02/09/2026
የሕጋዊ ሥነ-ልክ ክልከላዎችን መተላለፍ የሚያስከትለው የሕግ ተጠያቂነት
🚫🚫🚫🚫🚫🚫🚫🚫🚫🚫🚫🚫🚫🚫🚫🚫🚫🚫🚫🚫
የወንጀል ቅጣት
በአዋጁ አንቀጽ 19/1 ስር እንደተደነገገው ማንኛውም ሰው ሌላውን ለመጉዳት ወይም ለራሱ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ በአዋጁ አንቀጽ ከተመለከቱት የመለኪያ አሀዶች እና የአሃዶች ብዜቶች ውጭ በመጠቀም ምርት ወይም አገልግሎት ሲሸጥ ከተገኘ ከብር 10,000 እስከ ብር 50,000 በሚደርስ መቀጮ ወይም ከ3 ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት የሚቀጣ ሲሆን ድርጊቱ የተፈፀመው ለሁለተኛ ጊዜ ከሆነ ቅጣቱ ከብር 51,000 እስከ 100,000 የሚደርስ መቀጮ ወይም ከ6 ወር እስከ 3 ዓመት የሚደርስ ቀላል እሥራት ይሆናል፡፡ ድርጊቱ የተፈጸመው በቸልተኛነት በሆነ ጊዜ ቅጣቱ ከብር 10,000 እስከ ብር 20,000 በሚደርስ መቀጮ ወይም ከስድስት ወር በማይበልጥ ቀላል እስራት የሚያስቀጣ ይሆናል (አንቀጽ 19(6))፡፡
ማንኛውም ሰው እያወቀ የመለኪያ መሣሪያዎችን ዓይነት ወይም ንድፍ ለንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አቅርቦ ሳያስጸድቅ እና የተስማሚነት የምስክር ወረቀት ሳይሰጠው ሲያመርት፣ ወደ ውጭ አገር ሲልክ፣ ወደ አገር ውስጥ ሲያስገባ ወይም ሲያከፋፍል ከተገኘ ከብር 100,000 እስከ ብር 250,000 በሚደርስ መቀጮ ወይም ከ6 ወር እስከ 3 ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ይቀጣል (አንቀጽ 19(2))፡፡ ድርጊቱ የተፈጸመው በቸልተኛነት በሆነ ጊዜ ከብር 10,000 እስከ 20,000 በሚደርስ መቀጮ ወይም ከ6 ወር በማይበልጥ ቀላል እስራት የሚያስቀጣ ይሆናል (አንቀጽ 19(6))፡፡
ማንኛውም ሰው ሌላውን ለመጉዳት ወይም ለራሱ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ በአዋጁ መሠረት የመለኪያ መሳሪያን ለትክክለኛነት ማረጋገጥ ሳያቀርብ አገልግሎት ሲሰጥ ከተገኘ ከብር 10,000 እስከ 20,000 በሚደርስ መቀጮ ወይም ከ3 ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ይቀጣል (አንቀጽ 19(3))፡፡ ድርጊቱ የተፈጸመው በቸልተኛነት በሆነ ጊዜ ከብር 10,000 እስከ ብር 20,000 በሚደርስ መቀጮ ወይም ከ6 ወር በማይበልጥ ቀላል እስራት የሚያስቀጣ ይሆናል (አንቀጽ 19(6))፡፡
ማንኛውም ሰው በሕግ ሥልጣን ሳይኖረው አስቦ የመለኪያ መሳሪያን የትክክለኛነት ማረጋገጫ ምልክት ካላቀቀ፣ በሌላ ከተካ ወይም የፕሎምብ እሽግን ከበጠሰ ከብር 150,000 እስከ ብር 300,000 በሚደርስ መቀጮ እና ከ1 ዓመት እስከ 5 አመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል (አንቀጽ 19(4))፡፡ ድርጊቱ የተፈጸመው በቸልተኛነት በሆነ ጊዜ ከብር 50,000 እስከ ብር 100,000 በሚደርስ መቀጮ ወይም ከ1 ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት የሚያስቀጣ ይሆናል (አንቀጽ 19(7))፡፡
ማንኛውም ሰው ለራሱ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ተገቢውን መግለጫ ሳያደርግ፣ በመግለጫው ላይ የተጣራ መጠን ሳይገልጽ፣ በመግለጫው ላይ ከተገለጸው ጋር በማይጣጣም ሁኔታ ወይም የይለፍ የምስክር ወረቀት ሳይሰጠው የታሸገ ምርት ሲያመርት፣ ሲያሽግ፣ ወደ ውጭ አገር ሲልክ፣ ወደ አገር ውስጥ ሲያስገባ፣ ለሽያጭ ሲያቀርብ ወይም በሌላ መንገድ ሲያስተላልፍ ከተገኘ ከብር 100,000 እስከ ብር 200,000 በሚደርስ መቀጮ እና ከ3 አመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ይቀጣል (አንቀጽ 19(5))፡፡ ድርጊቱ የተፈጸመው በቸልተኛነት በሆነ ጊዜ ከብር 50,000 እስከ 100,000 በሚደርስ መቀጮ ወይም ከ1 ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት የሚያስቀጣ ይሆናል (አንቀጽ 19(7))፡፡
ማንኛውም የሕጋዊ ሥነ-ልክ ኦፊሰር ወይም ጠጋኝ ለራሱያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ የመለኪያ መሳሪያን ወይም የታሸገ ምርትን ትክክለኛነት በዛባ ሁኔታ ካረጋገጠ ወይም ከጠገነ ከብር 50,000 እስከ ብር 100,000 በሚደርስ መቀጮ እና ከ3 አመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ይቀጣል (አንቀጽ 19(8))፡፡