06/09/2026
የላቀ እምርታ፣ በምርታማነት ማንሰራራት የዘመናዊ ግብርና ምዕራፍ
ግብርና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መሠረት ብቻ ሳይሆን፣ የምግብ ዋስትና፣ የገቢ ምንጭና የዜጎች የኑሮ መሻሻል ዋነኛ መሠረት ነው። ይህን ዘርፍ ከባህላዊ አሠራር በማላቀቅ ወደ ዘመናዊ፣ ተወዳዳሪና ምርታማ ሥርዓት መለወጥ ደግሞ የዘመኑ ቀዳሚ ተግባር ነው።
ሀገራችን “የኢትዮጵያ ማንሰራራት” በሚል መሪ ቃል የምታከብራቸውን የጳጉሜን ቀናት መርሃ ግብር በይፋ ጀምራለች፣ “ጳጉሜ 1 የእምርታ ቀን” ሆኖ የሚከበር ሲሆን በዕለቱም በበጀት ዓመቱ በግብርናው ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶችን ከተረጅነት ወደ ምርታማነት የሚደረገውን ሽግግር የሚያጠናክሩ ስኬቶችን የምናጎላበት ወቅት ነው።
በክልላችን በ2018 በጀት ዓመት ከተመዘገበው 7.9 በመቶ ጠቅላላ የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ የግብርናው ዘርፍ ከ5.5 በመቶ በላይ ድርሻ ማበርከቱ፣ ዘርፉ ለክልሉ ምጣኔ ሀብት ዕድገት ያለውን ወሳኝ ሚና የሚያሳይ ሲሆን በበጀት ዓመቱ የተመዘገቡት አበረታች ስኬቶችም የዘርፉን የማንሰራራት ምዕራፍ በተግባር ያረጋገጡ ናቸው።
በዚህም የለውጥ ሂደት በክልላችን በ2017/18 የምርት ዘመን 188 ሚሊዮን ኩንታል እንዲሁም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 13 ሚሊዮን ኩንታል ምርት የተገኘ ሲሆን የግብርና ሜካናይዜሽንን ለማስፋፋት ከ978 በላይ የእርሻ ትራክተሮች ለአርሶ አደሮች መሰራጨቱ በዘመናዊ ግብርና የተገኙ ጉልህ አሻራዎች ናቸው።
በ2018/19 የምርት ዘመን 5.6 ሚሊዮን ሄክታር የሚታረስ መሬትን በመጠቀም 205 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት የተያዘው ግብ የምርታማነት ሽግግሩን የምርት አቅምን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ከማጠናከር ባሻገር የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማጽናት ጠንካራ መሠረት የሚፈጥር ነው።
የ25 ዓመቱ የአሻጋሪ ዕድገትና ዘላቂ ልማት ዕቅድ ለዘመናዊ ግብርና ከፍተኛ ትኩረት የሰጠ ሲሆን የዘርፉን ተዋናዮች ስምረት በማጠናከር ከፍጆታ የተሻገረ ለገበያና ለኢንዱስትሪ የሚሆን ምርት በማምረት የአርሶ አደሩን ገቢና የኑሮ ደረጃ ማሻሻል ዋና መዳረሻችን ነው።
ይህ ለውጥ በበጋ የመስኖ ስንዴ ልማት፣ በኩታገጠም እርሻ አሠራር፣ በሰፋፊና በተቀናጀ የፍራፍሬ ልማት እንዲሁም በሌሎች የምርታማነት ማሳደጊያ ሥራዎች በግልጽ እየታየ ነው። የምርት መጠንን ብቻ ሳይሆን ጥራትን፣ የገበያ ትስስርንና የአርሶ አደሩን ገቢ ማሳደግ ላይ የተመሠረተው አዲሱ አቅጣጫ የዘመናዊ ግብርናን ገቢራዊነት ያረጋገጠ ነው።
በመሆኑም የ“እምርታ ቀን” በግብርናው ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶችን የምናከብርበት ብቻ ሳይሆን፣ የተገኙትን ውጤቶች በማጠናከር የበለጠ ምርታማ፣ ተወዳዳሪ፣ ዘመናዊና ዘላቂ የግብርና ስርዓት ለመገንባት ትጋትንና ቁርጠኝነትን የምናረጋግጥበት ነው።
አቶ ደረጀ ማንደፍሮ
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኋላፊ