02/09/2026
የአካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ የዓለም ስጋት በመሆኑ፣ ጉዳዩን በተገቢው ተረድቶ ለመከላከል በትኩረት መስራት እንደሚገባ የክልሉ የአካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣ አስታወቀ
ነሐሴ 27/2018 ዓ.ም
ባለስልጣኑ ክልላዊ የአካባቢ ሁኔታ ለውጥ ዘገባ በሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር ለመመዘን በክልሉ ከሚገኙ አራት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመቀናጀት እየሰራ መሆኑም ተገልጿል
በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የሶዶ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ፣ የአካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ አሁን ላይ የዓለም ስጋት መሆኑን ገልጸዋል።
ስጋቱን ለመከላከል ጉዳይን በተገቢው ደረጃ ተረድቶ፣ በክልሉና በማህበረሰቡ ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ በጥናትና በመረጃ ለይቶ እንዲሁም በጠንካራ አመራር መምራትና ተገቢ ምላሽ መስጠት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በክልሉ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በምርምር የተደገፉ ሥራዎችን በማጠናከር፣ የአካባቢና የአየር ንብረት ችግሮችን በትክክል ለይቶ ለመፍታት መስራት እንዳለባቸውም አስረድተዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ልዩ አማካሪ ቦሻ ቦንቤ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በዘርፉ የሚካሄዱ ጥናቶችና የሚገኙ መረጃዎች በሪፖርት ደረጃ ብቻ ሳይቆዩ ወደ ተግባራዊ ውሳኔና ወደ መፍትሔ ተኮር ሥራዎች እንዲቀየሩ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።
በመረጃዎች ጥራትና ተአማኒነት ላይ ትኩረት እንዲሰጥም ዶ/ር ቦሻ አሳስበዋል።
የክልሉ አካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቴ ግጄ በበኩላቸው፣ ባለስልጣኑ በክልሉ ወቅታዊ የሆኑ የአካባቢና የአየር ንብረት ጉዳዮች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሆነ ገልጸው ።
ጥናቱ የክልሉን የባለፉት አምስት ዓመታት የአካባቢ ሁኔታ በተጨባጭ መረጃና በሳይንሳዊ ምርምር ለመመዘን ትኩረት ማድረጉን አብራርተዋል ።
ጥናቱ ያተኮረባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች የመሬት አጠቃቀምና የአፈር ጤንነት፣የውሃ ሀብቶችና የሥነ-ምህዳር፣የሥርዓተ-ምህዳርና የብዝሃ ሕይወት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ሁኔታና ተጽዕኖዎች እንዲሁም የቆሻሻ አያያዝና ብክለት መሆናቸውን አስረድተዋል ።
ጥናቱ ማህበረሰብና የተለያዩ የውሳኔ ሰጪ አካላት ስለ አካባቢው ሁኔታ ወቅታዊ፣ ትክክለኛ፣ ተዓማኒና ጠቃሚ መረጃ እንዲያገኙ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም ገልጸዋል።
በመድረኩ የጥናቱን ሥራ በሙያዊና በተቀናጀ መንገድ ለማካሄድ የተዘጋጀው የፕሮጀክት ፕሮፖዛል ሰነድ ቀርቦ በመገምገም፣ በክልሉ ከሚገኙ አራት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትብብር ወደ ተግባር እንዲገባ አቅጣጫ ተቀምጧል።