14/02/2024
በሀዲያ ዞን አንዳንድ ወረዳዎች ላይ ለተከሰተው የኩፍኝ ወረርሽኝ ምላሽ አሰጣጥ ሂደት ማጠናከሪያ መድረክ ተካሄደ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀዲያ ዞን በ5 ወረዳዎች ላይ የተከሰተውን የኩፍኝ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር ባለፉት ሁለት ወራት ከክልል ጤና ቢሮ፣የህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት አመራርና ባለሙያዎች ጀምሮ እስከዞን በተደረገው የተጠናከረ የድጋፍና ክትትል ተግባር፣የግብአት አቅርቦት እና በተደረጉ ልዩ ልዩ ድጋፎች በሽታውን በፍጥነት ከመዛመት በመከላከል ሊከሰት የሚችለውን ሞት መከላከል የተቻለ ቢሆንም ወረርሽኙን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ባልቻሉ አንዳንድ ወረዳዎች ላይ የቅኝት እና ምላሽ አሰጣጥ ተግባራትን ይበልጥ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ በውይይት መድረኩ ላይ ተገልጿል ፡፡
በተለየ መልኩ የባለሙያና የአመራር ትኩረት ይሻሉ የተባሉ ወረዳዎች ተለይተው በቀጣይ ትኩረት አድርገው በሚሰሩባቸውን ሂደቶች ላይ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
የኩፍኝ በሽታ በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው በፍጥነት የሚዛመትና ህፃናትን ለከፋ ጉዳትና ከፍ ሲልሞ ለሞት የሚዳርግ አደገኛ በሽታ በመሆኑ የክልል ጤና ቢሮና የህ/ብ ጤና ኢኒስቲትዩት ችግሩ በተከሰተባቸው መዋቅሮች የማኔጅመንት አካላትና ከፍተኛ ባለሙያዎችን በማቀናጀት ረዘም ላለ ጊዜ ቦታው ድረስ ወርደው እንዲደግፉ በማድረግ የተመዘገቡ መልካም ውጤቶችን በማስቀጠል ወረርሽኙን በአጭር ጊዜ ለመግታት መረባረብ ይገባል ተብሏል ፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ሽመልስ ዋንጉሮ እና የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም መጫ በጋራ ባስቀመጡት አቅጣጫ የወረዳ አስተዳዳሪዎች ፣የጤና ጽ/ቤት ሃላፊዎች፣የፓርቲ ጽ/ቤት ሃላፊዎች የፖሊቲካና ርዕዮተ አለም ዘርፍ ሃላፊዎች እንዲሁም የዞን ጤና መምሪያ የተለያዩ የስራ ክፍሎች ተቀናጅተው በመስራት የተከሰተውን የኩፍኝ ወረርሽኝ በጥቂት ቀናት ውስጥ ማቆምን ጨምሮ በወባ መከላከልና መቆጣጠር እንዲሁም በሌሎች ጤና ነክ ተግባራት ላይ ተጨባጭ ውጤት እንዲያስመዘግቡ በአፅንኦት አሳስበዋል፡፡