06/09/2026
ጳጉሜ 1 "የእምረታ ቀን"
በደቡብ ወሎ ዞን በአልብኮ ወረዳ "እመርታ ለዘላቂ ከፍታ!" በሚል መሪ ቃል የመስክ ሰብል ጉብኝትና የልምድ ልውውጥ ተካሄደ
በደቡብ ወሎ ዞን አልብኮ ወረዳ "እመርታ ለዘላቂ ከፍታ!" በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው «የእምርታ ቀን» በደመቀ ሁኔታ የተከበረ ሲሆን፤ የግብርና ልማት ሥራዎችንና የልምድ ልውውጥን ያካተተ የመስክ ሰብል ጉብኝት ፕሮግራም ተካሂዷል።
በእለቱ ላይ የተገኙት የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አህመድ ጋሎ እንደገለጹት፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በግብርናው ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት የምግብ ራስን መቻልን ለማረጋገጥ፣ ለአግሮ-ፕሮሰሲንግ ፋብሪካዎች የግብርና ምርቶችን ለማቅረብ እና የውጭ ምርቶችን በመተካት ኤክስፖርት የማሳደግ ሦስት ዋና ዋና ግቦችን ታስበው የተከናወኑ ናቸው።
አቶ አህመድ አያይዘውም ባለፉት ዓመታት ከ96 ሺህ በላይ የሚሆኑ የሴፍቲኔት ተጠቃሚዎችን ማስመረቅ የተቻለ ሲሆን፣ በያዝነው ዓመትም ከ261 ሺህ በላይ የሚሆኑ የሴፍቲኔት ተጠቃሚዎችን ለማስመረቅ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል። በተጨማሪም 14 ወረዳዎች ሙሉ በሙሉ ራሳቸውን ከምግብ ዋስትና ችግር ነፃ የሚያደርጉበት የትኩረት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
እንደ ማሾ፣ ባቄላ እና አኩሪ አተር ያሉ ኤክስፖርት የሚደረጉ ሰብሎችን የማምረት ሥራ የተጀመረ ሲሆን፤ ያልታረሱና የጋራ መሬቶችን በማረስ ለመጠባበቂያ የሚሆን ምርት የማከማቸት አሰራር ተዘርግቷል።
በዚህም በዞኑ ከ293 ሄክታር በላይ የወል መሬት በዘር የተሸፈነ ሲሆን፣ ከ300 ሺህ ኩንታል በላይ እህልና 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ከማኅበረሰቡ በማሰባሰብ የራስን ችግር በራስ አቅም ለመፍታት እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል።
የአልብኮ ወረዳ ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብደላህ ሰይድ በበኩላቸው፤ በወረዳው የሕዝቡን የተረጅነት አስተሳሰብ በመቀየር የመሬት፣ የውኃና የሰው ኃይል ጸጋዎችን አቀናጅቶ ለመጠቀም ሰፊ የመግባባት ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል። በወረዳው ከ14 ሺህ 952 ሄክታር በላይ የሚታረስ መሬት የሚገኝ ሲሆን፣ ከ553 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚገመትም ጠቁመዋል።
በወረዳው ከተረጅነት ማላቀቅ ጋር ተያይዞ በ03 ፈላና ቀበሌ እስካሁን ታርሶ የማይታወቀውን 39 ሄክታር የወል መሬት ከማኅበረሰቡ ጋር በመስማማት በትራክተር የማረስ ሥራ የተጀመረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት 7 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት በባቄላ፣ በጤፍ፣ በስንዴና በበቆሎ ዘር ተሸፍኖ በጥሩ ቁመና ላይ ይገኛል።
በምልከታው ወቅት ያናገርናቸው የአካባቢው አርሶ አደሮች አራጋው ይመር እና ሰይድ ሙሀመድ፤ ከዚህ ቀደም ለእንስሳት ማገጃነት ይውል የነበረውን የወል መሬት በጋራ በመስማማትና በትራክተር ማረስ መጀመራቸው ከእርዳታ ጠባቂነት ለመውጣት ትልቅ ተስፋ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።
አርሶ አደሮቹ የግብርና ባለሙያዎችን ምክር፣ ኮምፖስትና ዘመናዊ ግብአቶችን በመጠቀም በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ በማምረት የኑሮ ደረጃቸውን እያሻሻሉ እንደሚገኝ ገልጸዋል።