12/07/2024
26ኛው አለም ዓቀፍ የሐረር ቀን በዓል በክልሉ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ለማጎልበት አቅም የፈጠረ እንደነበር የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ አስታወቁ።
በክልሉ ሲከበር የቆየው 26ኛው ዓለም ዓቀፍ የሐረር ቀን በዓል ተጠናቋል።
በበዓሉ ማጠናቀቂያ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ እንደገለጹት በዓሉ በክልሉ የተጀመሩ የልማት ስራዎች እንዲነቃቁ እድል ፈጥሯል።
በተለይ በዓሉን በድምቀት ለማክበር ህዝቡና አመራሩ በመቀናጀት በክልሉ ከተማና ገጠር የመሰረተ ልማት ግንባታ፣ በጽዳትና ውበት እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች አበረታች የልማት ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በዓሉ የልዩነትና የመገፋፋት ሳይሆን የአብሮነትና የአንድነት፣ የመደጋገፍና አብሮ የመስራት ባህል የጎለበተበት መሆኑን በተግባር መታየቱንና ስኬታማ እንደነበርም ገልጸዋል።
ለበዓሉ ስኬታማነትም በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆችና አመራሩ ተናቦ እና ተቀናጅቶ በመስራቱ የተገኘ ውጤት መሆኑንም ጠቁመዋል።
በበዓሉ ላይ ለመሳተፍ የመጡ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሀገሪቱና በክልሉ የተከናወኑ የሰላም፣ የልማትና ሌሎች ስራዎችን ተመልክተው ምስክር የሰጡበት መሆኑን ተናግረዋል።
እንዲሁም በክልሉ የተከናወኑ አጠቃላይ የልማት ስራዎች መመረቃቸውን እና የኢንቨስትመንት አማራጮችንም መመልከታቸውን ጠቅሰው ይህም አበረታች መሆኑን ገልጸዋል።
ሀገራዊ ጥሪውን ተከትሎ ወደ ሀገር በመምጣት ተሳትፎ ላደረጉ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም ምስጋና አቅርበዋል።
በቆይታቸውም ያጎለበቱትን መልካም ትስስር በቀጣይም በኢንቨስትመንት፣ በዲፕሎማሲ፣ በስራ እድል ፈጠራ፣ በልማትና በሌሎች መስኮች ይበልጥ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮ ሃላፊ አቶ ተወለዳ አብዶሽ በበኩላቸው በዓሉ "ሐረር የሰላም፣ የመቻቻልና የአብሮነት ተምሳሌት" በሚል መሪ ሃሳብ መከበሩን አስታውሰዋል።
በዓሉም የክልሉን የልማት ስራዎች እንዲጎለብቱ እና ገጽታ መገንባት ማስቻሉን ተናግረዋል።
በበዓሉ ላይ ለመሳተፍ የመጡ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተለያዩ የልማትና የበጎ ፈቃድ ስራዎች ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ እድል መፍጠሩን አክለዋል።
በበዓሉ ማጠናቀቂያ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ፣ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሮዛ ኡመር፣ የሐረሪ ብሔራዊ ጉባዔ አፈ ጉባዔ አቶ ሙህየዲን አህመድ ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ ዳያስፖራዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።
በእለቱም ለበዓሉ መሳካት አስተዋፅኦና ተሳትፎ ላደረጉ አካላት የምስክር ወረቀትና እውቅና ተሰጥቷል።