14/08/2026
የዘላቂ ልማት ግቦች (SDGs) የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 ዕቅድ ላይ ውይይት ተካሄደ::
ነሐሴ 8/2018
* * * *
በሐረሪ ሕዝብ ክልላዊ መንግሥት የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ አዘጋጅነት፣ የግብርና ቢሮ፣ የውሃ ፍሳሽ አገልግሎት ባለሥልጣን፣ የኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ እና የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ የዘርፍ አስተባባሪዎችና ባለሙያዎች በተገኙበት የዘላቂ ልማት ግቦች (SDGs) የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት ቅድመ ዕቅድ ውይይት መድረክ ተካሄዷል።
ውይይቱን በንግግር የጀመሩት የቢሮው ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ያህያ አብዱራሂም መድረኩ ያለፈውን ዓመት ጥንካሬዎችና ድክመቶች ለመገምገም እና የቀጣይ ዓመት ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ ያለውን ወሳኝነት ገልጸዋል። የልማት ግቦቹን መሬት ላይ በማውረድ የህዝብን ኑሮ ማሻሻልና የሀገሪቱን የዕድገት ጉዞ ማቀላጠፍ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን አንስተው ባለፈው ዓመት በተለያዩ ዘርፎች በርካታ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል። አክለውም አሁን የታዩ ስኬቶችን አጠናክሮ ክፍተቶችን የማረሚያ ወሳኝ ጊዜ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በመድረኩ ባለድርሻ ተቋማት በበጀት ዓመቱ ያከናወኗቸውን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቶች እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ አቅርበዋል። በሪፖርቶቹ እናእቅዶች ላይም ተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት በማድረግ በጥልቀት ገምግመዋል።
በውይይቱ ወቅት በዋናነት በጀትን ለታለመለት ዓላማ ብቻ ማዋል፣ የፋይናንስ ደንቦችን በጥብቅ መከተል፣ የግዥ ሥርዓትን በጊዜ ማጠናቀቅ እና የኦዲት ግኝቶችን በመቀነስ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ላይ ትኩረት ተሰጥቷል። በተጨማሪም የወርሃዊ እና የሩብ ዓመት ሪፖርት አቅርቦትን ተቋማዊ ማድረግ እንዲሁም የመስክ ጉብኝት ፕሮግራሞችን በጊዜ ሰሌዳ መሠረት ማከናወን ይገባል ተብሏል።
በሌላ በኩል በ2018 በጀት ዓመት ለተለዩ ድክመቶች የማሻሻያ እርምጃዎችን በ2019 ዓመታዊ ዕቅድ ውስጥ ማካተት፣ ለፕሮጀክቶች ቅድመ ዝግጅት ማሳወቅ፣ የአካባቢ ተጽዕኖ ጥናት መሠራቱን ማረጋገጥ እና የፕሮጀክት መለያ ታፔላዎችን ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል። ከዚህም በላይ በየዘርፉ ለስንት ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጠር በዕቅዱ ላይ በግልጽ መገለጽ እንዳለበት የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።
በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ የቢሮው ምክትል ቢሮ ኃላፊ መድረኩ መሠረታዊ የአፈጻጸም ጉዳዮችን በዝርዝር ዳስሶ የጋራ መግባባት ላይ መድረሱን ጠቅሰው የተሳታፊዎች ውይይት ፍሬያማና ገንቢ እንደነበር ገልጸዋል። ውይይቱ ለቀጣዩ በጀት ዓመት ሥራዎች ጠንካራ መነሻ እንደሚፈጥር ሙሉ እምነት እንዳላቸው በመግለጽ መድረኩን አጠናቀዋል።
www.hararibof.gov.et
[email protected]
F.b.www.facebook.com/HBoFED
TikTok.https://www.tiktok.com/.bofec
T.me:- https://t.me/HBoFEC