27/04/2026
ይነበብ!!
የቴዲ አፍሮ ሥራዎች ከወንጌል እውነት እና ከመጥመቁ ዮሐንስ ተልዕኮ አንጻር ሲመዘን፣
ወንጌል የሚለው ቃል "ኢቫንጄሊዮን" ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም የምስራች ማለት ነው። ወንጌል የሰው ልጅ በኃጢአቱ ምክንያት ከእግዚአብሔር ተለይቶ ሳለ፣ እግዚአብሔር በልጁ በኩል ሰውን ለማዳን ያደረገው መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ነው። ይኸውም ሙሉ በሙሉ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ስለ እርሱ ሰው መሆን፣ ስለ መከራው፣ ስለ ሞቱ፣ ስለ ትንሳኤውና ዳግም ስለመምጣቱ ነው። ጠቅለል ባለ መልኩ ስንመለከት የወንጌል ማዕከላዊ ሃሳብ መተካት/ምትክነት (Substitution) ነው። ይህም እኛ ልንቀበለው የሚገባንን ሞትና ቅጣት ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተቀብሎ፣ የእርሱን ጽድቅና የዘላለም ሕይወት ለእኛ መስጠቱ የወንጌል እምብርት ነው።
"በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።" (ዮሐንስ 3:16)
የመዝሙርና ዘፈን አንድነት ሁለቱም ሙዚቃዊ መዋቅር ያላቸው መሆኑ ሲሆን፣ ሁለቱም የሰውን ስሜት የመንካት፣ መልእክትን የማስተላለፍና ባህልን የመግለጽ አቅም ያላቸው የጥበብ ውጤቶች ናቸው። ልዩነቱ ግን ሰማይ ከምድር እንደሚርቅ የተራራቁ ናቸው፤ የመዝሙር ምንጩ የእግዚአብሔር ቃል ሲሆን ግቡ ደግሞ ለእግዚአብሔር ክብርና ለአማኞች መታነጽ ነው። ዘፈን ግን ምንጩ ሰብአዊ ስሜት፣ ማህበራዊ ክስተት ወይም ፍልስፍና ሲሆን ግቡም ምድራዊ መዝናኛ ነው። ዘፈን ዓለማዊ እሴቶችን ሲያራምድ፣ መዝሙር ግን መለኮታዊ እውነትን ይሸከማል።
ከላይ ባየናቸው ሁለቱ የወንጌል ምንነት እና ከመዝሙርና ዘፈን አንድነትና ልዩነት ትርጓሜ ተነስተን ዶ/ር ደረጀ ከበደ በቴዲ አፍሮ በኢቶሪካ የዘፈን አልበም የሰጠው የግል ምልከታ ከመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ እና ራሱ ከዘመራቸው መዝሙሮች አንጻር ያለውን መጣረስ ለማሳየት እና ሌሎች የዶ/ር ደረጀን ምልከታ በቅንነት ተመልክተው ወደ ስህተት እንዳይሄዱ በገባኝ እውነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጭብጡን መሠረት በማድረግ ለመጠቆም ነው፡፡
መጥመቁ ዮሐንስ የክርስቶስን መምጣት ለማብሰር "የእግዚአብሔርን በግ" እያመለከተ መንገድ የጠረገ ነቢይ ነው። ዶ/ር ደረጀ ቴዲ አፍሮን ከዚህ ታላቅ ነቢይ ጋር ማነጻጸራቸው፣ የኪነ-ጥበብን ማህበራዊ ፋይዳ ከወንጌል ተልዕኮ ጋር የመቀላቀል አዝማሚያ የሚታይበት ከመጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ/ልከኛ አስተምህሮ ጋር የሚጣረዝ ምልከታ ነው፡፡ ዘፈን የሞራልና የፍትህ እሴቶችን ቢይዝም፣ የደህንነት ወንጌል ግን ሊሆኑ አይችልም። ኪነ-ጥበብ የሕሊና ድምፅ ሲሆን፣ ወንጌል ግን የመንፈስ ሕይወት ነው። ወንጌል ትኩረቱ የሰው ልጅ ከኃጢአት ስለማዳንና ስለ ዘላለም ሕይወት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ንግግር እርሳቸው በዝማሬያቸው ካከበሩትና ከፍ ካደረጉት የክርስቶስ ብቸኛ አዳኝነትና የወንጌል ልዩ ባሕርይ ጋር የሚጋጭ ሃሳብ ነው፡፡
እጅግ በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ ሃሳብ ተቃርኖ የሚያነሳቸውን ግለ-ምልከታ ተቀባይነት ለማረጋገጥ በሚል "ዘመርኩ እንጂ አልኖርኩበትም" ማለታቸው ነው፡፡ ይህን ሃሳብ በግል ማንጸባረቁ ችግር ባይኖረውም ለፖለቲካ ፍጆታ በሚል በዚህ መልኩ ማቅረቡ ግን ግብዝነት ነው፤ ምክንያቱም እርሳቸው በዝማሬዎቻቸው የጸጋውን ደጋፊነት ሲመሰክሩ ቆይተው፣ ዛሬ "አልኖርኩበትም" ማለታቸው አድማጩን ግራ የሚያጋባ ክስተት ከመሆን ባለፈ የሚያስገኘውን አዎንታዊ ውጤት በግሌ ምንም አልታየኝም፤ አይታየኝምም፡፡ ይህ ንግግር አገልጋይ እንደ ሰው ሊደክም እንደሚችል ቢጠቁምም፣ ወንጌል ግን ደካማውን ሰው ቀይሮ ለክብር እንደሚያበቃው የሚገልጸውን የክርስትና መሠረታዊ እውነት ዝቅ የሚያደርግ ነው፡፡ ለዚህም ነው ትክክለኛ/ልከኛ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ መሠረት ያደረገ አይደለም ያልኩት፡፡
ኪነ-ጥበብ (ዘፈን) ሰብአዊ ስሜትንና ማህበራዊ ንቃተ-ህሊናን ለማነቃቃት ትልቅ መሣሪያ ቢሆንም፣ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር እኩል "እውነትን እየሰበከ ነው" ተብሎ ሊወሰድ አይችልም፤ አይሆንምም፡፡ ዶ/ር ደረጀ በዝማሬዎቻቸው ሲያስተምሩ እንደነበረው፣ የወንጌል ሰበካ ምንጩም ግቡም ክርስቶስ ብቻ ነው። ታዲያ ዛሬ ላይ ቴዲ አፍሮን እንደ ወንጌል ሰባኪ መቁጠር፣ ዓለማዊ ጥበብንና መለኮታዊ መገለጥን በአንድ ሚዛን መመዘን በየትኛው መንገድ ትክክል ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባ አይደልም፡፡ ይህም በቤተክርስቲያን አስተምህሮ ውስጥ የ"ቅዱስ" እና የ"ዓለማዊ" መለያ መስመር እንዲደበዝዝ የሚያደርግ ክፉ ዘር ነው፡፡
ባጠቃላይ ወንጌል ሰውን ወደ ክርስቶስ እንጂ ወደ ሰው አድናቆት አይመራም። እርሳቸውም ቢሆኑ ባለፉት ዓመታት በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ አማኞች የነፍስ ምግብ/ስንቅ የሆኑ ዝማሬዎችን ያበረከቱት/የለገሱን፣ በራሳቸው ብቃት ሳይሆን በክርስቶስ ወንጌል ኃይል እንደነበረ ማስታወስ የተሳናቸው ይመስላል፤ ዛሬም ቢሆን እውነተኛው "ድምፅ" የሰው ልጅ ጽድቅ ሳይሆን የእግዚአብሔር ጸጋ መሆኑን መመስከር፣ ለራሳቸውም ሆነ ለትውልዱ የሚበጅ እውነት ወንጌልና ወንጌል ብቻ መሆኑን ተገንዘዝቦ ወደ ቀደመው እውነት እንዲመለሱ ምክሬም፣ ምኞቴም፣ ጸሎቴም ነው፡፡
ወንጌል ያሸንፋል!!
መልካም ቀን!!