02/09/2026
የቴክኒክና ሙያ ሥልጠናን ለገጠሩ ማህበረሰብ በፍትሃዊና ተደራሽ መልኩ ለማድረስ በ2019 የሥልጠና ዘመን ተንቀሳቃሽ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ለመተግበር መዘጋጀቱ ተገለጸ።
ተንቀሳቃሽ ሥልጠናው ‹‹ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ለገጠሩ ማህበረሰብ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት›› በሚል መሪ ቃል የሚተገበር ሲሆን፣ ዓላማውም በገጠር የሚኖሩ ማህበረሰቦች ከቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማስቻል የምርትና ምርታማነት አቅማቸውን ማሳደግ ነው።
የድሬዳዋ አስተዳደር ሥራና ክህሎት ቢሮ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኤጀንሲ ከግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ሥልጠናውን በድሬዳዋ በሚገኙ ሁለት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች አማካኝነት ለማስፈጸም አቅጣጫ ተይዟል።
በዚህም በግብርና፣ ከግብርና ውጪ በሆኑ ዘርፎች እና በገጠር ቴክኖሎጂ ልማት ላይ ያተኮሩ ሥልጠናዎችን ወደ ገጠር ማህበረሰቡ በማድረስ፣ በሥራ ላይ ያሉና ከዋና ሥራቸው ውጪ በሆኑ የሥልጠና ዘርፎች ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸውን 4,000 አርሶ አርብቶ አደሮች በማብቃት ምርትና ምርታማነትን ማሻሻል ታስቧል።
ይህንንም አስመልክቶ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ የገጠሩ ማህበረሰብ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ሥልጠናን ከተግባራዊ ቴክኖሎጂ ጋር ማጣመር እና የሥልጠና ይዘትን ከአካባቢው ትክክለኛ ፍላጎትና የገበያ አቅጣጫ ጋር ማስማማት ወሳኝ መሆኑ ተገልጿል።
በዚህም ሥልጠና በኮሌጅ ግቢ ብቻ የሚሰጥ አለመሆኑን የሚያረጋግጥ ሲሆን አሰልጣኞችና የሥልጠና ግብዓቶች ወደ ገጠር የሥልጠና ቦታዎች በመንቀሳቀስ ማህበረሰቡ በሚገኝበት አካባቢ ሥልጠና እንዲያገኝ የሚያስችል አተገባበር ይከተላል።
የአተገባበሩ ዋና ዋና እርምጃዎች
* የገበያ ተኮር አጫጭር ሥልጠና ፍላጎት ዳሰሳ ማካሄድ፤
* ተገቢ የሥልጠና ቦታዎችን ማመቻቸትና ለሥልጠና የሚስማማ ጥበቃ ማድረግ፤
* አሰልጣኞችንና የሥልጠና ግብዓቶችን ከኮሌጆች ወደ ገጠር ማንቀሳቀስ፤
* ለማህበረሰቡ በቂ ግንዛቤ መፍጠር፤
* ሰልጣኞችን መመልመልና በፍላጎታቸው መሠረት ወደ ሥልጠና ማቅረብ፤
* አንገብጋቢ የልማት ችግሮችን በመለየት በሥልጠናና በቴክኖሎጂ አማራጮች መፍትሔ ማመቻቸት፤
* ተግባራዊ ሥልጠና መስጠት፤
* የሥልጠና ተጠቃሚዎችን በድጋፍና በክትትል ማጠናከር፤
* የሙያ ብቃት ምዘና ማከናወን።
በመሆኑም ተንቀሳቃሽ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠናው የሥልጠና አገልግሎትን ከከተማ ወደ ገጠር በማስፋፋት የተደራሽነት ክፍተትን ለማጥበብ፣ የገጠር ማህበረሰብን በተግባራዊ ክህሎት ለማብቃት እና ሥልጠናን ከአካባቢያዊ የልማት ችግሮች ጋር በማስተሳሰር ዘላቂ የኢኮኖሚና የኑሮ ለውጥ ለማምጣት የሚያግዝ ተግባራዊ የክህሎት ልማት አቅጣጫ መሆኑ በቢሮው የሰልጣኝ ልማትና የተቋማት አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጀማል አደን ተጠቁሟል።
“ሥልጠና ወደ ማህበረሰቡ፤ ክህሎት ወደ ምርት፤ ሙያ ወደ ልማት!”
የሥራና ክህሎት ቢሮ ህዝብ ግንኙነት
ነሐሴ 27 ቀን 2018 ዓ.ም | ድሬዳዋ