04/09/2026
የስልጤ ዞን ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት መምሪያ በወረዳችን ሲያከናውን የቆየውን የ2018 በጀት አመት የማህበራት ቆጠራና ኢንስፔክሽን ስራ አጠናቀቀ!
ነሃሴ29/2018፤ !
ከዞኑ ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት መምሪያ የተውጣጣው የእንስፔክሽን ቡድን በወረዳችን በመገኘት ለዘጠኝ ተከታታይ ቀናት ሲያከናውን የቆየውን የ2018 በጀት አመት የማህበራት ቆጠራና የምዘና ኢንስፔክሽን ስራ በማጠናቀቅ ለወረዳው አስተባባሪ አካላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ግብረመልስ ሰጥቷል።
የምስራቅ አዘርነት በርበሬ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊና የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ሙዲን ሙዘሚል፣ የምስራቅ አዘርነት በርበሬ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ቶፊቅ ከድር፣ የወረዳው ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽ/ቤት ዋና ኃላፊ አቶ ቢረዳ አማን እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን ቡድኑ ለዘጠኝ ቀናት ባካሄደው አጠቃላይ የ2018 በጀት አመት የአፈፃፀም ምዘናና የማህበራት የመስክ ቆጠራ ስራዎችን በጉድለትና በጥንካሬ ግብረመልስ ሰጥቷል።
የእንስፔክሽን ቡድኑ እንደገለፀው በተዘጋጀው ቼክ-ሊስት መሰረት ምዘና መደረጉንና በ2018 በጀት አመት የተደራጁ ማህበራትን በሁሉም ቀበሌያት ቤት ለቤት በመንቀሳቀስ በመስክ ቆጠራ ሲደረግ መቆየቱን በመግለጽ በተገኙ ጥንካሬዎችና ጉድለቶችን ለባለድርሻ አካላት ግብረ መልስ መስጠት እጅግ ወሳኝና አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል።
የተደራጁ ኢንተርፕራይዞች የጠራ መረጃቸው ተይዞ አስፈላጊዉን ሁሉ ድጋፍ በመስጠት በተሰማሩበት የስራ መስክ ላይ ውጤታማ መሆናቸውን ማረጋገጥና በገበያ ውስጥ ብቁ፣ ተወዳዳሪና አሸናፊ ሆነው በመውጣት ከራሳቸው አልፈው በሀገራችን ኢኮኖሚ ላይ የራሳቸውን አሻራ እንዲያኖሩ ማስቻል የኢንስፔክሽኑ ዋና ዓላማ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
የምስራቅ አዘርነት በርበሬ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊና የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ሙዲን ሙዘሚል በወቅቱ እንደገለፁት፦ ግብረመልሱ እጅግ ወሳኝና የተለዩ ክፍተቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማስተካከል እንዲሁም የተሻለ የድጋፍና ክትትል ስርዓት ዘርግቶ ለመፈጸም ቁርጠኝነት የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
አቶ ሙዲን አክለውም በወረዳችን በበጀት አመቱ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው ከዚህ በተያያዘም የተመዘገቡ ስኬቶችን በማስፋፋት እና የታዩ ክፍተቶችን በማረም ለቀጣይ ስራዎች ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራ መሆኑን አንስተዋል።
የምስራቅ አዘርነት በርበሬ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ቶፊቅ ከድር በበኩላቸው ወጣቶችን የስራ እድል ተጠቃሚ ለማድግና የሥራ ዕድል ፈጠራው ዘላቂነት እንዲኖረው ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ክትትልና ድጋፍ ሲያደርጉ መምጣታቸውን ጠቁመው ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።