05/09/2026
በዞኑ የሚገኙ ከተሞች በማሳደግ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰሩ ያሉ አበረታች ስራዎች በቀጣይም ይበልጥ ማጠናከር ይገባል:- አቶ አበራ ወንድሙ
ነሀሴ 30/2018ዓ.ም(ጉንችሬ) የጉራጌ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ የ2018 በጀት አመት ማጠቃለያ ሴክቶሪያል ጉባኤ "አንድነት ለጽዳት፣ ትጋት ለአገልግሎት፣ ውሳኔ ለልማት" በሚል መሪ ቃል የምክክር መድረክ በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።
የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ እንዳሉት በዞኑ የሚገኙ ከተሞች ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የህብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
ለዚህም በዞኑ ከተሞች በህብረተሰብ ተሳትፎ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን አንስተው፤ በቀጣይም የከተሞቹ እድገት በማረጋገጥ ማህብረሰቡን የሚመጥኑ ለማድረግ ህብረተሰቡን ይበልጥ በማሳተፍ መስራት ይገባል ብለዋል።
በከተሞች ለህብረተሰቡ የምሰጠውን የአገልግሎት በላቀ ደረጃ ማሳደግ እንደሚገባ ያነሱት አቶ አበራ ከዚህም ባለፈ ህገወጥ የመሬት ወረራና ግንባታ መከላከል ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ከተሞች ያላቸውን የመሬት ሀብት በተገቢው ማወቅና መምራት እንዳለባቸው ጠቁመው፤ ከዚህም ባለፈ ከተሞቹ ይበልጥ ለማሳደግ ያላቸውን የገቢ አርዕስት በመለየት ገቢ መሰብሰብ ላይ በልዩ ትኩሩት መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
የጉራጌ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ፈቀደ እንዳሉት ከተሞች ነጋቸውን ሳይስቱ በፕላን መሰረት እንዲያድጉ ከማድረግ ባሻገር ለነዋሪዎች ምቹና ጽዱ እንዲሆኑ የቆሻሻ አወጋገድ ስርአት ማሻሻል ላይ በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል።
በከተሞች እየተገነቡ ያሉ የኮሪደር ልማት ስራዎች በጥራትና በፍጥነት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት ማድረግ እንዳለባቸውም አንስተዋል።
በዞኑ የሚገኙ ከተሞች በማሳደግ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰሩ ያሉ አበረታች ስራዎች በቀጣይም ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የጉራጌ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ትብለጥ እስጢፋኖስ በበኩላቸው በ2018 በጀት አመት በዞኑ የሚገኙ ከተሞች ከፍተኛ መነቃቃትና ተጨባጭ ዕድገት ማስመዝገባቸውን አመላክተዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ህብረተሰቡ በጥሬ ገንዘብ፣ በጉልበት፣ በቁሳቁስ ከ7 መቶ 22 ሚሊዮን ብር በላይ አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በዚህም 70 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ግንባታና 149 ነጥብ 7 ኪሎሜትር ከፈታ ከማድረግ ባሻገር 62 ነጥብ 57 የመብራትና 77 ነጥብ 4 የውሃ መስመር ዝርጋታ ማከናወን መቻሉንም ተናግረዋል።
በዞኑ በ5ቱም ከተማ አስተዳደሮች 15 ነጥብ 34 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት እየተገነባ መሆኑን ያነሱት ወይዘሮ ትብለጥ በዚህም በእስካሁኑ 7 ነጥብ 6 ኪሎሜትር ማጠናቀቅ ተችሏል ብለዋል።
ይህም ከተሞች ለስራና ለመኖሪያ ምቹ እንዲሆኑ ከማድረግ ባለፈ ውበታቸው እንዲገለጥ እንዳደረገም አንስተው፤ ከዚህም ባለፈ የገጠር ኮሪደር ልማት ስራ በጥራትና በስፋት እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
በሁለተኛ ዙር የአንድ ከተማ አንድ ፕሮጀክት ኢንሼቲቭ 28 ፕሮጀክቶች በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት ማድረግ ተችላል ነው ያሉት።
የህብረተሰቡን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመቅረፍና ተገልጋዮችን በፍትሃዊነት ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት ማዘመን ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች እንዳሉት በዞኑ የህብረተሰብ ተሳትፎ በማጠናከር ከተሞች ለማሳደግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን አንስተው ይህ በቀጣይም ሊጠናከር ይገባል።
ከተሞች ይበልጥ ለማሳደግ በፕላን መምራት፣ ህገወጥነትን መከላከልና የገቢ አርዕስቶችን አሟጦ መሰብሰብ ላይ በትኩሩት እንደሚሰሩም ተናግረዋል።
በመጨረሻም የመምሪያው ኃላፊ ከታችኛው መዋቅር ጋር የ2019 በጀት አመት የግብ ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን በ2018 በጀት አመት የላቀ አፈጻጸም ያስመዘገቡ 1ኛ,ጉመር፣ 2ኛ, እዣና 3ኛ, አበሽጌ ወረዳዎች ሲሆኑ ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት 1ኛ, እምድብር፣ 2ኛ, ጉንችሬና 3ኛ,አገና በመሆን እውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
እንዲሁም ከወረዳዎች የገደባኖ ጉታዘር ወለኔ ወረዳና ከከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ልዩ ተሸላሚ ሆነዋል።
የዞኑ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ነው