19/08/2026
የደቡብ ወሎዞን መንገድ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ መምሪያ ከ839 ሺህ ብር በላይ የሚገመቱ የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደረገ፤
******
የደቡብ ወሎ ዞን መንገድ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ መምሪያ ባቀረበው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ጥሪ መሠረት፣ የአሽከርካሪ ማህበራትና የተሽከርካሪ ተቋማት ከ839 ሺህ ብር በላይ የሚገመቱ የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ አድርገዋል።
በዞኑ የሚገኙ ሰባት የትራንስፖርት ማህበራት ድጋፉን ማበራከታቸውን የገለጹት የለጎ ሐይቅ ከፍተኛ፣ መካከለኛና አነስተኛ ሕዝብ ማመላለሻ ባለሃብቶች ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ አስመሮው ባይህ፤ ለወላጅ አልባዎችና አቅም ለሌላቸው ወገኖች ድጋፍ ማድረግ በመቻላቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል።
አክለውም ማህበራቸው ከ600 ደርዘን በላይ ደብተርና እስክሪብቶ ማበርከቱን ገልጸው፣ ይህ ዓይነቱ የበጎ አድራጎት ተግባር በሁሉም ዘንድ ሊቀጥል እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
በተመሳሳይ የደሴ ከተማ የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋም ሰብሳቢ አቶ በዙነህ ሀይሌባህሩ በበኩላቸው፤ በማህበሩ ሥር የሚገኙ 10 ባለሃብቶች 100 ደርዘን ደብተርና 100 ደርዘን እስክሪብቶ ማበርከታቸውን ገልጸዋል።
የዘንድሮው ድጋፍ ከቀደሙት ዓመታት በይዘቱና በመጠኑ የተሻለ መሆኑን ጠቁመው፣ የትምህርት ቁሳቁስ መግዛት ለማይችሉ ወገኖች እጅ መዘርጋት የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የደቡብ ወሎ ዞን መንገድ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ መምሪያ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም አሰን፤ በተደረገው እንቅስቃሴ ከ600 ደርዘን በላይ ደብተርና ከ245 ባኮ በላይ እስክሪብቶ መሰብሰቡን አብራርተዋል።
የተሰበሰበው ቁሳቁስ በዞኑ አብይ ኮሚቴ አማካኝነት እስከ ወረዳ ድረስ ላሉ አቅመ-ደካሞችና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወገኖች ልጆች እንደሚሰራጭ ተናግረዋል።
ኃላፊው አክለውም፣ አሽከርካሪዎችና ተቋማት ባሉባቸው ችግሮችና ውጣ ውረዶች ውስጥ ሆነው ላደረጉት ወገናዊ ደጋፍና ለላቁት በጎ አድራጎት በመምሪያው ስም ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።
መረጃው የደቡብ ወሎዞን መንገድ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ መምሪያ ነው።