27/08/2026
አቢዮ ኤርሳሞ ስታዲየምን ከታቀደለት ጊዜ ቀድሞ ለውድድር ለማድረስ እየተሠራ ነው – አቶ ታምሬ ኤርሚያስ
ነሀሴ 20/2018 (ሆሳዕና)
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ባለሙያዎች ቡድን በሆሳዕና አቢዮ ኤርሳሞ መታሰቢያ ስታዲየም ያከናወነውን ሦስተኛ ዙር ምልከታ አጠናቀቀ።
በጉብኝቱ የተገኙት የሀዲያ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ እና የሀዲያ ሆሳዕና እግር ኳስ ክለብ ምክትል ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ታምሬ ኤርሚያስ፣ የፌደራሉ ቴክኒክ ቡድን የጠቆማቸውን ቀሪ ሥራዎች ከተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ቀድመው በመጨረስ ሜዳውን ለውድድር ለማድረስ በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ አስታወቁ።
በ2019 የውድድር ዘመን አዳዲስ ክለቦች ወደ ሊጉ ስለሚቀላቀሉ ተጨማሪ መጫወቻ ሜዳዎች እንደሚያስፈልጉ የጠቆሙት የአክሲዮን ማህበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ፤ የሆሳዕና፣ የሀላባ እና የአርባምንጭ ስታዲየሞች መስፈርቱን አሟልተው እንዲዘጋጁ መመረጣቸውን ገልጸዋል። የፌደራሉ ቡድንም ከዚህ ቀደም የነበሩ ጉድለቶች የተሸፈኑበት ፍጥነት የሚያስመሰግን መሆኑን ጠቅሶ፣ ቀሪ ሥራዎች ጥራታቸውን ጠብቀው በፍጥነት እንዲጠናቀቁ አሳስቧል።
በምልከታው መርሃ ግብር የኢትዮጵያ እግር ኳስ የውድድርና ሥነሥርዓት ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር ወገኔ ዋልተንጉስን ጨምሮ የዞኑ ከፍተኛ የሥራኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።