12/08/2026
የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር እንዲሳካ ሁሉም የበኩሉን ያበርክት!!
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሀምሌ 8፣ 2018 በይፋ መጀመሩ ይታወሳሉ። ሀገራዊ ምክክሩ ቀደም ሲል በተመረጡ እና በስምንት አንጓዎች በተደራጁ አጀንዳዎች ዙሪያ ከተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች እና የማህበረሰብ ክፍሎች በተወከሉ በሺህ የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች እየተካሄደ እንደሚገኝ የሂደቱ አስተባባሪ የሆነው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታውቋል።
ምክክሩ ቀደም ሲል በተነደፈ የውይይት ስርዓት መሰረት በመካሄድ ላይ እንድሚገኝ እና ባለፉት ጥቂት ቀናት በአጀንዳዎች ላይ ምክክር በማካሄድ የተወሰኑት የስራ ቡድኖች ውይይታቸውን ማገባደድ መጀመራቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል። ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) በሀገራዊ ምክክሩ በንቃት በመሳተፍ ላይ ይገኛል።
በሀገራችን ለረዢም ጊዜ የልዩነት እና የግጭት ምንጭ ሆነው በቆዩ ጉዳዮች ዙሪያ የሚደረግ ምክክር እጅግ አከራካሪ እና አጨቃጫቂ ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል። በሀገራዊ ምክክሩ ውይይት እየተደረገባቸው የሚገኙ አጀንዳዎች፡ የማንነት ጉዳይ፣ የአስተዳደር ወሰን፣ የእኩል ተሳታፊነት እና እኩል ተጠቃሚነት፣ የታሪክ እና ትርክት ጉዳዮች፣ ሀገራዊ ምልክቶች እና መገለጫዎች፣ የከተሞች አስተዳደር፣ ቋንቋ፣ የህዝብ ውክልና እና የምርጫ ስርዓት እና ሌሎች እጅግ መሰረታዊ ጉዳዮች ሰፊ የሀሳብ ልዩነት እና ፍጭት ሊያስከትሉ የሚችሉ ናቸው። በእነዚህ አጀንዳዎች ዙሪያ ስምምነት ላይ መድረስ አልጋ በአልጋ እንደማይሆን መገመት ይቻላል።
በታሪካዊም ሆነ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የተለያየ እይታ፣ አስተሳሰብ፣ ፍላጎት፣ የታሪክ ግንዛቤ፣ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ወዘተ ያላቸው ግለሰቦች፣ ቡድኖች፣ የፖለቲካ ኃይሎች በተለያዩ አጀንዳዎች ዙሪያ ያላቸውን አስተሳሰብ በማቀራረብ፣ ሁሉንም አሸናፊ ሊያደርጉ በሚችሉ ምክረ ሀሳቦች ላይ ለመድረስ ከፍተኛ ትእግስት፣ ጥበብ እና ኃላፊነት ይጠይቃል። በተጀመረው ሀገራዊ ምክክር ሀገራችንን ካለችበት ውስብስብ ችግሮች አላቆ የተሻለ ሰላም እና እድገት የተረጋገጠባት ሀገር ለመፍጠር ከራስ እና ከራስ ቡድን ፍላጎት በላይ ሀገርን እና ህዝብን ያስቀደመ እይታ፣ ዝግጅት እና ቅንነት ያስፈልጋል።
ባለፈት ጥቂት ሳምንታት በሁሉም አጀንዳዎች ዙሪያ እየተደረጉ ያሉ ውይይቶች ከሞላ ጎደል በመግባባት እና በሰላማዊ ሁኔታ በመካሄድ ላይ መሆናቸው ተስፋ የሚሰጥ ቢሆንም፣ አልፎ አልፎ የምክክር ሂደቱን ሊያውኩ የሚችሉ አካሄዶች እና ፍላጎቶች ሲከሰቱ ይስተዋላል። ሀገራዊ ምክክሩ ዓላማውን በትክክል ያሳካ ዘንድ ሂደቱ ሳይንሳዊ በሆነ የምክክር ስነ ዘዴ፣ ገለልተኛ እና አካታች በሆነ መልኩ ሊካሄድ ይገባል።
በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የምክክር ሂደቱ ተሳታፊዎችም ሆነ ከሂደቱ ውጪ ያሉ ባለድርሻ አካላት ሂደቱን በተመለከተ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ፣ የሚወስዱት አቋም እና የሚሰጡት አስተያየቶች በሀገራዊ ምክክሩ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያሳድሩ እና ሂደቱ የታለመለትን ዓላማ እንዳይመታ ሊያደርጉ ይችላሉ። በአንድ ወይም በጥቂት አጀንዳዎች ዙሪያ በሚፈጠር አለመግባባት አጠቃላይ የምክክር ሂደቱ ቅርቃር (Deadlock) ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ሀገራዊ ምክክሩ ዓላማውን እንዳያሳካ ምክንያት ሊሆኑ ይችላል።
በመሆኑም የተጀመረው ሀገራዊ ምክክሩ በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የቆዩ እና ጥልቅ አለመግባባቶችን ለመፍታት በሚያስችል ሁኔታ ይጠናቀቅ ዘንድ፣ የምክክሩ ቀጥተኛ ተሳታፊዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለሂደቱ መሳካት የበኩላቸውን አስተዋጾ ሊያበረክቱ ይገባል። በምክክሩ የሚሳተፉ አካላት ይህ ታሪካዊ ሂደት በስኬት ይጠናቀቅ ዘንድ፣ ከራስ ፍላጎት ባሻገር የሌሎችን ፍላጎት እና ስጋት በቅጡ ለመረዳት፣ ለመደራደር እና የሌሎችን ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ መግባባት ላይ ለመድረስ ተነሳሽነት እና ቁርጠኝነት ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።
የምክክር ሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ የአንድ ወገን ፍላጎትን በሌሎች ላይ ለመጨን ከሚደረግ ሙከራ መራቅ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በምክክር ሂደቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ከሚያደርጉ አፍራሽ ተግባራት መቆጠብ ያስፈልጋል።
የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር በሀገራችን ካሉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች መካከል የተወሰኑትን ለመፍታት እና ቀሪ የሀሳብ ልዩነቶች በሂደት የሚፈቱበትን ልምድ እና ተግባራዊ ተሞክሮ ሰጥቶን እንደሚያልፍ ይጠበቃል። ነእፓ በሀገራችን አካታች ሀገራዊ ምክክር እንዲካሄድ ባለፉት ዓመታ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ እንደቆየው ሁሉ፣ የተጀመረው የምክክር ሂደት እንዲሳካ የበኩሉን አስተዋጾ እንደሚያደርግ በዚህ አጋጣሚ ያረጋግጣል።
ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ
ነሀሴ 6፣ 2018