23/05/2026
በአሚር ኑር ወረዳ ታላቅ የምረጡኝ ቅስቀሳ ተካሄደ
በአሚር ኑር ወረዳ ቀበሌ 02 የብልፅግና ፓርቲን የምረጡኝ ቅስቀሳ አስመልክቶ ደማቅ የ“ቡና ጠጡ” መርሃ ግብር ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የጀጎል ኮሪደር ልማትን ጨምሮ በክልሉ የተከናወኑ ግዙፍ የልማት ስራዎች የወጣቶችና የሴቶችን ሁለንተናዊና ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ መሆናቸው ተገልጿል።
በመረሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የሐረሪ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ ኃላፊ ወይዘሮ ዚነት ዩሱፍ፤ ፓርቲው ሴቶችንና ወጣቶችን ያካተተ፣ በተግባር የሚታይ የልማትና የብልፅግና ጉዞ እያረጋገጠ መሆኑን አብራርተዋል።
ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ በመፍጠር እና በመፍጠን ስራ መርህ እየተገነባ የሚገኘው አዲስ የስራ ባህል፣ ወጣቶች ሌትና ቀን በመታተር ለሀገራቸውና ለክልላቸው ዕድገት ታሪካዊ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ማስቻሉንም ገልፀዋል።
የህዝባችን የዘመናት ቁጭት ወደ ድል በተለወጠበት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የወጣቶች አሻራ የጎላ እንደሆነ ሁሉ፣ በታሪካዊቷ የሐረር ከተማ ባለፉት ዓመታት የተከናወነው የጀጎል ኮሪደር ልማት የዚሁ ስኬት ትልቅ ማሳያ መሆኑ በመድረኩ አንስተዋል።
በተለይም የጀጎልን ታሪካዊና ባህላዊ እሴት በጠበቀ መልኩ የኮሪደር ልማቱ መከናወኑ ከተማዋን ለነዋሪዎች ምቹ፣ ለቱሪስቶች ደግሞ ይበልጥ ሳቢና ማራኪ አድርጓታል ብለዋል።
በኮሪደር ልማቱ የመንገድ መብራቶች በፅዳትና ውበት እንዲሁም በተያያዙ የልማት ስራዎች ላይ ሰፊ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች በጉልበታቸው፣ በእውቀታቸውና በገንዘባቸው ታሪካዊ አሻራቸውን ያሳረፉ ሲሆን፣ ሰፊ የስራ ዕድል ተጠቃሚ መሆን ችለዋል ሲሉ ተናግረዋል።
በዚህ ፈጣን ዕድገት በሺዎች የስራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውንና ብዙዎችም የኑሮ ደረጃቸውን በእጅጉ ማሻሻላቸውን ኃላፊዋ ገልጸዋል።
የሐረር ከተማም ሆነ የአጠቃላይ ሀገሪቱ ተምሳሌታዊ ዕድገት እውን ሊሆን የቻለው የወጣቶችን እና የሌላውንም የህብረተሰብ ክፍል እምቅ አቅም በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ያስቻለው አካታቹ የ“መደመር ፍልስፍና” ተግባራዊ መሆን መጀመሩ እንደሆነ ተመላክቷል።
በመጨረሻም ወይዘሮ ዚነት ዩሱፍ የጀጎል ኮሪደር ልማትን ጨምሮ የተከናወኑ የልማት ስራዎች የፓርቲው በተግባር የተረጋገጠ ጉዞ ውጤቶች መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ማህበረሰቡ ለፓርቲው የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልና ነገን ዛሬ እየገነባ፣ ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን እያረጋገጠ የሚገኘውን ብልፅግና ፓርቲን እንዲመርጥ ጥሪ አቅርበዋል።
የመደመር፣ የትብብር እና የአንድነት መገለጫ የሆነው የስንዴ ነዶ እንድመርጡ ጥሪ አስተላልፈዋል።
#ምርጫ2018