22/08/2026
እንኳን ደስ አለን !
ታርካዊዉ ሀገራዊ ምክክር ለሀገራዊ መግባባት በኢትዮጵያ አሸናፊነት በድል በሰላም ተጠናቀቀ።
ከጅምር እስከ ማጠናቀቅ ሂደት የረዳን ልዑል እግዝአብሔር የተመሰገነ ይሁን !!
ለ45 ተከታታይ ቀናት በስምንት አጀንዳዎች በሰማንያ ሰባት ንዑስ አጀንዳዎች እና በ 243 መሪ ጥያቄዎች መነሻ 4000 ተመካካሪዎች ከ10 ጀምሮ እስከ 500 (ማለትም ጥቃቅን ቡድን ፣ ንዑስ ቡድን ፣ ስልታዊ ቡድን እና ስራ ቡድን ) በጥቃቅን ቡድን ሀሳብ ከማመንጨት እስከ ስራ ቡድን ከመጡበት አከባቢና ከወከሉት የህብረተሰብ ክፍል መሠረት በየአጀንዳዎቹ ምክክር በማድረግና በተነሱ ሀሳቦች ሁሉንም ሊያግባባ የሚችል የተሻለ አማካይ ምክረ ሀሳቦች ላይ በመግባባት በስምንቱም አጀንዳ በጠቅላላ ከ400 በላይ ምክረ ሀሳብችን ለምክክር ኮምሽኑ ማስረከብ ተችሎአል።
የምክክሩ ሂደትም እጅግ ሰላማዊ በተመካካሪዎች መካከል መደማመጥ እና መቀባበል የነበረበት አንዱ የአንዱን ሀሳብ በማክበር ፣ በየአከባቢዉ ያሉ ችግሮችን እንደ ጋራ ችግር በማዬት ሁሉንም የሚያግባባ የመፍትሄ ምክረ ሀሳብ በማምጣት በኢትዮጵያዊ ጨዋነት የተመራ ሂደት ነበር። ከሂደቱም ብዙ ትምህርት የወሰድንበት ነበር ።
ምክክሩ በመደመር ፍልስፍና መሠረት ኢትዮጵያ ለሀገራዊ መግባባት የዉስጥ ችግሯን በራሷ ልጆች ተመካክራ የመፍትሄ ምክረ ሀሳብ ማስቀመጥ የቻለች ታላቅ ሀገር መሆኗን ያስመሰከረችበት ታርካዊ ኩነት ነዉ ።
እኔም የዚህ ታርካዊ ምክክር ተሳታፊ የመሆን እድል አግኝቼ ከተመካካሪነት ባለፈ ከጥቃቅን ቡድን እስከ ስራ ቡድን የተመካካሪዎችን ምክረ ሀሳቦች ከወንድም እህቶቼ ጋር አጠናቃሪ በመሆን ታርካዊ ሀላፊነት ተሰጥቶኝ የድርሻዬን በመወጣቴ እጅግ ኩራት ይሰማኛል ።
የነገዋ ኢትዮጵያ ለጠላት የማትመች ዜጎቿ በጥቃቅን አጀንዳዎች የሚነቋቆሩባት ሳትሆን የምክክር የሰላምና የብልፅግና ተምሳሌት ሀገር እንደምትሆን ትልቅ ተስፋ አለኝ !
ተስፋን የሰጠን እግዝአብሔር የታመነ ነዉ !
እግዝአብሔር ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ !!