09/07/2026
የኤሌክትሮኒክ ደረሰኝ ሥርዓት አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 1142/2018 በአጭሩ
***********************************
የታክስ አስተዳደራችንን ዘመናዊ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ እንዲሁም የግብር ስወራን ለመከላከል የገቢዎች ሚኒስቴር አዲስ የኤሌክትሮኒክ ደረሰኝ ሥርዓት አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 1142/2018 (Directive No. 1142/2026) አውጥቷል።
በመመሪያው የተካተቱ ዋና ዋና ነጥቦች፦
•ዲጂታል ደረሰኝ (Electronic Invoice)፦ በየቀኑ የሚደረጉ ግብይቶች በሚኒስቴሩ እውቅና ባገኘ ሶፍትዌር አማካኝነት ዲጂታል ሆነው ይመዘገባሉ። እያንዳንዱ ደረሰኝ ልዩ የደረሰኝ ምዝገባ ቁጥር (IRN) እና ፈጣን መላሽ ኮድ (QR Code) ይኖረዋል።
•የኢኮሜርስ (e-Commerce) እና የዲጂታል ገበያ ቦታዎች፦ በኦንላይን መድረኮች ላይ የሚከናወኑ ግብይቶችም በተናጠል በሻጩ የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር (TIN) ደረሰኝ እንዲቆርጡ ሥርዓት ተዘርግቶላቸዋል።
•ከቀጥታ ግንኙነት ውጭ (Offline Mode) መሥራት፦ የኢንተርኔት ግንኙነት በሚቋረጥበት ወቅት ግብይት እንዳይስተጓጎል ለተወሰነ ጊዜ ከመስመር ውጭ ሽያጭን መመዝገብና ግንኙነቱ ሲመለስ በቀጥታ ወደ ማዕከላዊ ሲስተሙ መላክ የሚያስችል አማራጭ ተካቷል።
• ጠንካራ የደህንነት ሥርዓት፦ ጥቅም ላይ የሚውሉ የሽያጭ መመዝገቢያ ሶፍትዌሮች ሁሉ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የደህንነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ማቅረብ ይኖርባቸዋል።
ለአቅራቢዎችና ለአገልግሎት ሰጪዎች የተቀመጡ ቅድመ-ሁኔታዎች፦
•የዕውቅና ምስክር ወረቀት ለማግኘት አልሚዎችና አቅራቢዎች እንደየዘርፋቸው ተስማሚ የባለሙያ ብዛትና በየሁለት ዓመቱ የሚታደስ የመልካም አፈጻጸም ዋስትና (Performance Guarantee) በባንክ ወይም በመድን ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፦
•የሽያጭ መመዝገቢያ ሥርዓት አቅራቢዎች፦ 30,000 የአሜሪካን ዶላር ዋስትና እና ቢያንስ 4 ባለሙያዎች
•የሶፍትዌር አገልግሎት አቅራቢዎች ፦ 50,000 የአሜሪካን ዶላር ዋስትና እና ቢያንስ 6 ባለሙያዎች
•የኢኮሜርስ ኦፕሬተሮች፦ 25,000 የአሜሪካን ዶላር ዋስትና
•ለራሱ ብቻ የሚጠቀም ታክስ ከፋይ፦ 15,000 የአሜሪካን ዶላር ዋስትና
የዋስትና መጠኑና የባለሙያዎቹ ብዛት እንደ ታክስ ከፋዮች ብዛትና ዓመታዊ ጥቅል የሽያጭ መጠን ሊጨምር ይችላል። ይህ መመሪያ በታክስ ሕጉ መሠረት የሂሳብ መዝገብ በሚይዙ ሁሉም ታክስ ከፋዮች ላይ ተፈጻሚ ይሆናል።