20/08/2026
የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ከሚሰጠው ሀገራዊ ፈይዳና ጠቀሜታ አኳያ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት መጠናከር እንደሚገባው ተገለጸ
(ሆሳዕና፣ ነሐሴ 14/2018 ዓ.ም) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ ከተጠሪ ተቋማት፣ ከባለድርሻ አካላትና ከስር መዋቅሮች ጋር በ2018 አፈጻጸም እና በ2019 ዕቅድ ላይ በሀላባ ቁሊቶ ከተማ የውይይት መድረክ እያካሄደ ነው።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አበበ ከበደ እንደተናገሩት፤ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ከሚሰጠው ሀገራዊ ፈይዳና ጠቀሜታ አኳያ የባለድርሻ አካላት ቅንጅትን በማጠናከር እየተሠራ ነው ብለዋል።
ኤጀንሲው የዜጎችን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለማረጋገጥ፣ ለአገራዊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ዕቅዶች ትክክለኛ መረጃን በማቅረብ፣ እንዲሁም «እያንዳንዱ ሰው የሚታወቅባት ኢትዮጵያን» ለመገንባት እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ሽፋኑን ለማሳደግ በክልሉ በሚገኙ 7 ዞኖች እና 3 ልዩ ወረዳዎች ከሚገኙ 1,278 የገጠርና የከተማ ቀበሌዎች መካከል በ1,259 ቀበሌዎች ምዝገባው እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ በሁሉም ኩነቶች 155,562 ምዝገባ የተከናወነ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ ልደት 140,280፣ ሞት 5,708፣ ጋብቻ 8,932፣ ፍቺ 628 እና ጉድፈቻ 14 ተመዝግቧል። ከነዚህም ውስጥ 10,572 ኩነቶች በታብሌት የተመዘገቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የምዝገባ አፈጻጸምና የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ አበረታች ውጤቶች የተመዘገቡበት መሆኑን የተናገሩት አቶ አበበ፤ የክረምት የተማሪዎች ልደት ምዝገባ በስኬት መከናወኑን ጠቅሰዋል።
በክልሉ ውስጥ በሚገኙ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ስርጭቶች፣ እንዲሁም በሕትመት ውጤቶች ወቅታዊ መልዕክቶችን በማስተላለፍ የሕብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።
በዲጂታላይዜሽንና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ በተሠሩ ሥራዎች በሁሉም ዞኖች፣ ልዩ ወረዳዎችና ሆስፒታሎች የታብሌት ምዝገባ ሂደት ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱን ተናግረው፤ በቀበሌዎች አገልግሎት ፈላጊዎችን የፋይዳ መታወቂያ የመጠየቅ ባህል መዳበሩ ትልቅ እምርታ ማምጣቱን አመላክተዋል።
የክብር መዝገብ ሹሞች ሥራውን እንደ ተደራቢ ተግባር ማየት እና አገልግሎቱን በሳምንት የተወሰኑ ቀናት ብቻ መስጠታቸው ደግሞ አሁንም እንቅፋት መሆኑን አቶ አበበ ተናግረዋል።
ከአሰራር ውጪ ከአገልግሎት ፈላጊ ዜጎች ተጨማሪ ክፍያ በሚጠይቁና ከደላላ ጋር በመመሳጠር ገንዘብ በመጠየቅ የተሳተፉ 31 የክብር መዝገብ ሹሞችና ተጠራጣሪዎችን በሕግ የማስጠየቅ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይ በሁሉም ኩነቶች ወቅታዊና የዘገየ የምዝገባ ሽፋንን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ እንደሚሠራ የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ በልዩ ልዩ ምክንያት ምዝገባ ያቋረጡ ቀበሌዎች ወደ ምዝገባ ሥራ እንዲመለሱ ማድረግ፣ የታብሌት ምዝገባን በሁሉም መዋቅሮች ማጠናከር እና የመዝጋቢዎችን የክህሎት ክፍተት መሙላት ተጠናክሮ እንደሚሠራ ተናግረዋል።
መድረኩ ጥንካሬዎችን ለማስቀጠል፣ ያጋጠሙ ማነቆዎችን እና በቀጣይ ትኩረት የሚሰጥባቸው ተግባራት ዙሪያ በመምከር መግባባት የሚደረስበት ነው ብለዋል።
የክልሉ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የሕግና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ተወካይ አቶ ግርማ ጊቻሞ በበኩላቸው፤ ሁሉም ሰው የሚታወቅባትን ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ ራዕይ ተሰንቆ እየተሠራ ያለ በመሆኑ፣ ይህንን በሚመጥን ልክ መፈጸም ከሁሉም ይጠበቃል ብለዋል።
ተቋሙ በርካታ ጠንካራ ጎኖች ያሉት ቢሆንም አሁንም የሚስተዋሉ ውስንነቶችን መቅረፍ እንደሚገባውና ምዝገባው በማይከናወንባቸው አካባቢዎች ምዝገባውን በማስጀመር ለዜጎች አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ኤጀንሲው በ2030 ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እየተሠራ ያለውን ሥራ የሚመጥን የቴክኖሎጂ አሰራር ስርዓት በመዘርጋት ኪራይ ሰብሳቢነትን በተገቢው መከላከል እንደሚገባውም ተናግረዋል።
በመድረኩ የክልል ቢሮ ኃላፊዎች፣ የዞንና ልዩ ወረዳ ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አመራሮች፣ የዕድሮች ጥምረት፣ የሆስፒታል ሥራ አስኪያጆችን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፏል ።