07/09/2026
"የክልሉ ቤተ መንግስት መላው የክልላችንን ህዝብ ሊወክል እና ሊመጥን በሚችል መልኩ ተገንብቷል"- ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
ጳጉሜን 02/2018 ዓ.ም
ግንባታው በዘጠኝ ወራት ዉስጥ የተጠናቀቀው የክልሉ መንግስት ቤተ-መንግስት ተመርቆ በክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተጎብኝቷል።
በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የቤተ መንግስት ግንባታው መላው የክልሉን ህዝብ ሊወክል እና ሊመጥን በሚችል እንዲሁም ባህላዊን ከዘመናዊ ዲዛይን ባጣመረ መንገድ ተግንብቶ መጠናቀቁን ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስት የተቋማት የህንፃ ግንባታ ፕሮጀክት ባጠረ ጊዜ መጠናቀቅ ክልሉን በፅኑ መሠረት ላይ ከማኖር ባለፈ፤ በስድስቱም ክላስተር ማዕከላት የተቋማት ህንፃ ግንባታዎችን በማስጀመር ግንባታቸው በጥራትና በፍጥነት እንዲጠናቀቅ በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።
ግንባታው በዘጠኝ ወር ተጠናቆ ለዚህ እንዲበቃ የብዙዎች እጅ ያረፈበት መሆኑን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ ለአንጆ ኑስ ኮንስትራክሽን ፣ ለክልሉ ግንባታ እና ዲዛይን ቁጥጥር ባለስልጣን፣ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን እንዲሁም እገዛ ላደረጉ አካላት በሙሉ የላቀ ምስጋና አቅርበዋል።
በመጨረሻም የቤተ መንግስቱን ምረቃ ምክንያት በማድረግ ለክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ ከወላይታ ዞን እና ከወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር የክብር ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።