01/09/2026
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ክልላዊ የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነት የማረጋገጥ የ10ኛ ሳምንት ተግባራትን በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫዎች አስቀመጡ
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ክልላዊ የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ለማብሰር በመንግስት እና ፓርቲ አመራር በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች በመከናወን ላይ የሚገኙ የ10ኛ ሳምንት ተግባራት ያሉበት ደረጃን በበይነ መረብ በመገምገም ለታለመው ግብ ስኬት ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል፡፡
በስብሰባው የክልሉ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ወገኔ ቡዙነህ፤ በክልሉ የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ሳምንታዊ አፈጻጸም የተመለከተ ዝርዝር ሪፖርት አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይቱ፤ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ክብርና ሉዓላዊነት በመሸጋገር በክልሉ በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች በመከናወን ላይ ባሉ ተግባራት የ10ኛ ሳምንት አፈጻጸም መሻሻሎች መኖራቸውን ገልፀው ፤ ዕቅዱን ለማሳካት ከተቀመጠው የጊዜ ሰለዳ እና በክልሉ ካለው አቅም አንጻር አሁንም በየመዋቅሩ ብዙ መስራት እንደሚገባ በአጽንኦት ገልፀዋል፡፡
አመራሩ የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተያዘው ሀገራዊና ክልላዊ ግብ፤ አንገብጋቢና የማይቀር የሉአላዊነት ጉዳይ መሆኑን በውል ተገንዝቦ የተጀመሩ ተግባራትን ብዝኃ ታታሪነትን ተላብሶ በሙሉ ትኩረት በቁርጠኝነት በመምራት ከግብ ማድረስ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት በክልሉ በራስ አቅም የሰብዓዊ ድጋፍ መሸፈን የሚያስችል አቅም ለመገንባት በመደረግ ላይ ያለው ርብርብ የሚያግዝ የተሻሻለ የአደጋ ጊዜ መጠባበቂያ ፈንድ ደንብ ማፅደቁን ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ደንቡን በሁሉም ደረጃ በአግባቡ ገቢራዊ በማድረግ ለውጤት ማብቃት እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
ለዚህም ደንቡን ወደ ተግባር ለመቀየር በክልል ደረጃ የተጀመሩ የህብረተሰብ ውይይቶችን በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች ተደራሽ በማድረግ፤ ለታለመው የአደጋ ጊዜ የመጠባበቂ ፈንድ የሚውል ገንዘብ በአፋጣኝ ከዚህ ወር ጀምሮ የማሰባሰብ ስራውን መጀመር እንደሚገባ አስምረዋል።
የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ አጀንዳው የመላው ህዝብ የጋራ አጀንዳ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ሀብት በማሰባሰቡ ሂደት አመራሩ፣ የመንግስት ሠራተኛው፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የልማት ድርጅቶች፤ የሀይማኖት ተቋማት፣ የንግዱ ህብረተሰብ፤ አርሶና አርብቶ አደሩን ጨምሮ ሁሉም የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ ማድረግ በሚያስችል አግባብ ማስፈጸም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ የተያዘው ግብ በየደረጃው ያለው አመራር የመምራት፤ የመፈፀምና የማስፈፀም አቅሙ የሚለካበት ጭምር መሆኑን ተረድቶ፤ ለስኬቱ በመፍጠንና መፍጠር መሪህ በከፍተኛ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት መመራትና መፈፀም እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
የሰብዓዊ ድጋፍን ከማረጋገጥ ተግባራት ጎን ለጎን ከኢሊኖ ክሰተት ጋር ተያይዞ የአየር ንብረት ለውጥ በምርታማነት ላይ የደቀነውን ፈተና እና በሰውና በእንስሳት ጤና ላይ ልያስከትል የሚችለውን ጉዳት ለመከላከልና ለመቀነስ የሚያስችል የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎችን መስራት እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል።
ከአየር መዛባት ችግር ጋር ተያይዞ በሁሉም አካባቢዎች በፍጥነት ለሚደርሱ ሰብሎች ትኩረት ሰጥቶ መስራት እና የመጠባበቂያ እህል ክምችት ስራዎችን በአግባቡ መምራት እንደሚገባም አክለዋል።
ተረጂዎችን ከማሻገር ጋር በተያያዘ በማህበረሰብና በቤተሰብ ደረጃ የጠራ የብዝነስ ዕቅድ ነድፎ ለአንድ ተጎጂ አንድ የስራ እድል የመፈጠር ግብን በማሳካት እና መሰረታዊ ችግሮችን በመፍታት ከችግር ለመሻገር መስራት እንደሚገባም ገልፀዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በመጨረሻም በክልሉ ተረጂነትን በማስቀረት የሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም መሸፈን የሚያስችል ተቋማዊ አቅም ለመገንባት በመከናወን ላይ ያሉ ተግባራት ጠንካራ ጎኖችን አጠናክሮ ማስቀጠል እና ክፍተቶችን ለይቶ በትኩረት በመስራት ለማሳካት የሚያስችሉ ቀጣይ አቅጣጫዎች በማስቀመጥ ሃሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡
የክልሉ ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ ገብረመስቀል ጫላ በበኩላቸው፤ የተረጂዎችን መረጃ ከማጥራት እና ከፋይዳ የዲጂታል መታወቂያ ጋር ከማስተሳሰር አኳያ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት በሁሉም መዋቅሮች መቶ በመቶ በማጠናቀቅ ዜሮ ማድረስ መቻሉ አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።
አክለው እንደ ክልል ለተያዘው ግብ ስኬት በየደረጃው ባለው አመራር የሚታዩ የወጥነትና የቁርጠኝነት ክፍተቶችን በፍጥነት በማረም፤ ተግባራትን በከፍተኛ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት መምራትና ለላቀ ውጤት መትጋት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ርዕሰመስተዳድርጽቤት