26/08/2026
በጋሞ ዞን የቆጎታ ወረዳ ህዝብ ምክር ቤት በ17ኛ በመደበኛ ጉባኤ የወረዳውን የ2019 ዓ.ም በጀት 321,106,326 ብር በማጽደቅ አጠናቀቀ።
ነሐሴ 20/2018 ዓ.ም
የቆጎታ ወረዳ ህዝብ ምክር ቤት 4ኛ ዙር መርሐ ግብር 13ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 17ኛ መደበኛ ጉባኤ የወረዳውን የ2019 ዓ.ም በጀት 321,106,326 ብር በማጽደቅ አጠናቅቋል።
በጉባኤው የወረዳው የልማትና የአገልግሎት ስራዎች አፈፃፀም በስፋት ተመላክተዋል።
በተለይም በግብርና ምርታማነት፣ በገቢ አሰባሰብ፣ በከተማ ልማት፣በጤና ፣በትምህርት ፣ በስራ ዕድል ፈጠራና በሌሎችም ዘርፎች የተከናወኑ ስራዎች አፈፃፀም ሪፖርትን የቆጎታ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አየለ ቱንጄ አቅርበዋል።
በቀረበው ሪፖርት ከምክር ቤት አባላት ጥያቄና አስተያዬት የቀረበ ሲሆን በቀረቡ ጥያቄዎችና አስተያየቶች አስተዳዳሪው ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚህም በከተማ ልማት የመንገድ፣መብራት እና በሌሎችም መሠረተ ልማት ስራዎች ጥሩ አፈፃፀም የተመዘገበባቸው መሆኑን ገልፀዋል።
በግብርና ዘርፍ ምርታማነትን ለማሳደግ የተወሰዱ ርምጃዎችና የአርሶ አደሩን የምርት አቅም ለማሳደግ የተደረጉ ጥረቶች እንደ ጥሩ ውጤት የሚወሰዱ ናቸው ብለዋል።
በገቢ አሰባሰብም የገቢ መሠረትን ማስፋትና የሚሰበሰበውን ገቢ ማሳደግ ረገድ መሻሻሎች መኖራቸው ገልፀው የገቢ ስራን ውጤታማ ለማድረግ በቅንጅት መስራት የሚያስፈልግ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በትምህርት ዘርፍ የተማሪዎችን ተሳትፎና የትምህርት ጥራት ለማሻሻል የተደረጉ ስራዎች አበረታች ውጤት የተመዘገበባቸው እንደሆነ በመጠቆም በተማሪ መጠነ መድገም ሁሉም የጋራ ኃላፊነትን መወጣት የሚገባ መሆኑን አሳስበዋል።
በጤና ዘርፍ የማህበረሰብ ፋርማሲ ግንባታና አገልግሎት ማስጀመር ፣የእናቶች ማቆያ እና ሌሎችም ተግባራት የተሻለ አፈፃፀም የተመዘገበባቸው መሆኑን አመላክተዋል
በስራ ዕድል ፈጠራም ወጣቶችን ወደ ስራና ምርታማነት ለማስገባት የተወሰዱ ተግባራት ለውጥ የታዬባቸው ሲሆን በቀጣይም ወጣቶችን በተለያዩ ዘርፎች ውጤታማ ለማድረግ የሚሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በማጠቃለያቸውም የግብርና ምርታማነትን ይበልጥ ማሳደግ፣ የገቢ አሰባሰብን ማጠናከር፣ የከተማ ልማት ስራዎችን በዕቅድና በጥራት ማስፈፀም፣ የትምህርት ጥራትን ማሻሻል እና የስራ ዕድል ፈጠራን በማስፋት ወጣቶችን በተሻለ ሁኔታ ተጠቃሚ ማድረግ እና በሌሎች ዘርፎችም የተያዙ ዕቅዶች በተግባር እንዲፈፀሙ ፣የህዝብ ተሳትፎ እንዲጠናከርና የልማት ስራዎች በቁርጠኝነት ለመፈፀም የሚሰራ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል።
በመጨረሻም የቆጎታ ወረዳ ፍርድ ቤት የ2018 አፈፃፀምና የ2019 በጀት ዕቅድ ቀርቦ ሀሳብ አስተያዬት ተሰጥቶበታል።
በተጨማሪም የቆጎታ ወረዳ 2019 ረቂቅ በጀት በቆጎታ ወረዳ ኢኮኖሚ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ በሆኑት በአቶ ተምበሮ ቴሮ የቀረበ ሲሆን 321,106,326 ብር ሆኖ ለምክር ቤቱ ቀርቧል።
የቀረበውን ረቂቅ በጀት ለተቋማት በተሸነሸነው በጀት ዝርዝር መነሻ የቆጎታ ወረዳ ም/ አስተዳዳሪና ፋይናንስና ፕላን ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ደስታ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
በዚህም የ2019 የወረዳው በጀት 321,106,326 ብር በምክር ቤት አባላት ፀድቆ ጉባኤው ተጠናቅቋል።
Gamo Zone People's Council Office - የጋሞ ዞን ህዝብ ምክር ቤት ጽ/ቤት