30/08/2026
ያሆዴ ከዘመን መለወጫ በዓልነት ባሻገር የማህበራዊ ካፒታል፣ የሰላምና የባህላዊ ኢኮኖሚ መሠረት መሆኑ ተገለጸ
ፎንቆ:- ነሓሴ 24/2018 (የአንሌሞ ወረዳ ኮሙኒኬሺን)
የሀድያ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል የሆነው ያሆዴ የማህበረሰቡን ማህበራዊ ካፒታል ጠብቆ ለማቆየት፣ ሰላምና እርቅን ለማስፈን እንዲሁም ባህላዊ እሴቶችን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ የጎላ ሚና እያበረከተ እንደሚገኝ ተገለጸ።
በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም «ያሆዴ የሀድያ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል» መጽሐፍ አዘጋጆች አንዱ የሆኑት መምህር መለሰ አቢዴ ከሀድያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በዓሉ በዘመናዊነትና በለውጥ ሂደት ውስጥ በሚገኝ ማህበረሰብ ውስጥ ማህበራዊ ትስስርን ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።
መምህር መለሰ እንዳብራሩት፤ ያሆዴ ሰዎች በጋራ እንዲሰበሰቡ፣ እንዲገናኙና እንዲጠያየቁ በማድረግ የመረዳዳትና የመተማመን እሴቶችን ያስቀጥላል።
ይህም ሃይማኖት፣ ዘመናዊነትና ስደት በባህል ላይ የሚያመጡትን ተጽዕኖ በመቋቋም ማህበራዊ ካፒታሉ ሳይሸረሸር እንዲጸና እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
ባህል የአንድ ማህበረሰብ የማንነት መገለጫ መሆኑን ያነሱት ተመራማሪው፤ ያሆዴ ለአዲሱ ትውልድ «እኛ ማን ነን?» የሚለውን የማንነት ጥያቄ በተግባር የሚመልስና ባህል፣ ቋንቋ፣ ልማድና ታሪክ የሚገለጽበት ትልቅ የትምህርት መድረክ እንደሆነ ገልጸዋል።
በዓሉ ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ያለውን ማህበራዊ መስተጋብር በማጠናከር ረገድ ስላለው ፋይዳ ሲያብራሩም፤ በያሆዴ ላይ አጎራባች ብሔረሰቦች መሳተፋቸው የተሳሳቱ ግንዛቤዎችን በመቀነስ የመከባበር፣ የሰላምና የማህበራዊ ውህደት መድረክ እንዲሆን ማስቻሉን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ያሆዴ የእርቅና የስነ-ልቦና እፎይታ የሚገኝበት መሆኑን የጠቀሱት መምህር መለሰ፤ ተጣልተው የቆዩ ወገኖችና በተለይም የተፋቱ ባልና ሚስት ተመልሰው የሚገናኙበት መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ መምህር መለሰ ማብራሪያ፤ በበዓሉ ወቅት የሚተገበረው ባህላዊ የማህበረሰብ እርቅ ጥፋተኛውን በማግለልና በመቅጣት ፋንታ በምክርና በይቅርታ ወደ ማህበረሰቡ በመመለስ የሰዎችን የስነ-ልቦና እርካታና ማህበራዊ መረጋጋት የሚያረጋግጥ ነው።
በዓሉ በሚከበርበት ወቅት የገንዘብም ሆነ የዕቃ ዱቤ ወይም ብድር (Aabba) ሙሉ በሙሉ እንዲከፈል የሚደረግበት ባህላዊ መመሪያ መኖሩን ተናግረዋል።
ይህም ዕዳ ለቀጣይ ዓመት እንዳይሸጋገር በማድረግ በማህበረሰቡ መካከል የቃል ኪዳን ታማኝነትንና የንግድ ኃላፊነትን ያጠናክራል።
በሌላ በኩል በበዓሉ ወቅት የሚቀርቡ የዕደ-ጥበብ ውጤቶች፣ ባህላዊ አልባሳትና የኪነ-ጥበብ ዝግጅቶች ባህሉ እንዳይጠፋ ከማድረግ ባሻገር ለአካባቢው አምራቾችና አርቲስቶች የገቢ እድል በመፍጠር ለባህላዊ ኢኮኖሚው እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው አብራርተዋል።
በመጨረሻም ያሆዴ «ምንም ለሌለው የሚሰጥበትና ሰዎች በእኩልነት የሚያከብሩት» መሆኑን የገለጹት መምህር መለሰ አቢዴ፤ ሀብት ያለውና የሌለው በእኩል የሚስተናገዱበት፣ ከሰው ባሻገር የቤት እንስሳት እንኳ የሚንከባከቡበት የደግነትና የተካፋይነት በዓል መሆኑን አብራርተዋል።
በስራና በስደት ርቀው የቆዩ የቤተሰብ አባላት ተገናኝተው የጋራ ትውስታቸውን የሚያድሱበት፣ ወጣቶችም ጥንድ የሚሆኑበትና የመተጫጨት እድል የሚያገኙበት ትልቅ ማህበራዊ ተቋም መሆኑን አብራርተዋል።
በመሆኑም ወጣቶች እሴቶቹን የባህሉን ቀጣይነት ማረጋገጥ እንዳለባቸው ተናግረዋል።
#ሀዲያ ቴሌቬዥን #