የደቡብ ወሎ ዞን መስህቦች
ደቡብ ወሎ ዞን በምስራቅ አማራ የሚገኝ ሲሆን የቆዳ ስፋቱም 1,872,611 ሄክታር ነው፡፡ በምስራቅ አፋር ክልልና የኦሮሚያ ብሔረሰብ ዞን፣ በምዕራብ ምስራቅ ጎጃምና ደቡብ ጎንደር ዞን፣ በሰሜን ሰሜን ወሎ ዞንና በደቡብ ሰሜን ሸዋና ኦሮሚያ ክልል ያዋሰኑታል፡፡ በውስጡ 20 ወረዳዎች እና 3 የከተማ አስተዳደሮች አሉት፡፡
ደቡብ ወሎ ዞን ከ10.1°-11.43° ላቲቲዩድ ሰሜንና ከ38.29°.40.29° ሎንግቲዩድ ምስራቅ ባለዉ ጂኦግራፊያዊ ክልል ውስጥ የሚገኝ ሲሆን የመሬት አቀማመጡ ወጣ ገባነት የበዛት ነው፡፡ የአየር ንበረቱ 9.2% ቆላማ፣ 54.4% ወይናደጋ፣ 35.2 ደጋ እና 1.2% ዉርጭ ነዉ፡፡ የሙ
ቀት መጠኑ ደግሞ ከፍተኛው ከ20-27c° ዝቅተኛው ደግሞ ከ10 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በታች ይሆናል፡፡ ዓመታዊ የዝናብ መጠን 500-1,200 ሚ.ሜ ነው፡፡
ደቡብ ወሎ የቱሪስቶችን ቀልብ የሚስቡ በርካታ ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊ፣ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ቅርሶች ባለቤት ነዉ፡፡
የተለያዩ ብሔርሰቦችና የሃይማኖት ስርዓቶች ተዋደዉና ተከባብረዉ የሚኖሩበት፤ ኢትዮጵያ የምትታወቅባቸዉ 4 ባህላዊ የሙዚቃ ቅኝቶች ጭምር በዚህ ዞን ይገኛሉ፡፡
ደቡብ ወሎ በጥንት ዘመን አንቱ የተሰኙ የሃይማኖት ሙህራንና መሪዎች የተፈጠሩበት በመሆኑ ዛሬም የስራቸዉን ኃያልነት የሚያንጸባርቁ ምስክሮቻቸዉ በቋሚነት አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ስለሆነም የዘመኑን የስነ-ህንጻ ዕድገት ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ በርካታ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ተጠንተዉ እዉቅና ያልተሰጣቸዉ አብያተ ገዳማት፣ ቤተ-መንግስትና መስጅዶች፣ በብራና ላይ የተጻፉ የጽሁፍ መረጃዎች፣ ስዕሎችና ቅርጻቅርጾች፣ ንዋየ ቅድሳት፣ አልባሳት፣ የመገልገያ ቁሳቁሶች፣
ታሪካዊ ቦታዎች፣ የጦር ምሽግ፣ የጦር ሜዳ ታዋቂ ሰዎች መካነ -መቃብሮች እንዲሁም የበርካታ ተፈጥሯዊ የመሬት አቀማመጥ፣ ወንዞች፣ ሃይቆች፣ ተራሮች፣ ብርቅየ እንስሳት እጽዋት እንዲሁም ረቂቅ መስህቦች በስፋት የሚገኙበት ነዉ፡፡
የዞኑ ርዕሰ መድና ደሴ የመቻቻልና የዉቦች አገር ከአዲስ አበባ 401 ኪ.ሜ በኢትዬጲያ ሰሜን ምስራቅ ክፍል ከባህር ጠለል በላይ በ11° 05‘ ሰሜን ኬክሮስና ለ39°40‘ ምስራቅ ኬንትሮስ ላይ ትገኛለች፡፡ ከባህር ጠለል በላይ 2,500 ሜትር ከፍታ አላት፡፡
ደሴ ከተማ በ1885 ዓ.ም በንጉስ ሚካኤል ተቆረቆረች፡፡ ደሴ ከተማ ከመቆርቆሯም በፊት ሆነ በኋላ በምስራቅ አዝዋ ገደል፣ በምዕራብ ጦሳ ተራራን ተገን ፈልገዉ፤ በተፈጥሮ የተጣራ የውኃ ማማና ከሸዋ ወደ ጎንደርና ትግራይ ሲመላለሱ ማዕከላዊ ማረፊያ መሆኗን ተገንዝበዉ ድንኳናቸውን ተክለዉ ይቆዩባት ነበር፡፡ ለአብነትም አጼ ቴዎድሮስ ፣ አጼ ዮሃንስ፣ አጼ ሚኒሊክና እቴጌ ጣይቱ ይታወቃሉ፡፡
ራስ ሚካኤል በአጼ ሚኒሊክ የራስነት ማዕረግ ተሰጥቶት ወሎና ትግራይን ሲያስተዳድሩ ማዕከላቸዉ ትዉልድ ቦታቸው ተንታ ነበር፡፡ ከተንታ በግዛታቸዉ ማዕከልነትና የተሻለ የዉሃና ልምላሜ ያለዉ ስትራቴጂክ ቦታ ፈልገዉ ደሴን ያገኙ ሲሆን ቤተ-መንግስታቸዉንም ወደ ሐራወበሎ ኩሩ አምባ አሁን ደሴ ዙሪያ ከሚገኘዉ ቤተ-መንግስታቸውን መስርተው ቆረቆሯት፡፡
በአድናቆትም ‹‹ምንኛ ደስ የምትል ቦታ ነች በዚች ቢኖሩ ሀሴትና ደስታን ማግኘት ይቻላል›› ይላሉ፡፡ እናም ደሴ ዛሬ ትናንት ንጉሷ የመሰረቱትን ሃይማኖታዊ ተቋማቶችና ቤተ-መንግስታቸዉን፣ የት/ም ተቋማት ወዘተ መስህቦችን የተቸረች ስትሆን በአሁኑ ወቅት በመሰረተ ልማት ራሱዋን በማሳደግ ላይ ያለች ሜትሮፖሊ ከተማ ነች፡፡ ከተማዋ የተሟላ የቱሪዝም አገልግሎት መስጠት የምትችል ሲሆን የቧንቧ ዉሃ፣ የ24 ሰዓት መብራት፣ ደረጃቸዉን የጠበቁ የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት፣ የትራንስፖርት ስምሪት፣ ደረጃዉን የጠበቀ መንገድ፣ የስልክ፣ የፖሊስ፣ የባንክ፣ የንግድ ወዘተ የፈለጉትን አገልግሎት የሚያገኙባት ውብ የውቦች መኖሪያ ነች፡፡