27/08/2026
"የህፃናት ማቆያ ማዕከላት መገንባት ዋና አላማ የህፃናትን ደህንነት መጠበቅ እና እናቶች በስራ ቦታቸው ላይ የነበረባቸውን ስጋት ማስወገድ ነው"፦ አቶ አሊ ይማም
ደሴ፣ ነሐሴ 21 ቀን 2018 ዓ.ም
በደቡብ ወሎ ዞን በሁለት ፑል (አስተዳደር ፑል) እና በጤና ፑል የተገነቡ ደረጃቸውን የጠበቁ የህፃናት ማቆያ ማዕከላት ተመርቀው ለዞኑ ሴት የመንግስት ሰራተኞች እና ለህፃናት አገልግሎት መስጠት ጀመሩ።
የማዕከላቱን መመረቅ አስመልክቶ የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ ይማም እንደገለጹት፣ የህፃናት ማቆያ ማዕከላቱ መገንባት ዋና አላማ የህፃናትን ደህንነት መጠበቅ እና እናቶች በስራ ቦታቸው ላይ የነበረባቸውን የልጆች እንክብካቤ ስጋት ማስወገድ ነው።
እናቶች ልጆቻቸውን በስራ ቦታ ይዘው በሚውሉበት ወቅት የህፃናት ጤና አደጋ ላይ እንደሚወድቅና የምግብ አቅርቦታቸው እንደሚስተጓጎል የጠቆሙት አቶ አሊ፤ ማዕከላቱ መከፈታቸው የእናቶችን ስጋት ከመቀነሱም በላይ በተረጋጋ መንፈስ ስራቸውን እንዲያከናውኑ በማድረግ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን በእጅጉ እንደሚያሻሽለው ተናግረዋል።
አቶ አሊ አክለውም የማዕከላቱ ግንባታና የግብዓት ማሟላት ስራ በተቋማት የበጀት ትብብር የተከናወነ መሆኑን ገልጸው፣ በቀጣይም ለሞግዚቶች የሚከፈለው ደሞዝ በክልሉ የሚሸፈን ሲሆን ተቋማት ማዕከላቱ ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲያገለግሉ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ሴቶች፣ ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ቤተልሔም ብርሃኑ በበኩላቸው፤ የማዕከላቱ ግንባታ በሁሉም ሴክተሮች በመተባበር ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበት ገልጸዋል።
ስራው በርካታ ጉልበት፣ ወጪ እና ማስተባበር የሚጠይቅ በመሆኑ የሴት ሰራተኞችን ትዕግስት የጠየቀ እንደነበር አብራርተው፣ አሁን ላይ የመኝታ፣ የመጫወቻ እና የተንከባካቢዎች (ሞግዚቶች) ቅጥር ተጠናቆ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል። ይህም የሴት ሰራተኞችን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የፈታ ትልቅ ስኬት መሆኑን አብራርተዋል።
የዞኑ ሲቪል ሰርቪስ መምሪያ ኃላፊ አቶ በሪሁን ተገኝ በስነ-ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፤ በ2018 የበጀት ዓመት የዞኑ አመራር በአራቱም ፑሎች የህፃናት ማቆያ እንዲኖር በወሰነው መሰረት ዛሬ ሁለቱ ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል። ማዕከላቱ የመንግስት ሰራተኞች ልጆቻቸውን በታመነ ቦታ በማሳረፍ ስራቸውን በተሻለ ሁኔታ እንዲያከናውኑ የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል።
አቶ በሪሁን አክለውም እንደ ሲቪል ሰርቪስ መምሪያ አስፈላጊው የሰው ሀይልና ተንከባካቢዎች መመደባቸውን ገልጸው፣ ህፃናቱን ለመረከብ የሚያስችል ህግና አሰራር ተዘጋጅቶ ስልጠና በመሰጠቱ ሰራተኞች ከነገ ጀምሮ ልጆቻቸውን ማምጣት እንደሚችሉ አስታውቀዋል። በተጨማሪም የትራንስፖርት እና የመኖሪያ ቤት ጥያቄዎችን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት ሰራተኛውን ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌታቸው በለጠ የህጻናት ማቆያ ማዕከሉ ለመንግስት ሠራተኞች ጥያቄ ምላሽ የሰጠ መሆኑንን በመጠቆም በቀጣይ ማዕከሉን የበለጠ ለማዘመን ይሠራል ብለዋል።
ሴቶች ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ፣ ገንዘብ መምሪያ: አስተዳደር ጽ/ቤት ማዕከላቱ ለአገልግሎት እንዲበቁ በማስተባበር የላቀ ተሳትፎ እንደነበራቸው ተገልጿል።
*****