20/08/2026
በአስተዳደሩ በክረምት ወራት የሚከናወኑ የበጎ ፍቃድ የጤና አገልግሎቶች ከዘመቻነት አልፈው የህብረተሰቡ ዘላቂ ማህበራዊ ባህል እንዲሆኑ የማድረግ እና የማጠናከር ስራ እየተሰራ መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ ድሬደዋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ገለጹ።
የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ እና የቀዶ ጥገና እስፔሻሊስት ሀኪሞች መካከል በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት የቀዶ ህክምና ወረፋ የሚጠብቁ ታካሚዎች /Sergical Backlog/ ለመቀነስ የተዘጋጀ የውይይትና የማስጀመሪያ መድረክ ተካሄደ።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የብልፅግና ፖርቲ ድሬደዋ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በበጎ ፍቃድ የቀዶ ህክምና ዘመቻ ማስጀመሪያ መድረክ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት የመንግስት እና የግል የጤና ተቋማት ባለሙያዎች በተቀናጀ መንገድ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ የበጎ ፍቃድ ስራዎችን እያከናወኑ እንደሚገኝ ጠቁመው በክረምት ወራት የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በአስተዳደሩ የቀዶ ጥገና ወረፋ ለሚጠብቁ ታካሚዎች ህክምና ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ እና ወደ ሌሎች ሩቅ ቦታዎች በመሄድ የሚደርስባቸውን እንግልት፣ የቤተሰብ መበተን እና ከፍተኛ ወጪ ለማስቀረት አገልግሎቱ እዚሁ ድሬዳዋ ውስጥ እንዲያገኙ መደረጉ ትልቅ የሠብአዊነት ሥራ መሆኑን ገልፀዋል።
አቶ ኢብራሂም አያይዘውም ድሬዳዋን የአካባቢው ክልሎች እና የጎረቤት ሀገራት የሚገለገሉበት የህክምና ማዕከል ለማድረግ ከግል የጤና ተቋማት ጋር የሚደረገው አጋርነት (Public-Private Partnership) ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመጠቆም ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለበጎ ፍቃደኛ ሀኪሞች እና ለህክምና ተቋማት በአስተዳደሩ ስም ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን አስተዳደሩም ለሚሠሩት በጎ ሥራዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እና አጋርነት ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በመድረኩ ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ፅጌረዳ ክፍሌ በበኩላቸው በክረምት በበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ ከመንግስት እና ከግል ጤና ተቋማት ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት በርካታ ህብረተሰብ ተጠቃሚ የሆኑባቸው ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ጠቁመው በዚህም የስኳር እና የደም ግፊት ህመምተኞችን የመለየት ሥራ የተከናወነ ሲሆን፣ ከ40 ዓመት በላይ ለሆኑ የጤና ሴክተር ሴት ሰራተኞች ነፃ የጡት ካንሠር (Mammography) ምርመራ እየተካሄደ መሆኑንና የሄፓታይቲስ 'ቢ' እና 'ሲ' ምርመራ ተካሂዶ አዎንታዊ ለሆኑ ታካሚዎች አስፈላጊው የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ገልፀዋል።
በተመሳሳይ ከ1,200 በላይ በ3 የመንግስት ትምህርት ቤቶች የልብ ምርመራ መደረጉን እና ከ52 በላይ ህጻናት ላይ የልብ ህመም ችግር በመገኘቱ አስፈላጊው የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል ብለዋል።
ዶክተር ፅጌረዳ አክለውም በአስተዳደሩ የቀዶ ህክምና ወረፋ ላይ ያሉ 270 ያህል ታካሚዎችን ችግር ለመፍታት ከቀዶ ጥገና ስፔሻሊስት ሀኪሞች ጋር በመቀናጀት ስራው በይፋ መጀመሩን ጠቅሠው ከእነዚህ መካከል 135 ያህሉ የጆሮ፤ አፍንጫ እና ጎሮሮ (ENT) ህክምና የሚሹ በመሆናቸው አስፈላጊው ግብአት እና የህክምና መሳሪያዎች ከተሟሉ በኋላ 75 ያህሉን በአንድ ሳምንት ውስጥ ለማከም እቅድ ተይዞ ወደ ስራ መገባቱንና በዛሬው ዕለትም የሁለት ሰዎች ኦፕሬሽን ተጀምሮ ሥራው በይፋ መጀመሩን ገልፀዋል።
በመድረኩ የተገኙ በጎ ፍቃደኛ ሀኪሞች በበኩላቸው የጊዜ ሠሌዳቸውን በመከፋፈል የበጎ ፍቃድ ስራውን ለመከወን ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በመድረኩ የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ሀላፊ አቶ ዩሱፍ ሠኢድን ጨምሮ የማኔጅመንት አባላት ተሣትፈዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኮሙዩኒኬሽን
14/12/2018 ዓ.ም