06/09/2026
የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በተግባራዊ ክህሎት ለማጠናከር ከዘጠኝ ወረዳዎች ለተውጣጡ የተፈጥሮ ሀብት ባለሙያዎች ስልጠና ተሰጠ።
ስልጠናው በቆላማ ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት (LLRP) ድጋፍ የተዘጋጀ ሲሆን፣ የአፈር መሸርሸርን ለመቀነስ፣ የውሃ ሀብትን ለመጠበቅና የመሬት ምርታማነትን ለማሻሻል የሚያግዙ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ቴክኖሎጂዎች ላይ ያተኮረ ነው።
የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ ኬት ቾል እንደገለጹት፣ በስልጠናው የሚያገኙትን እውቀትና ክህሎት ወደ ወረዳዎቻቸው በማስፋፋት በእርከን ሥራና በሌሎች የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ላይ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
አቶ ኬት አክለውም፣ ስልጠናው ፕሮጀክቱ በ2019 ዓ.ም. ካቀዳቸው የሥራ እቅዶች አንዱ መሆኑን ጠቁመው፣ የግብርና ባለሙያዎችን በክህሎት ማብቃት በቀጥታ ወደ አርሶ አደሩ በመድረስ የአመራረት ሥርዓቱንና የኑሮ ሁኔታውን ለማሻሻል የሚያስችል አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
በተጨማሪም ስልጠናው ባለሙያዎች የተማሩትን እውቀት በተግባር በመተርጎም በወረዳና በቀበሌ ደረጃ ለሚከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎች የተሻለ የቴክኒክ ድጋፍ እንዲሰጡ ያስችላል።
የቆላማ አከባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት በተለይም በቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ሁኔታን፣ የግብርና ምርታማነትንና የማህበረሰብ ተጠቃሚነትን ለማሻሻል የሚከናወኑ ሥራዎችን በመደገፍ ላይ ይገኛል።