29/08/2026
"በአንድ እጅ ሰላም፣ በሌላኛው ልማት" ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
የአማራ ክልል ከፍተኛ እና መከካለኛ መሪዎች በተገኙበት የ2018 በጀት ዓመት የፓርቲ እና የመንግሥት ሥራዎች አፈጻጸም እና የ2019 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ በ2018 በጀት ዓመት ጥራት ያለው ዕቅድ መታቀዱን አስታውሰዋል። ዕቅዱን ስኬታማ ለማድረግ በየደረጃው የሚገኙ መሪዎች ቃል ኪዳን ገብተው ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጸዋል። በትኩረት በተሠራው ሥራ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውንም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በ2018 በጀት ዓመት በክልሉ የፖለቲካ መረጋጋት እና የፓርቲው ቅቡልነት ከፍ እንዲል ከፍተኛ ሥራዎች መተግበራቸውን ገልጸዋል። በጀት ዓመቱ የክልሉ ዋነኛ ችግር የኾነውን የፖለቲካ ጽንፈኝነትን የታገልንበት ነው ብለዋል።
ሀገራዊ ትስስርን ለማጠናከር የሚያስችሉ እሴቶችን የበለጠ ለማጎልበት የሀገራችን እና የክልላችን ሕዝብ የጋራ ርዕይ እንዲኖራቸው የሚያደርጉ ሥራዎች የተሠሩበት እና ሀገራዊ ምክክር በስኬት የተካሄደበት እንደነበርም ገልጸዋል። በጀት ዓመቱ ስኬታማ ምርጫ የተካሄደበት እንደነበርም አንስተዋል።
ሰላምን፣ ፍትሕን እና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል። ከውስጥ እና ከውጭ የተጣመሩ አካላትን ሀገር አፍራሽ አካሄድ ለመግታት ሰፊ ሥራ መሠራቱን ነው የተናገሩት።
በክልሉ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ተከትሎ የተከሰተውን የተደራጀ ወንጀል ለመግታት መሠራቱንም አንስተዋል። ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት መደረጉን ነው የገለጹት። በአንድ እጃችን ሰላም እያስከበርን፣ በሌላ እጃችን ደግሞ ልማት እያለማን ውጤታማ ተግባራትን ሠርተናል ነው ያሉት።
የኑሮ ውድነትን፣ ሥራ አጥነትን እና የኢኮኖሚ መዛባትን ለማስተካከል ተሠርቷል ብለዋል። በማኅበራዊ ዘርፍም ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል። በመልካም አሥተዳደር ዙሪያ ውጤታማ ተግባራት ተሠርተዋል፤ በተለይም የአገልግሎት አሠጣጥን ለማሻሻል በትኩረት ተሠርቷል ነው ያሉት። ገቢን ለማሳደግ ጥረት መደረጉንም ገልጸዋል።
ስኬታማ ሥራዎች እንደተከናወኑ ሁሉ ልናልፋቸው የማይገቡ ችግሮችም አሉ ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ። የክልሉን የጸጥታ ችግር ለማስተካከል ውጤታማ ሥራዎች ቢከናወኑም አሁንም ጠንካራ ሥራ መሥራት እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት። አወንታዊ ጉዳዮችን በማስፋት፤ ውስጣዊ እና ውጫዊ ተጋላጭነትን በመከላከል የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መሥራት ይገባል ብለዋል።
መሪዎች በመድረኩ በቂ ግንዛቤ በመያዝ በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
አዲሱ በጀት ዓመት መሠረታዊ ለውጥ የምናመጣበት መኾን አለበት ነው ያሉት።