27/08/2026
የሠራተኞች የጋራ ትብብር፣ ተነሳሽነትና አብሮነት ለተቋማዊ ስኬት ወሳኝ ነው። ኢንጂነር አክሊሉ አዳኝ
ነሐሴ 21/2018 ዓ.ም፥ዲላ
የአንድ ተቋም የሰው ኃይሉ የመተባበር መንፈስና ተነሳሽነት ለተቋሙ ስኬት ቀዳሚውን ሚና እንደሚጫወት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር አክሊሉ አዳኝ ገለጹ።
ኃላፊው ከአገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሳትፎአቸው መልስ ከቢሮው አጠቃላይ ሠራተኞች ጋር በተቋሙ ወቅታዊ ተግባራት ዙሪያ በመወያየት አስፈላጊውን የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል።
ከውይይቱ አስቀድሞም አጠቃላይ የተቋሙ ሠራተኞች «የእንኳን ደህና መጡ» አቀባባል አድርገውላቸዋል።
ኢንጂነር አክሊሉ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የአገራዊ ምክክር ጉባኤው የአገሪቱን የወደፊት ተስፋ የሚያለመልም፣ የበርካታ ዜጎች ልዩ ልዩ ሐሳቦች በሰፊው የተንጸባረቁበትና በአንድነት የተቋጨበት ታላቅ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ የዜጎች የአንድነት ሐሳብም አገሪቱን ወደ ላቀ የዕድገት ምዕራፍ ለማሸጋገር የሚያስችል መሆኑ በብዙዎች የታመነበት መሆኑን አስታውሰዋል።
ከዚህ ባሻገር፣ ኃላፊው በተቋሙ በተጠናቀቀው የሠራተኞች የድልድል ጉዳይ ላይ ሐሳብ የሰጡ ሲሆን፤ ሁሉም ሠራተኛ በመመሪያው መሠረት መመደቡ ለተቋሙ ስኬት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በውሃ ዘርፍ ብቻ 117 ተቋማት ተገንብተው እስከ 500 ሺህ የሚጠጉ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ጠቅሰው፤ የዚህ ስኬት ማዕከል የሠራተኛው የላቀ ጥረት መሆኑን አድንቀዋል።
በተጨማሪም በአዲሱ የተቋሙ ሠራተኞች ድልድል መሠረት ሠራተኛው የየድርሻውን በመወጣት ለቀጣይ ተቋማዊ ድሎች በጋራ እንዲተጋ አሳስበዋል።
በሌላ በኩል መንግሥት በሚከተለው «ከተረጅነት ወደ ምርታማነት» መርህ መሠረት ሠራተኛው በመደበኛ ሥራው የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል።
ከዚህም በተጨማሪ «ለአደጋ ያልተጋለጠ ማኅበረሰብ ለመፍጠር» በሚለው የመንግሥት ዕቅድና ማሻሻያ ውስጥ የሠራተኛው ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ፣ እያንዳንዱ ሠራተኛ በግለሰብ ደረጃ የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ አሳስበዋል።
የአለም አቀፋዊ የአየር ለውጥና በኤልኒኖ ሳቢያ ሊከሰቱ የሚችሉ ተፈጥሮአዊ አደጋዎችን ለመመከት የሚያስችሉ ክልላዊ ቅድመ ዝግጅት ላይ ሁሉም የቢሮው ማህበረሰብ አባላት የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።
ንጹህ ውሃ፣ሳኒቴሽንና ታዳሽ ኃይል፤ለዘላቂ ህይወት!
Clean Water,Sanitation & Renewable Energy for a Sustainable Life!
የቢሮው የህዝብ ግኑኝነት ዳይሬክቶሬት
የመረጃ ምንጮቻችንን ይጎብኙ
Face book: https://www.facebook.com/share/1CdGNHnV4G/
Telegram Channel: https://t.me/southethiopiawaterenergy2026