02/06/2026
ኢትዮጵያውያን በሰላማዊ መንገድ መርጠዋል፤ ኢትዮጵያ አሸንፋለች- የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
ኢትዮጵያውያን በ7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ መንገድ በመምረጥ ኢትዮጵያን አሸናፊ አድርገዋል ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
ጠቅላላ ምርጫው በሰላማዊ ሁኔታ በስኬት መጠናቀቁንም አመልክቷል።
አገልግሎቱ ባወጣው ይፋዊ መግለጫ ኢትዮጵያውያን መርጠዋል፤ ኢትዮጵያ አሸንፋለች! ሲል ገልጿል።
አገልግሎቱ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመላከተው፣ ኢትዮጵያ ከዜጎቿ የፈለገችውን ሁሉ በፈለገችው ጊዜና ሁኔታ የምታገኝ ሀገር መሆኗንና ለሀገራቸው የተጠየቁትን ሁሉ ለመስጠት ወደኋላ የማይሉ ዜጎች ስላሏት በእጅጉ እንደምትኮራ ገልጿል።
ከዓድዋ እስከ ሕዳሴ ግድብ፣ ከወገን ለወገን መረዳዳት እስከ አረንጓዴ ዐሻራ የዜጎቿን ተሳትፎ ጠይቃ ከመሻቷ በላይ እንደተሳካላትና ዛሬም የተደገመው ይኸው እንደሆነ አብራርቷል።
ኢትዮጵያ ዴሞክራሲን ለማንበር፣ በግልጽና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ መንግሥትን ለመምረጥ እንዲሁም ሕገ-መንግሥታዊነትን ፅኑ መሠረት ለማስያዝ እንደምትሻ የጠቀሰው መግለጫው፤ ለዚህ ደግሞ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ እንደ ትልቅ አጋጣሚ መጠቀም ማስፈለጉን አስታውቋል።
ለዚህ አገራዊ ጥሪ በምላሹ ከ54 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለመራጭነት ተመዝግበው ቀኑን ሲጠባበቁ መቆየታቸውንና የእናት ሀገር ጥሪን በመቀበልም በነቂስ ወጥተው ሲመርጡ መዋላቸውን አገልግሎቱ ገልጿል።
መራጮች ሌሊቱንም ጭምር አጋምሰው ድምፅ የሰጡ ሲሆን፣ ይህም በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ ዜጎች ለረዥም ሰዓታት ተሰልፈው ድምፅ የሰጡበት ልዩ ምርጫ ያደርገዋል ብሏል።
ምርጫው እንዳይካሄድ ባዳ እና ባንዳ ተቀናጅተው ያልቆፈሩት ጉድጓድና ያልደረደሩት እንቅፋት እንዳልነበረ የጠቀሰው መግለጫው፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ ለጠራችው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ የማይቻል ነገር ባለመኖሩ ሂደቱ በስኬት መጠናቀቁንና ኢትዮጵያውያን በሰላማዊ መንገድ መርጠው ኢትዮጵያ ማሸነፏን አረጋግጧል።
የኢትዮጵያን የዴሞክራሲያዊ ምርጫ ጥሪ ተቀብሎ ከንጋት እስከ ምሽት በመምረጥ ምላሽ ለሰጠው ሕዝብ፣ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ እንዲጸና እና ዜጎች በሰላም እንዲመርጡ ምቹ ዓውድ ለፈጠሩ የፀጥታ አካላት፣ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ በየደቂቃው ሲያደርሱ ለነበሩ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት እንዲሁም የምርጫውን ሂደት ለመሩ፣ ላስተባበሩ እና ለታዘቡ ሁሉ ኢትዮጵያ የላቀ ምስጋና ታቀርባለች ሲል አገልግሎቱ አስታውቋል።