06/08/2026
የታሪክ፣ የሕግ እና የፍትሕ በር፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ
ሐምሌ 30/2018 ዓ.ም
130 ሚሊዮን ሕዝብ መተንፈሻዉን በጎረቤት አገራት ፈቃድ ላይ አንጠልጥሎ ሊቀጥል ይችላልን? የባሕር በር አልባነት የተፈጥሮ ዕጣ ፈንታ ነው ወይስ ሉዓላዊነትን የሚጎዳ የማይታይ የጂኦፖለቲካ ማዕቀብ?
የዓለም አቀፉን የሕግ ማዕቀፍ እና የጂኦፖለቲካዊ አሠራር ስንመለከተዉ የተባበሩት መንግሥታት የባሕር ሕግ ኮንቬንሽን (UNCLOS) በክፍል 10 ስር ለባሕር በር አልባ አገራት የሰጠውን መብት በሰፊው ያትታል። በተለይም አንቀጽ 125(1) እነዚህ አገራት የዓለምን ውቅያኖሶች ሀብት ለመጋራት እና መብታቸውን ለማስከበር "ወደ ባሕር የመድረስ መብት እና የመተላለፊያ ነፃነት" እንዳላቸው የማያሻማ ድንጋጌ አስፍሯል።
ከዚህም ባሻገር አንቀጽ 127 በመተላለፊያ (ትራንዚት) አገራት ላይ ከሚጣል የጉምሩክ ቀረጥ ነፃ የመሆን እንዲሁም አንቀጽ 131 በማሪታይም ወደቦች ላይ የባሕር በር ካላቸው አገራት መርከቦች ጋር እኩል የመስተናገድ መብት ይሰጣቸዋል።
ይሁን እንጂ በተግባር የባሕር በር ባለቤት የሆኑ አገራት ጂኦግራፊያዊ ብልጫቸውን እንደ ፖለቲካዊ ጫና ማሳረፊያ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። በዚህም ምክንያት የባሕር በር ባለቤት ያልሆኑ ሀገራት በከፍተኛ የትራንስፖርት ወጪ፣ በማያቋርጥ የዋጋ ግሽበት እና በኢኮኖሚያዊ ጥገኝነት ይሰቃያሉ።
የዓለም የውሃ ሀብት የሁሉንም አገራት ብልጽግና ማረጋገጥ ሲገባው ይህ መዋቅራዊ የፍትሕ መጓደል አዳጊ አገራትን ከዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ከማድረጉም ባሻገር፣ ብሔራዊ ደህንነታቸውን አደጋ ላይ ይጥላል።
የኢትዮጵያ የእስካሁኑ ጉዞ ይህንን ግዙፍ መዋቅራዊ ጫና በተሳሳተ ትርክት ሸፋፍኖ ማቆየት ነበር። ለዓመታት "ስለ ቀይ ባሕር መናገር ግጭት መጋበዝ ነው" በሚል ፍርሃት ሀገራችን ታሪካዊ፣ ጂኦግራፊያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ስነ-ልቦናዊ ትስስር ያላትን የቀይ ባሕር መብት ጥያቄ እንደ ነውር ስትቆጥረው ቆይታለች።
ነገር ግን የሕዝብ ቁጥሯ 130 ሚሊዮን በደረሰበት በዚህ ዘመን፣ ይህ ግዙፍ ማኅበረሰብ በጂኦግራፊያዊ እስረኝነት ታፍኖ መኖር አይችልም፤ በተፈጥሯዊ ሂደትም መተንፈሻ መፈለጉ አይቀሬ ነው።
የሌሎች አገራት የሕልውና መሠረት የሆነው የዓባይ ወንዝ ጉዳይ የዓለም አጀንዳ ሆኖ ሳለ፣ የኢትዮጵያ የሕልውና መሠረት የሆነው የቀይ ባሕር ጉዳይ እንዳይነሳ የሚደረግበት የጂኦፖለቲካዊ ግብዝነት ዛሬ ላይ ፈጽሞ ተሰብሯል።
ይህ የኢትዮጵያ አዲስ የእይታ ለውጥ ወደብ ከመጠቀም ባለፈ በዓለም አቀፉ የባሕር ሕግ (UNCLOS) የተረጋገጠውን በማሪታይም የኢኮኖሚ ዕድሎች፣ በአካባቢ ጥበቃ እና በቀጠናው የባሕር ደህንነት ላይ እኩል ተሳታፊ የመሆን ተፈጥሯዊ ሉዓላዊ መብትን የማስከበር ሐቀኛ ጉዞ ነው።
ስለሆነም ቀጣይ መሆን የሚገባው የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ እርምጃ፣ ይህንን ሕጋዊ ጥያቄ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር በአዲስ የትብብር እና የጋራ ፋይናንስ ማዕቀፍ ማስተሳሰር ነው።
ኢትዮጵያ የባሕር በር የሌላቸው አገራት የሚያጋጥማቸውን ጫና ለመቀነስ በጋራ ኢንቨስትመንት ላይ የተመሠረተ "የማይበጠስ የጥቅም ውህደት" መፍጠር አለባት።
የባሕር በር ባለቤት መሆናችን ለጎረቤት አገራት ዋስትና እንጂ ስጋት አለመሆኑን በተግባር ለማሳየት፣ የውስጥ አንድነት ከምንም ነገር በላይ ወሳኝ ነው።
ስለዚህም አሁን እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ ምክክር የውስጥ ፖለቲካዊ መግባባታችንን በማጽናት፣ ጂኦግራፊያዊ ዕጣ ፈንታችንን በሰላማዊ እና ምክንያታዊ ድርድር እንድንቀይር የሚያስችለን የጸና መሠረት ነው።
የባሕር በር ጥያቄያችን የማንም ችሮታ ሳይሆን፣ ትውልድ እንዳይታፈን በጋራ የምንከፍተው የታሪክ፣ የሕግ እና የፍትሕ በር ነው!