07/09/2026
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ አለምነሽ ደመቀ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ
ውድ የቢሯችን አመራሮች፣ መላው የገቢዎች ባለሙያዎች እና የክልላችን ግብር ከፋዮች!
በመጀመሪያ በ2018 በጀት ዓመት በተለያዩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ኢኒሼቲቮች በተደረገው ከፍተኛ እንቅስቃሴና በተመዘገበው የላቀ የሥራ አፈጻጸም፣ ተቋማችን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ የክልሉ ከፍተኛ የእውቅና ሽልማትና የመኪና ተሸላሚ በመሆኑ የተሰማኝን ወሰን የሌለው ደስታና ኩራት ለመግለጽ እወዳለሁ።
ይህ ድል በአጋጣሚ የተገኘ ሳይሆን፣ የመላው የተቋማችን ሰራተኞች እና አመራሮች የቀን ከሌሊት የጽናት፣ የትጋትና የተቀናጀ ሥራ ግልጽ ጥረት ውጤት ነው። በየደረጃው የሚገኙ የመዋቅራችን አባላት ያለመታከት ያሳያችሁት የባለቤትነት ስሜት፣ ከፍተኛ የሙያ ሥነ-ምግባር እና ለአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ያደረጋችሁት ያልተቆጠበ ጥረት ለዚህ ታላቅ ስኬት አብቅቶናል።
በተጨማሪም የዚህ ታላቅ ስኬት ባለቤቶች የሆናችሁ፦
👉 ታማኝ ግብር ከፋዮቻችን የክልላችንን ልማትና እድገት በመደገፍ ግብራችሁን በወቅቱና በትክክል በመክፈል የዜግነት ግዴታችሁን ስለተወጣችሁ ፤
👉 ባለድርሻ አካላትና የክልሉ ስለተወጣች ለተቋማችን ስኬት አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ስላደረጋችሁልን፤
ላቀረባችሁልን ድጋፍና ላሳያችሁት አጋርነት በቢሮዬ እና በራሴ ስም የላቀ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።
ውድ የሥራ ባልደረቦቼ!
ይህ የተሰጠንም ከፍተኛ እውቅና እና የሽልማት ተሽከርካሪ ያለፉ ስኬቶቻችን ማክበሪያ ብቻ ሳይሆን፣ ለቀጣዩ የ2019 በጀት ዓመት የበለጠ እንድንሰራ፣ የተቀመጡ የገቢ እቅዶችን አበልጽገን እንድናሳካ እና ዘመናዊና ፍትሃዊ የገቢ አሰባሰብ ስርዓትን አጠናክረን እንድንቀጥል የተጣለብን ትልቅ ኃላፊነትና የቤት ሥራ ነው።
በቀጣይም ይህንን የተከበሬ የላቀ አፈጻጸም ባህል አድርገን በመቀጠል፣ ለክልላችን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ለህዝባችን ተጠቃሚነት በጋራና በጠንካራ መንፈስ እንደምንሰራ ሙሉ እምነት አለኝ።
በድጋሚ እንኳን ደስ አለን!
ወ/ሮ አለምነሽ ደመቀ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ