04/09/2026
በሚሊዮን የሚቆጠር የህዝብና የሀገር ሀብት የዘረፉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ።
በደሴ ከተማ አስተዳደር በተደጋጋሚ የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመሮችን እና የቴሌኮሙኒኬሽን መሠረተ ልማት እቃዎችን ሲዘርፉ የነበሩ ግለሰቦች፣ ከተደበቁበትና ከቀበሩት ንብረት ጋር በቁጥጥር ስር ማዋሉን የደሴ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ከ4ኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ ጋር በመቀናጀት ባደረገው ጥብቅ የምርመራ ስራ፣ በአንድ ግቢ ውስጥ ተበታትነውና ተደብቀው ይገኙ የነበሩ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር የሚያወጡ የኃይል ማስተላለፊያ ትራንስፎርመሮች እና የቴሌ እቃዎች ሙሉ በሙሉ ተይዘዋል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ጥላሁን ታደሰ እንደገለጹት፣ የተፈጸመው ድርጊት ሀገርን ከማጥፋት የማይተናነስና ህዝብን ከሰላም አስከባሪው ለመነጠል የታለመ እኩይ ተግባር መሆኑን አንስተዋል።
መምሪያው ልዩ የምርመራ ቡድን አዋቅሮ ወደ ስራ በመግባቱ የተሳካ ውጤት መገኘቱን ጠቁመው፣ በተጠርጣሪዎች ላይ የሚደረገው ህጋዊ ማጣራት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
አዛዡ አያይዘውም ምርመራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና መረጃ በመስጠት ለዚህ ስኬት መገኘት ከፍተኛ ሚና ለተጫወተው ማህበረሰብና ድርጊት ፈፃሚዎችን አካላት ተከታትሎ በቁጥጥር ስር ላዋለው የፀጥታ ኃይሎችን ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል ።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ሠላም እና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ሠይድ አሊ በበኩላቸው፣ ሀገርንና ህዝብን ለማልማት የሚደረገውን ጥረት ለማደናቀፍ የተደራጀ የዘራፊዎች ቡድን በቁጥጥር ስር መዋሉ ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል።
ኃላፊው አክለውም ድርጊቱ ማንም አካል ከህግ እጅ ማምለጥ እንደማይችል የሚያሳይ በመሆኑ፣ ህብረተሰቡ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር የሚያደርገውን አጋርነት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደሴ ሪጅን ዳይሬክተር አቶ ሀብቱ አበበ፣ ከሐምሌ ወር ጀምሮ ተባብሶ የነበረውን የስርቆት ወንጀል በማስቆም የንብረት ውድመትን ለመታደግ ለተደረገው ከፍተኛ የትብብር ስራ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የሰሜን ምስራቅ ሪጅን ሴኩሪቲ ማናጀር ኮሎኔል ገዛህኝ አለባቸው በበኩላቸው፣ ተቋሙ ጉዳዩን ከአጋር የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት በልዩ ትኩረት እየተከታተለው እንደሚገኝ ገልጸዋል።