31/10/2025
የጎንደር ዙሪያ ወረዳ አስተዳደር ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመቀናጀት ሰላምና ጸጥታ እያስከበረ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የእርድ እንስሳ ድጋፍ አደረገ
በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ሰላምና ጸጥታን የማስከበር ስራ በሠራዊቱ፣ በሌሎች የጸጥታ መዋቅር አባላትና በህዝብ ተሳትፎ እየተከናወነ ሲሆን ወረዳው ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመቀናጀት በአካባቢው ለሚገኘው የ57ኛ ክፍለ-ጦር የሀገር መከላከያ ሠራዊት የእርድ እንስሳ ድጋፍ አድርጓል፡፡
የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኑርሁሴን ሁሴን በዚህ ጊዜ እንዳሉት በቅርቡ ሰላምና ጸጥታ ለማስከበር ወደ ወረዳው የገባው የ57ኛ ክፍለ-ጦር የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ከሌሎች የጸጥታ መዋቅር አባላትና ከህዝቡ ጋር በመተባበር በአጭር ጊዜ ሰላም ለማጽናት የሚያስችሉ ውጤቶችን እያስመዘገበ እንደሚገኝ ገልጸው ህይወቱን እየሰጠ ሰላም እያረጋገጠ ለሚገኘው ሠራዊት የተደረገው የእርድ እንስሳ ድጋፍ ግዳጅን በላቀ ሁኔታ ለመወጣት እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡
አክለውም ዋና አስተዳዳሪው በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ነፍጥ አንግበው ህዝብን ሲያሰቃዩ የነበሩ ወጣቶች በምህረት እየገቡ መሆኑን አንስተው መንግስት ሠላምና ጸጥታን ለማረጋገጥ ከጦርነት ውጭ ያሉ ሰላማዊ የድርድርና የምህረት በሮችን የዘረጋ በመሆኑ በጫካ የሚገኙ ወንድሞች ከግጭትና ጦርነት የምናተርፈው የሀብት ውድመት፣ የአካል ጉዳትና የህይወት መስዕዋትነት መሆኑን ተገንዝበው የሰላም አማራጮችን በመቀበል ህዝባቸውንና ሀገራቸውን እንዲክሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሀገር መከላከያ ሠራዊት በ403ኛ ኮር የ57ኛ ክፍለ-ጦር ለውጊያ ድጋፍ አገልግሎት ምክትል አዛዥ ሌትናል ኮሎኔል ቴዎድሮስ ዘመነ በበኩላቸው ከወረዳ አስተዳደሩና ከአካባቢው ህዝብ ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው ከሌሎች የጸጥታ መዋቅር አባላት ጋር በመቀናጀት የሚከፈለውን መስዕዋትነት በመክፈል የህዝባችን ስቃይና መከራ የሚያበቃበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም ብለዋል፡፡
ጎንደር ዙሪያ ወረዳ ኮሙኒኬሽን
እየተደረገ ያለው ግጭት በአንድ ህዝብ ልጆች መካከል መሆኑን ያነሱት ሌትናል ኮሎኔል ቴዎድሮስ ዘመነ ሳይገባቸው የውጭ ጠላቶችን ተልዕኮ ይዘው የህዝብን ስቃይ በሚያራዝምና የሀገርን ልማት በሚያደናቅፍ ዓላማ በሌለው ውጊያ የተሰለፉ ወጣቶች በምህረት ወደ ህዝቡ በመቀላቀል ሰላማዊ ህይወት ለመኖር ለሚወስኑ ወንድሞቻችን መከላከያ ሠራዊቱ አስፈላጊውን የህይወት ዋስትናና እንክብካቤ ይሰጣል ብለዋል፡፡