላስካ ኮሙኒኬሽን)
በላስካ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ካሉ ርዕሰ መምህራን እና ሱፐርቫይዘሮች እንዲሁም ከትምህርት አመራሮች ጋር የ2019 የትምህርት ዘመንን ውጤታማ ማድረግ ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሄደ።
የላስካ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢንጂነር በኃይሉ አጎናፍር ለውጤታማ የመማር ምስተማር ሥራ ትምህርት ቤቶችን ዝግጁ ከማድረግ ጀምሮ ብቁና ተወዳዳሪ ተማሪዎችን ለማብቃትም መምህራን፣ የተማሪ ወላጆች፣ ተማሪዎች እና የትምህርት አመራሮች ከወዲሁ በቅንጅት ልሰሩ እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
ምቹ የትምህርት ከባቢን ከመፍጠር እና በትምህርት ቤቶች የትምህርት ቁሳቁሶችን ከማሟላት ረገድ የህብረተሰብ ተሣትፎ በእጅጉ እንደሚያስፈልግ ያመላከቱት ከንቲባው ለውጤታማነቱም በጋራ ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
አክለውም የተማሪዎችን ውጤት በማሻሻል ሂደት የአንበሳውን ድርሻ የሚወጡት መምህራን ከዕቅድ ዝግጅት ጀምሮ በቂ ዝግጅት ማድረግና የማጠናከሪያ ትምህርቶችንም በመስጠት የነገዋ ሀገር ተረካቢ ዜጋን የመቅረጽ ኃላፊነታቸውን በተገቢው እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚቀላቀሉ ተማሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ መምጣቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ያወሱት ከንቲባው በዘንድሮው የትምህርት ዓመት የሚመዘገበውን ውጤት በማላቅ የተማሪዎችን መጻዕ ዕድሎቻቸውንም ብሩህ ማድረግ እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል።
የላስካ ከተማ አስተዳደር ትምርት ቤቶች ዩኒት አስተባባሪ አቶ አንተነህ አጥናፉ ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ጀምሮ የመጀመሪያና መካከለኛ ደረጃ፣ የልዩ ፍላጎት እንዲሁም ተግባር ተኮር የጎልማሳዎች ትምህርት ብሎም በአማራጭ መሠረተ ትምህርት በመደበኛ እና መደበኛ ባልሆኑ የሚማሩ ተማሪዎችን ለመቀበልና ምዝገባ አካሂዶ ወደ መማር ማስተማር ሥራ ለመሰማራት ትምህርት ቤቶች ከወዲሁ እንዲዘጋጁም ጥሪ አቅርበዋል።
በትምህርት ቤቶች እየተስተዋለ የሚገኘውን መጠነ ማቋረጥን ለማስቀረት አስመላሽ ኮሚቴዎችን በየትምህርት ቤቶች ከማደራጀት በዘለል ወደሥራ ማስገባት እንደሚጠበቅ ያወሱት አቶ አንተነህ የመጠነ መድገምን ቁጥር ዝቅ ለማድረግም በየትምህርት ክፍሉ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የግብ ስምምነቶችን መልሶ ማጤን እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በ2019 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ስራው ከመስከረም 05/2019 ዓ.ም ጀምሮ በይፋ እንደሚጀምር ያስታወቁት የዩኒት አስተባባሪው የምዝገባ ሂደቱም በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ከነሃሴ 13/2018 ዓ.ም ጀምሮ አስከ ጳጉሜ 05/2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ ታውቆ ተማሪዎች በጊዜ እንዲመዘገቡም ጥሪ አቅርበዋል።
የውይይት መድረኩ ተሣታፊዎችም በዘንድሮው የትምህርት ዘመን የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ከማሻሻል ጀምሮ የተማሪዎችን ውጤት ለማላቅም አስቀድሞ ውይይት መካሄዱ በተማሪዎች ውጤት መሻሻል ላይ ማነቆ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ቀን ሳለ ለመረባረብ ምቹ ምህዳር የሚፈጥር መሆኑን አስታውቀዋል።
ነሃሴ 11/2018 ዓ.ም
ላስካ