30/08/2026
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የዱር እንስሳት ጥበቃ ሽፋንን ለማሳደግና ተፈጥሮን በዘላቂነት ለመንከባከብ የተቀናጁ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሚገኝ ተገለፀ
ነሐሴ 24/2018 ዓ.ም
የተፈጥሮ ጸጋዎችንና የዱር እንስሳት ሀብትን በዘላቂነት በመንከባከብ የጥበቃ ሽፋንን ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሚገኙ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ በደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኘውንና 197 ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍነውን "ታማ" የማህበረሰብ የዱር እንስሳት ጥበቃ ቦታ አያያዝና በቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ የመከረበትን የቦርድ ስብሰባ በጂንካ ከተማ አካሂዷል።
የቦርድ መድረኩን የመሩት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ወይንቱ መልኩ፤ የክልሉን የዱር እንስሳት ጥበቃ ሽፋን ለማሳደግ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቁመው፥ "ታማ" የማህበረሰብ ጥብቅ ስፍራ ከእነዚህ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች አንዱ መሆኑን አብራርተዋል።
ኃላፊዋ አክለውም፣ በአካባቢው የሚገኙትን የኦሞ እና የማጎ ብሔራዊ ፓርኮች ሕልውናና የሥነ-ምህዳር ትስስር ዘላቂ በሆነ መንገድ ለማስቀጠል የ"ታማ" ጥብቅ ስፍራ እንክብካቤ ወሳኝና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በታማ የማህበረሰብ የዱር እንስሳት ጥበቃ ስፍራ የተመዘገቡ መልካም ውጤቶች፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ተግባራትን አስመክተው ማብራሪያ የሰጡት የማህበረሰቡ ዋና አስተባባሪ አቶ ባርኬዴ ኩሉሜደሬ ሰፊ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
የቦርዱ አባላትም የተከናወኑ ተግባራትን በመገምገም፣ ጥብቅ ስፍራው የተጣለበትን አገራዊና አካባቢያዊ ኃላፊነት ይወጣ ዘንድ ሁሉ አቀፍ ክትትልና ሙያዊ ድጋፍ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በተጨማሪም የቦርዱ አባላት በታማ ጥብቅ ስፍራ መተዳደሪያ ደንብ እና እስከ አሁን በተከናወኑ አጠቃላይ የሥራ አፈጻጸሞች ላይ ጥልቀት ያለው ውይይት አካሂደዋል።
በቀጣይም ከአካባቢው ማህበረሰቦች ጋር የሚደረገው የጋራ ምክክር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተገለጸ ሲሆን፤ ከደቡብ አሪ ወረዳ የአሪ ማህበረሰብ ተወካዮች እንዲሁም ከሣላማጎ ወረዳ ከዲሜ፣ ከባጫ እና ከሙርሲ ማህበረሰቦች የተወጣጡ አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች በተገኙበት በታማ የዱር እንስሳት ጥበቃ ስፍራ የጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ ሰፊ ውይይት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።