17/11/2025
የጡት ካንሰር - ይወቁ፣ ይቅደሙ!
1. የጡት ካንሰር ምንድን ነው?
የጡት ካንሰር በጡት ውስጥ ያሉ ሕዋሶች ባልተለመደ መልኩ ሲራቡና ሲያድጉ የሚከሰት በሽታ ነው። የጡት ካንሰር በኢትዮጵያ የተስፋፋ ያለ የካንሰር ዓይነት ሲሆን፣ ከሁሉም የካንሰር አይነቶች የጡት ካንሰር ታማሚዊች 32% ይዞ ይገኛል።
መረጃዎች እንደሚያሣዩት በየዓመቱ 16,000 በላይ አዲስ የጡት ካንሰር ታማሚዎች በኢትዮጲያ ይመዘገባሉ። ከ70% በላይ ሴቶችም በሽታው የመጨረሻ ደረጃ ወይም ስር ከሰደደ በሁዋላ ወደ ጤና ተቋም ስለሚመጡ የህክምናው ዉጤት ዉስብስብ እና ዝቅተኛ ያደርገዋል፡፡ በኢትዮጵያ አብዛኛው ሴቶች የጡት ካንሰር ግንዛቤ ስለሌላቸዉ የምርመራ እና የሕክምና አገልግሎቶች ለማግኘት የተገደቡ ናቸው።
2. የጡት ካንሰር በምን ይከሰታል?
የጡት ካንሰር አንድ የተለየ መንስኤ ባይኖረዉም ፤ መከላከል የምንችላቸዉ እና የማንችላቸዉ ነገሮች በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።
3. መነሻ ምክንያቶች
• በቤተሰብ የነበረ ታሪክ ወይም የተወረሰ ዘረመል
• የመጀመሪያ የወር አበባ ቀደም ብሎ መጀመር ወይም ለማረጥ መዘግየት እና እድሜ መጨመር
• የመጀመሪያ እርግዝናን ከ30 ዓመት በኋላ ሲሆን እና አለማጥባት
• ወፍረት፣ በተለይ የወር አበባ ከተቋረጠ በኋላ
• አልኮል መጠጣት ወይም ማጨስ
• ቀደም ብሎ በደረት ላይ የተደረገ የጨረር ሕክምና ጋር ተያይዞ መኖር መንስኤዎች ሊሆኑ ይችላሉ።
4. ምልክቶች — ከሚከተሉት አንዱን ካዩ ወደ ጤና ባለሙያ ይሂዱ!
• በጡት ወይም በእጅ ትከሻ ስር የተለየ እብጠት ወይም መጠጠር
• የጡት መጠን ወይም ቅርፅ መቀየር
• የቆዳ መቅላት ወይም መንቀጥቀጥ
• የጡት ጫፍ ወደ ውስጥ መግባት ወይም ደም የያዘ ፈሳሽ መውጣት
• በጡት ውስጥ በአንድ ቦታ የማያቆም ህመም መሰማት ምልክቶች ናቸው።
5. በቀላሉ ራስዎን መፈተሻ መንገድ
1. በመስታወት ፊት ቆሞ ትከሻዎን ቀጥ በማድረግ እና እጆችዎን በወገብ ላይ አድርገው ጡቶችዎን ይመልከቱ። የቆዳ መቆጣት እና የጡት መጠን ለውጦች ይመልከቱ። እጆችዎን ወደ ላይ ቀጥ አድርገው ያንሱ እና ለውጦችን ይመልከቱ።
2. በተጨማሪ አንድ እጅዎን በማንሳት በሌላኛው እጅዎ በመካከለኛው 3 ጣቶች ክብ እንቅስቃሴ በማደረግ ከጡትዎ የውጨኛ ክፍል ጀምረው እስከ ጫፉ ድረስ ይመርምሩ። እጅዎን በመቀያየር ሁለቱንም ጡቶች ተኝተው አልያም ቆመው መመርመር ይችላሉ።
6. ምርመራ
• ከላይ የተጠቀሱ ምልክቶችን ካስተዋሉ እና የተለየ ለውጥ ካገኙ በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ምርመራ ያድርጉ።
• የጡት ካንሰር ምርመራ በሰለጠነ የጤና ባለሙያ በተመረጡ ጤና ተቋማት ይሰጣል።
• የጡት ካንሰር ምርመራ እንደ አስፈላጊነቱ አልትራሳውንድ ወይም ማሞግራፊ ጨምሮ ፓቶሎጂ ምርመራዎችን ያጠቃልላል።
7. ሕክምና
የጡት ካንሰር ህክምና የተለያዩ አማራጮች አሉት
• ቀዶ ጥገና፣ ኬሞቴራፒ፣ የሆርሞን እና የጨረር ሕክምና
8. ተጋላጭነትን ለመቀነስ መደረግ ያለባቸው ነገሮች
• ክብደት መቆጠጠርና አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ
• አልኮልን መቀነስ እና አለማጨስ
• በተቻለ መጠን በወሊድ ወቅት ማጥባት
• በቤተሰብ ውስጥ የበሽታው ታሪክ ካለ ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ ምርመራ ማድረግ
• ማንኛውም ለውጥ በሚኖርበት ጊዜ ቀደም ብለው ህክምና ምርመራ ያድርጉ — ቀድሞ ከተገኘ የመዳን እድሉ ከፍተኛ ስለሆነ
9. መቼ ወደ ህክምና ተቋም መሄድ አለብዎት
ያልተመደ እብጠት ወይም መጠጠር፣ የቆዳ ለውጥ፣ የጡት ጫፍ ለውጥ ወይም የጡት ህመም ሲያጋጥምና ምልክቶቹ ከጥቂት ሳምንታት በላይ ከቆዩ በአፋጥኝ ወደ ጤና ተቋም መሄድ ይገባል፡፡