30/08/2026
በከሚሴ ከተማ በምግብ ራስን የመቻል እና ከተረጂነት ወደ ምርታማነት መሸጋገር ላይ የግንዛቤ ፈጠራ መድረክ ተካሄደ።
ነሐሴ 24/2018;ከሚሴ ከተማ አስተዳደር መንግስት ኮሙኒኬሽን።
በከሚሴ ከተማ በምግብ ራስን የመቻል፣ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት መሸጋገር እና የአደጋ ስጋት አይበገሬነትን ማጠናከር ዙሪያ ለአብይ ኮሚቴና ለንዑሳን ኮሚቴዎች የግንዛቤ ፈጠራ መድረክ ተካሄደ።
መድረኩ ዋና ዓላማው የከተማውን ነዋሪዎች በምግብ ራስን እንዲችሉ ማድረግ፣ ከተረጂነት ተላቀው ወደ ምርታማነት እንዲሸጋገሩ የሚያስችሉ አማራጮችን ማጠናከር እና በተለያዩ አደጋዎች ወቅት የመቋቋም አቅምን ማሳደግ ላይ ትኩረት ማድረግ ነው።
በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የከሚሴ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ አረቡ አሊ፣ በምግብ ራስን የመቻልና ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የሚደረገው ሽግግር የከተማዋን የልማት አቅም ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
አቶ አረቡ አሊ የምግብ ራስን መቻልን እውን ለማድረግ የሥራ ቅንጅትን ማጠናከር፣ የማህበረሰቡን ተሳትፎ ማሳደግና ያሉ ሀብቶችን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በመድረኩ የምግብ ራስን መቻል የአንድ ማህበረሰብ ዘላቂ ልማት መሠረት መሆኑን በመገንዘብ፣ የምርታማነት አቅምን ማሳደግ፣ የሥራ ዕድልን ማስፋት፣ የሀብት አጠቃቀምን ማሻሻልና የራስን አቅም በመጠቀም የኢኮኖሚ አቅምን ማጠናከር የሚቻልባቸው አቅጣጫዎች ተዳሰዋል።
በተጨማሪም የአደጋ ስጋት አይበገሬነት ለመገንባት ቅድመ ዝግጅት፣ የስጋት መከላከልና የማህበረሰቡን የመቋቋም አቅም ማጠናከር ያለው ሚና በስፋት ተነስቷል።
በመድረኩ የተካተቱ አብይና ንዑሳን ኮሚቴዎች የተሰጣቸውን ኃላፊነት በተቀናጀ መልኩ በመወጣት፣ የከተማውን ማህበረሰብ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለማሸጋገር በትጋት እንዲሠሩ አቅጣጫ ተሰጥቷል።
በመጨረሻም በምግብ ራስን መቻል፣ በምርታማነትና በአደጋ ስጋት አይበገሬነት ዙሪያ የተያዙ ዕቅዶችን በተግባር ለማሳካት የሁሉም የሥራ አካላትና የማህበረሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ ተገልጿል።