08/05/2026
➡️ሐረር፡ የጥበብ ማህፀንና የእጆች ተአምር!
ሐረር የጥበብና የዕደ-ጥበብ መፍለቂያ ብቻ ሳትሆን ጥበብ ራሷ በሰው ልጅ እጅ ሥጋ ለብሳ የምትኖርባት ሕያው ከተማ ናት። የሐረር ዕደ-ጥበብ በጊዜ ብዛት የማይደበዝዝ በዘመናዊነት የማይተካ የጥበብ ምንጭ ነው። ጀጎልን መጎብኘት ታሪኳን እና ማራኪ ህንፃዎቿን መመልከት ብቻ ሳይሆን በእነዚያ እጆች ውስጥ የሚኖረውን የጥበብ ነፍስ መረዳት ጭምር ነው።ሐረሪዎች በጌጣጌጥ፣ በእንጨት ውጤቶች፣ በድንጋይ ቅርጻ ቅርፅ እና በአላላ ስፌት ያላቸው ጥበብ ለዘመናት የዘለቀ ማንነታቸው መገለጫ ነው። ከእነዚህ የጥበብ ውጤቶች መካከል ደግሞ "ወቅሪ" (Waqri) የተሰኘው የአንገት ሐብል በልዩ የታሪክና የባህል ቦታው ጎልቶ ይታያል።
📿 ወቅሪ፡ ከአንገት ጌጥነት በላይ!
ወቅሪ ለሐረሪ ሴቶች የውበት ብቻ ሳይሆን የክብርና የሥርዓት መገለጫ ነው። ዋና ዋና አገልግሎቶቹም፦
ወቅሪ በሀረሪ ሴቶች ዘንድ ሙሽሪት በሰርጓ ወቅት (በአሩዝ መዋለል) የምትለብሰው፣ እንዲሁም ቀለም መስበር ማለትም የቁርአን 30 ጁዝ ቀርታ የጨረሰች ሴት በምርቃቷ እለት በአንገቷ የምታደርገው የጌጥ አይነት ነው። በተጨማሪም የሙሽሪት እናት በቅልቅል ወቅት የምትለብሰው የአንገት ጌጥ ነው።
የሚገርመው የታሪክ እውነታ፦ በቀድሞ ዘመን "ወቅሪ" እንደ ጌጥ ብቻ ሳይሆን እንደ ትንሽዬ የሀብት ማከማቻ (Safe box) ያገለግል ነበር። ክዳኑ ተከፍቶ ውስጥ የከበሩ ወርቆች፣ ገንዘብና ጠቃሚ ወረቀቶች ይቀመጡበት ነበር። ይህ ድንቅ የጥበብ ውጤት ትላንት በኩራት ሲጠቀሙበት የኖረ ዛሬም ለማንነታቸው ድምቀት እየተጠቀሙበት ያለና ለወደፊትም ለተተኪው ትውልድ የሚተላለፍ የሐረር ሕያው ቅርስ ሆኖ ይዘልቃል።
🔥 የአሰራሩ ጥበብና ጥሬ ዕቃዎች
አንድን "ወቅሪ" ለዓይን ማራኪ ለማድረግ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎች ከፍተኛ ጥረትና ትዕግሥት ያደርጋሉ። የሚሠራባቸው ማዕድናትም፦
• ወርቅና ብር (Gold & Silver)
• ነሐስ፣ መዳብና አሉሚኒየም (Bronze, Copper & Aluminum)
🛠 የአሰራር ሂደት፦
1. መቅለጥና መፈጠር
ጥሬ ዕቃዎቹ (ብር፣ ወርቅ ወይም ሌሎች ማዕድናት) በከፍተኛ ሙቀት እንዲቀልጡ ይደረጋል።
• የሙቀት መጠኑ፦ እንደ ብር ያሉ ማዕድናት የመቅለጫ ነጥባቸው 961.8 °C አካባቢ ሲሆን ወርቅ ደግሞ ከ100 °C በላይ ለማዕድኑ መቅለጥ ወሳኝ የሆነውን ከፍተኛ ኃይል ያሳያል።
• ፈሳሽነት፦ ማዕድኑ ሙሉ በሙሉ ወደ ፈሳሽነት ከተቀየረ በኋላ ወደሚቀጥለው ምዕራፍ እንዲሸጋገር በልዩ መያዣ ተደርጎ ይዘጋጃል።
2. ቅርጽ ማስያዝ
ማዕድኑ ከቀለጠ በኋላ እንደፈለጉት እንዲሆን የማድረግ ሂደት ይከተላል።
• መወጠር ፦ የቀለጠው ማዕድን ከቀዘቀዘ በኋላ ወደ ቀጭን ሽቦነት እንዲቀየር በልዩ ቀዳዳዎች ውስጥ ይሳባል። ይህም ለማስጌጫ የሚሆኑ ጥቃቅን ክሮች ለማዘጋጀት ይጠቅማል።
• መጠፍጠፍ ፦ ማዕድኑን በመዶሻ በመምታት ወይም በመጭመቂያ በማሳለፍ ወደ ስስ ሉህነት እንዲቀየር ይደረጋል። ይህ ለጌጣጌጡ መሠረት ወይም "መሬት" የሚሆን ጠፍጣፋ አካል ለመፍጠር ያገለግላል።
3. የ"ሱፍሪ" (Sufri) ጥበብ እና የማስጌጥ ሂደት
"ሱፍሪ" በሃረሪ የጌጣጌጥ አሰራር ውስጥ እጅግ የተከበረና ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ የጌጥ ስልት ነው።
• ረቂቅነት፦ ሱፍሪ ማለት በጣም ቀጫጭን የሆኑ የወርቅ ክሮችን በመጠቀም በጌጣጌጡ ላይ እንደ ጥልፍ የሚሰሩ የጂኦሜትሪክ ቅርጾችና አበባዎች ናቸው።
• ሽብረቃ፦ በዚህ ሂደት ላይ ትናንሽ የብረት ዘሮች ወይም ኳስ መሰል ቅርጾች በጌጣጌጡ ላይ ይለጠፋሉ። ይህም ለጌጣጌጡ ወጣ ገባ ያለ እና ለዓይን ማራኪ የሆነ ውበት ይሰጠዋል።
• ጥበቡ፦ ሱፍሪ ዝም ብሎ ማስጌጥ ሳይሆን የእጅ ባለሙያው ያለውን ትዕግስትና ረቂቅ የኪነ-ጥበብ ችሎታ የሚለካበት ነው። እያንዳንዱ ሽቦና ቅንጣት እርስ በእርሳቸው ተገጣጥመው በአንድነት እንዲቆሙ በልዩ የብየዳ ዘዴ ይጣበቃሉ።
✨ ሐረር የጥበብና የዕደ-ጥበብ መፍለቂያ ከተማ ናት! ✨
ባህላችንን እንወቅ፣ ቅርሳችንን እንጠብቅ።
📍 ምንጭ፦ የቅርስ ዳ/ዳይሬክተር
📅 ሚያዝያ 30/2018 ዓ.ም