22/08/2026
የሀረሪ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞችና አመራሮች በማረሚያ ፖሊስ ኮሚሽን የመስክ ምልከታና የድጋፍ መርሃ ግብር አካሄዱ
የሀረሪ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ሰላሃዲን እና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች በሀረሪ ማረሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በመገኘት የክረምት በጎ መርሃ ግብርን ምክንያት በማድረግ ለህግ ታራሚዎች ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን፣ የኮሚሽኑን ሁለንተናዊ የስራ እንቅስቃሴም የመስክ ምልከታ አድርገዋል።
በዚህ የመስክ ምልከታ ወቅት የሁለቱ ተቋማት የቅርብ ቅንጅታዊ አሰራር ውጤታማነት እና የታራሚዎች የእርምት ሁኔታ በስፋት ተገምግሟል።
የሀረሪ ማረሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አድናን አህመድ እንደገለጹት፤ ቀደም ሲል በፍርድ ቤቶች በኩል በወንጀል ጥፋተኛ ተብለው ወደ ማረሚያ ኮሚሽኑ በሚላኩ የህግ ታራሚዎች ላይ ያለቀጠሮ እና የፍርድ ሂደት መዘግየት ምክንያት በርካታ ክፍተቶች ይታዩ ነበር።
ሆኖም በሁለቱ ተቋማት መካከል በተፈጠረው በጎና የቅርብ የጋራ ስራ ላለፉት ጊዜያት በተደጋጋሚ ሲነሱ የነበሩ አቤቱታዎችንና ጥያቄዎችን ሙሉ በሙሉ ለመፍታት መቻሉን ገልፀው፣ ይህ ቅንጅት የፍትህ ሂደቱ ፈጣንና ቀልጣፋ እንዲሆን ማድረጉን አስረድተዋል።
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ሙራድ አብዱላሂ በበኩላቸው፤ የጠቅላይ ፍርድ ቤት አመራሮች እና ዳኞች ያካሄዱት የክረምት በጎ መርሃ ግብር እንዲሁም የተደረገው የመስክ ምልከታ ከፍተኛ አዎንታዊ ተፅዕኖ እንዳለው ገልጸዋል።
ምክትል ኮሚሽነሩ አክለውም፤ የፍርድ ቤት አካላት በማረሚያ ቤት በአካል በመገኘት የታራሚዎችን የእርምት፣ የሙያ እና የስነ-ልቦና ማነፅ ሁኔታ በቅርበት መመልከታቸው ለፍትህ ስርአቱ መሻሻል እና ለህግ ታራሚዎች ሰብአዊ መብት አያያዝ መጎልበት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
በተጨማሪም የጠቅላይ ፍርድ ቤት አመራሮችና ዳኞች በህግ ታራሚዎች የማሳያ እርሻ ልማት ቦታ በመገኘት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ያካሄዱ ሲሆን፣ በዚህም የአካባቢ ጥበቃና የአረንጓዴ ልማት ጥረቱን ደግፈዋል።
መርሃ ግብሩ የተጠናቀቀው የጠቅላይ ፍርድ ቤት አመራሮችና ዳኞች ለህግ ታራሚዎች ያዘጋጁትን ልዩ ልዩ ድጋፎች በማስረከብ እና በቀጣይም በሁለቱ ተቋማት መካከል ያለው አጋርነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በማረጋገጥ ነው።
ዘጋቢ :- ኮማንድር መህዲ