17/08/2026
የሲዳማ ክልል ሥነ-ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በተጠናቀቀዉ በጀት ዓመት ከ38 ሚሊዮን ብር በላይ ከምዝበራ ማዳኑን አስታወቀ።
ነሀሴ 11/2018ዓ.ም
ሀዋሳ
የሲዳማ ክልል ሥነ-ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የ2018 ዓ.ም የሥራ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 ዓ.ም እቅድ ዝግጅት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ወ/ሮ ዘላለም ለማ እንደተናገሩት፤ በበጀት ዓመቱ በመልካም ሥነ-ምግባር የታነጸ፣ ሙስናን የሚጠየፍ እና አጥብቆ የሚታገል ማኅበረሰብ በመገንባቱ ረገድ አበረታች ውጤት ተመዝግቧል።
ይህም በፀረ-ሙስና ትግሉ ውስጥ የላቀ የሕዝብ አጋርነት እንዲጎልበት ከማድረጉም በላይ በተቋማት ውስጥ የግልጸኝነትና የተጠያቂነት አሠራርን በማስፈን በሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ይታዩ የነበሩ ብልሹ አሠራሮችን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ማስቻሉን ገልጸዋል።
ኮሚሽነር ዘላለም አክለውም ከህዝብ የደረሱ ጥቆማዎችን በከፍተኛ ትኩረትና ጥንቃቄ በማስተናገድ አግባብነት ላላቸው አካላት በማቅረብ ከፍተኛ ሀብት ከምዝበራ ማዳን መቻሉን ተናግረዋል።
አያይዘውም ሌብነትንና ያለአግባብ ሀብት ማካበትን ለመታገል በሚደረገው እንቅስቃሴ፣ ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ባፈሩ ግለሰቦች ላይ መረጃዎችን አደራጅቶ ወደ ሕግ የማቅረቡ ሂደት አሁንም መሻሻል የሚገባቸው ክፍተቶች እንዳሉበት ገልጸው፤ ከዚህ አንጻር የኮሚሽኑ ሠራተኞች በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በሌላ በኩል በኮሚሽኑ የእቅድና በጀት ዝግጅት፣ ክትትል እና ግምገማ ዳይሬክተር አቶ በላይ ባንጋሳ የቀረበው ሪፖርት እንደሚያመለክተው፤ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ለ205,600 የሕብረተሰብ ክፍሎች በሥነ-ምግባር፣ በሙስና ወንጀል ጎጂነት እና በትግል ስልቶች ዙሪያ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ተሰጥቷል።
በተጨማሪም በክልሉ በሚገኙ መንግሥታዊና ሕዝባዊ ተቋማት የሚታዩ የአሠራር ክፍተቶችን በጥናት በመለየት፣ በ4 ቁልፍ የልማት ዘርፎች ላይ ያተኮሩ ጥናቶች ተካሂደው ከተጠኚ ተቋማት ጋር የስምምነት ሰነድ በመፈራረም ወደ ትግበራ ተገብቷል ነዉ ያሉት።
የመንግሥት ሠራተኞችና ተሿሚዎች ሀብት ንብረታቸውን እንዲያስመዘግቡ በማድረግ የጥቅም ግጭትን ለመከላከልና የአገልግሎት አሰጣጥን በግልጽነት ለመምራት በተከናወነው የሀብት ምዝገባ ሥራ 5,463 ግለሰቦች ሀብታቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ ያስመዘገቡ ሲሆን፣ የ89,790 ግለሰቦች ደግሞ እንዲታደስ ተደርጓል ስሉ አብራርተዋል፡፡
ዳይረክተሩ አክለውም በበጀት ዓመቱ ከሕዝብ የቀረቡ 711 ጥቆማዎችን መነሻ በማድረግ በተደረገ አስቸኳይ የቅድመ-መከላከል እንቅስቃሴ 38,427,726.3 ብር ከምዝበራና ከብክነት ማዳን መቻሉን ገልፀዋል።
በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ በበጀት ዓመቱ የታዩ ጉድለቶችን በማረም የ2019 ዓ.ም ዕቅድን በላቀ ቅንጅት ለማስፈጸም የሚያስችል የጋራ አቅጣጫ ተቀምጦ መድረኩ ፍጻሜ አግኝቷል።
ለፈጣንና ወቅታዊ መረጃዎች
Email
[email protected]
WhatsApp
https://chat.whatsapp.com/KCvsTVV91bXLhSCNFmYd9I?mode=gi_t
YouTube
https://www.youtube.com/
Telegram
https://t.me/+2d8PjI0EYkQ5OTdk
Tikitok
https://www.tiktok.com/.ethics.acc?_r=1&_t=ZS-94chEynKxkG
ወደ ቢሮአችን በአካል ለመምጣት ከታች ያለውን የጎግል ማፕ መገኛ ይጠቀሙ።
https://maps.app.goo.gl/zTQ44e3nCqy5qEMC7?g_st=atm